የሱዳን ቀውስ በጎረቤት አገራት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሱዳን ላለፉት ቀናት በግጭት እየታመሰች ነው። ሁለት ጀነራሎች አንጃ ፈጥረው ለስልጣን ሽሚያ ግጭት ውስጥ ገብተዋል።
የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት እና የአገሪቱ መከላከያ ኃይል አዛዥ ናቸው።
ከመደበኛ ሠራዊቱ ጋር ጦር የገጠመው ፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይል ደግሞ በሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራ ነው።
በሁለቱ ጀነራሎች መካከል የተፈጠረው የስልጣን ሽሚያ ውጥረት ፈንድቶ በመዲናዋ ካርቱም እና በበርካታ ከተሞች ግጭት ቀስቅሷል። የበርካቶችንም ሕይወት ቀጥፏል።
የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ኦማር አል በሽርን ከስልጣን መወገድ ተከትሎ ወንበሩን የተቆጣጠረው የሲቪል አስተዳደር ብዙም ሳይቆይ ከኃላፊነቱ ተነሳ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ሱዳን በሉዓላዊ ምክር ቤት በሁለቱ የጦር ጀነራሎች ስትመራ ቆይታለች።
የግጭቱ ማዕከልም እነዚህ ሁለት የጦር ጀነራሎች ነው። ጀነራሎቹ ሱዳንን የማስተዳደር ስልጣን ለሲቪል አስተዳደር ለማስተላለፍ ተስማምተናል ብለዋል። የፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይል አባላትንም ወደ አገሪቱ መደበኛ ጦር እንደሚቀላቀሉ መስማማታቸውን ገልጸዋል።
ሄምቲ በሚለው ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት ጀነራል ዳጋሎ የሚመሩት 100 ሺህ አባላት ያሉትን የፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይል የአገሪቱን ጦሩን መቼ ይቀላቀላል፤ ጥምር ጦሩንስ ከዚያ በኋላ ማን ይመራዋል በሚለው ሁለቱ ጀነራሎች መግባባት አልቻሉም።
ከግጭቱ መቀስቀስ በፊት ውጥረት ነግሶ ነበር። ግጭት ይቀሰቀሳል ተብሎ ግን አልተጠበቀም። ሱዳናውያን እምነታቸው ወዲህ ነው፤ የጦር ጀነራሎቹ ልዩነቶቻቸውን በንግግር ይፈታሉ የሚል ነበር። ጀነራሎቹ ግን ሌላኛውን መንገድ መረጡ።
የሱዳን እጣ ፈንታንም ጥያቄ ውስጥ ከትቷል። ስጋቱ ግን ለሱዳናውያን ብቻ አይደለም።
በሱዳን ያለው ሁኔታ ተባብሶ ከቀጠለ መዘዙ ለምስራቅ አፍሪካም የሚተርፍ መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞቹ አደም ካሴ እና ዓብዱራህማን ሰይድ አቦ ሓሽም የሚስማሙበት ጉዳይ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አቦ ሓሽም ከቢሲሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ፕሬዝዳንት አል በሽር ላይ መፈንቅለ መንግሥት በተካሄደበት ማግስት ወታደሩ ወደ ፖለቲካዊ ስልጣን ክፍፍል ከገባ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ቀድመው መረዳታቸውን ይናገራሉ።
ለዚህ ደግሞ ሁለት ጉዳዮችን በምክንያትነት ያስቀምጣሉ።
አንደኛው ወታደሩ ስልጣን ከያዘ ለመልቀቅ ፈቃደኛ አይሆንም የሚል ነው። ሕዝቡን ለማረጋጋት ያህል እንዲያው ለነገሩ ‘ስልጣኑን ወደ ሲቪል አስተዳደር እናስረክባለን’ ይበሉ እንጂ ውሳኔው ከልብ የመነጨ አልነበረም ይላሉ።
ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በሠራዊቱ ውስጥ ያለው ክፍፍል ነው። ሄምቲ የሚመሩት ጦር ለሃገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት ደጋፊ መስሎ ቢታይም ከመፈንቅለ መንግሥቱ ማግስት ራሱን ችሎ ነበር የወጣው። ይሄም አደገኛ ነገር እንደሚያስከትል ግልጽ ነበር ሲሉ ተንታኙ ይገልጻሉ።
የፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይሉ በሃገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰን ከሌሎች አገሮች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ማድረጉ፤ ወታደሮቹን ወደ የመንና ሊቢያ ማሰማራት መቻሉ፤ በትጥቅ፣ በገንዘብም ሆነ በዲፕሎማሲ ከዋናው ሠራዊት ልቆ መሄዱን ማሳያ መሆኑን ያስረዳሉ።
