የሱዳንን ግጭት ለማስቆም ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናከሩ

ካርቱም

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሳምንት ሊደፍን የተቃረበውን የሱዳን ግጭት በአስቸኳይ ለማስቆም ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ተጠናክረው ቀጠሉ።

ባለፉት ቀናት የአገሪቱ መደበኛ ጦር ከፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ ጋር ሲዋጋ የቆየ ሲሆን በግጭቱ ቢያንስ 300 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ የተጎዱ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ደግሞ መኖሪያቸውን ጥለው ተሰደዋል።

የተባበሩት መንግሥታት፣ አሜሪካ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ እና ጎረቤት አገራት የኢድ አል-ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ለሦስት ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለሰብዓዊነት ተግባር ለ72 ሰዓታት ተኩስ ለማቆም ተስማምቻለሁ ብሏል። ይህ ኃይል የተኩስ አቁሙ ተፈጻሚ የሚሆነው በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር አርብ ከንጋት 12 ሰዓት ጀምሮ ይሆናል ብሏል።

ቡድኑ ለ72 ሰዓታት የሚቆይ የተኩስ አቁም አድርጊያለሁ ቢልም ከዚህ ቀደም በሁለቱም ተዋጊዎች ከስምምነት ተደርሶባቸው የነበሩ የተኩስ አቁም ስምምነቶች ተጥሰው ነበር።

ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል የተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት ተስፋ የመጣው የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ እና ምዕራባውያን ሰላማዊ ሰዎች ከተኩስ ቀጠና እንዲወጡ ተኩስ እንዲቆም ከጠየቁ በኋላ ነው።

“ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት በአሁኑ ሰዓት እጅግ በጣም ወሳኝ ነው” ብለዋል ጉተሬዝ።

ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት ስለመከበሩም ሆነ የአገሪቱ ጦር በተኩስ አቁሙ ስለመስማማቱ እስካሁን ግልጽ አይደለም።

ቀደም ሲል የአገሪቱን ጦር የሚመሩት ጀነራል አብደለ ፋታህ አል-ቡርሃን ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ጋር የሚደረግ የትኛውንም አይነት ድርድር ውድቅ አድርገዋል።

ከግጭቱ መቀስቀስ በኋላ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ሕጻናት የሆኑ ከ10ሺህ እስከ 20ሺህ የሚገመቱ ሰዎች ከሱዳን ሸሽተው ወደ ቻድ መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ገልጿል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ተዋጊዎች ቢያንስ እስከ እሑድ ድረስ ተኩስ ለማቆም እንዲስማሙ ጠይቀዋል።

ብሊንከን በመግለጫቸው አገራቸው በሱዳን ስላሉ ሰላማዊ ሰዎች፣ የሰብዓዊ ድርጅት ሠራተኞች እንዲሁም አሜሪካውያንን ጭምሮ የዲፕሎማቶች ደኅንነት እጅግ አሳስቧታል ብለዋል።

የሱዳን ጦር በመግለጫው እንዳለው ጀነራል አል-ቡርሃን ከቱርክ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከኢትዮጵያ መሪዎች እንዲሁም ከአሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የካታር የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች የስልክ ጥሪ ደርሷቸዋል።

ግጭቱን ተከትሎ በርካቶች መኖሪያቸውን ጥለው ተሰደዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ግጭቱን ተከትሎ በርካቶች መኖሪያቸውን ጥለው ተሰደዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የግጭቱ ማዕከል የሆኑት የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይል አዛዥ ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ናቸው።

ሁለቱም ጀነራሎች በሕዝባዊ ተቃውሞ እአአ 2019 በቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦማር አል-በሽር ላይ ፊታቸውን ከማዞራቸው በፊት በፕሬዝዳንቱ ሥር ሲያገለግሉ ነበር።

ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ ሁለቱ የጦር ጀነራሎች በሱዳን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆነው ቀጥለዋል። ጀነራሎቹ በሱዳን ሥልጣን ለሲቪል አስተዳደር ለማስተላለፍ ተስማምተናል ይበሉ እንጂ ዳጋሎ የሚመሩት የልዩ ኃይል አባላቱ ወደ አገሪቱ ጦር ስለሚቀላቀሉበት ሁኔታ መስማማት አልቻሉም።

አል-ቡርሃን ወደ 120ሺህ የሚጠጋ ጠንካራ ሠራዊት ያላቸው ሲሆን ዳጋሎ ደግሞ ወደ 150ሺህ የሚጠጋ ወታደር አላቸው።

አል-ቡርሃን እና ዳጋሎን የሚያጋጫቸው ጦራቸው በአንድ ተዋህዶ ማን ይመራዋል የሚለው ብቻ ሳይሆን አለመግባባቱ የጥቅም ጉዳይም አለበት።

ሱዳን ወደ ውጭ ልካ ብዙ ገንዘብ ከምታገኝባቸው ምርቶች መካከል ወርቅ ቀዳሚው ነው። የዳጋሎ ቤተሰብ ደግሞ በወርቅ ሽያጭ እና በወርቅ ማውጫ ስፍራዎች ላይ እጁ ረዥም ነው።

ወርቅ ገንዝብ ከማስገኘቱም በላይ በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ አለው። አብዛኛው ወርቅ ወደ ተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የሚሄድ ነው። የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊው ቡድን ዋግነር በማዕድን ማውጣት ሥራዎች ላይ ፍላጎት አለው።

ከዚህ ውጭ በአፍሪካ በቆዳ ስፋት ሦስተኛ ደረጃ ላይ በምትገኘው ሱዳን የሚከሰተው አለመረጋጋት ከአገሪቱ አልፎ በቀጠናው ላሉ እና ለመላው ዓለም ስጋት ነው።

በሱዳን ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንዲኖራቸው ፍላጎት ያላቸው አሜሪካ፣ ሩሲያ እና ሳዑዲ አረቢያ በምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር እየሆነ ያለውን በቅርበት እየተከታተሉ ይገኛሉ።