“[የፈጥኖ ደራሹ ልዩ ኃይሉ] ጉልበት እያገኘ ነበር የመጣው። ውሎ አድሮ ወደዚህ ግጭት እንደሚገባ የታወቀ ነበር” ይላሉ አቦ ሓሽም።
ልዩ ኃይሉ የአገሪቱን ጦሩን መቼ ይቀላቀላል፤ ጥምር ጦሩንስ ከዚያ በኋላ ማን ይመራዋል የሚለው አለመግባባትም የተወለደው ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው።
“በአንድ አገር ሁለት የታጠቁ ሃይሎች ሊኖሩ አይችሉም። በተለይ የታጠቀ፤ የራሱ አመራር ያለው፤ የራሱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚያካሂድ ጦር የሃገሪቱን ሠራዊት አቅምና ተቀባይነት ያሳንሳል እንጂ አያጠነክረውም። ይህ አንድን ሃገር ለመጠበቅና ለመከላከል አቅም አይሰጥም” ሲሉ ያክላሉ።
ግጭቱ ግን የሱዳናዊያን ብቻ ነው ብሎ ማሰብ አይገባም የሚሉ በርካቶች ናቸው።
ሱዳን እና ጎረቤት አገራት
በሱዳን ጉዳይ ቀጥተኛ ፍላጎት ያላቸው ጎረቤት አገራት በርካቶች ናቸው።
የአሁኑ ግጭት የተቀሰቀሰበት ምስራቅ አፍሪካ ለወትሮውም ቢሆን ከግጭት የራቀ አይደለም። ግጭት ባይኖር እንኳን ውጥረት የሰፈነበት ቀጠና ነው። የፖለቲካ ተንታኙ አደም ካሴ በሱዳን ግጭት የተቀሰቀሰው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ባለበት ወቅት መሆኑን ይጠቅሳሉ። በደቡብ ሱዳንም ሆነ በኤርትራ የፖለቲካ ውጥረት ያለ መሆኑን ያስታውሳሉ።
“የቀይ ባህር መስመር የዓለም መሠረታዊ የንግድ መስመር ነው። ይህን ጨምሮ ሱዳንም ትልቅ ሃገር ከመሆኗ አንጻር ለአጭርም ሆነ ለረዥም ጊዜ ግጭት መፈጠሩ ለቀጠናው ከፍተኛ የሆነ ችግር ነው የሚፈጥረው” ሲሉ ይገልጻሉ።
ሱዳን ውስጥ የሚሆነውን ነገር በአሉታም ሆነ በአዎንታ ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው ይችላል።
በተለይም ችግሩ ከተባባሰ ነገሮች ውስብስብ እንደሚሆኑ ያነሳሉ።
መፈናቀል እና ሰዎች ወደ ጎረቤት አገራት መሰደድ ሊጀምሩ እንደሚችሉም ጠቁመዋል።
በግጭቱ መሐል ከግብጽ በስልጠና ሊሳተፉ የመጡ ናቸው የተባሉ ወታደሮች በልዩ ኃይሉ መሬዌ በተባለ ስፍራ ‘በቁጥጥር ስር’ መዋላቸው ተዘግቧል።
“ግብጽ አል-ቡርሃንን ትደግፋለች። ካይሮ ምን ዓይነት እርምጃ እንደምትወስድ እናያለን። ቁጭ ብላ ግን አታይም። ሁኔታው ያሰጋታል። አንደኛ ነገር ሰፊ ድንበር ይጋራሉ፤ ሁለተኛው ደግሞ የአባይ ወንዝ በሱዳን ነው የሚያልፈው” ይላሉ አቦ ሓሽም።
ስለዚህ የካርቱምን ዕጣ ፈንታ ካይሮ በቅርበት ትከታተላለች።
ወደ ስልጣን የሚመጣው ኃይል በአባይ ዙሪያ የሚይዘው አቋም ያሳስባታል። የካይሮን ፍላጎት የሚጻረር ኃይል ወደ ስልጣን እንዳይወጣ ትሰጋለች። ስለዚህ ወደ ሱዳን የመግባት ዕድልዋ ሰፊ ሊሆን እንደሚችልም ያነሳሉ።
ቀደም ሲል የነበራትን እጅ አዙር አካሄድ በመተው ‘በግላጭ’ ልትሳተፍ እንደምትችልም ይገምታሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያም ብትሆን በሱዳን ጉዳይ ብዙ ይመለከተኛል የምትላቸው ጉዳዮች አሉ።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ እንዲሁም ሁለቱ አገራት በድንበር ከመተሳሰራቸውም በተጨማሪ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሱዳን ውስጥ ይኖራሉ።
በሱዳን የሚሆነው ነገር ሁለቱ ሃገራት በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ የራሱ ተጽዕኖ ይኖረዋል።
“ግጭት እስካለ ድረስ በግድቡና የድንበር ጉዳዮች ላይ ሠላማዊ ነገር የመምጣት ዕድሉ ይጠባል። ነገር ግን ግጭቱ በሠላም የሚያልቅ ከሆነ እና ስርዓት ያለው ነገር ከተፈጠረ የሱዳንን ህዝብ ጥቅም አስቀድሞ የሚሠራ ካለ በተለይ ግድቡን በሚመለከት ጥሩ ደረጃ ሊደረስ ይችላል” ይላሉ አቶ አደም።
እንደ ተንታኙ ከሆነ ግጭቱ ከቀጠለ ግን ለግድቡም ሆነ ለህዝብ እንቅስቃሴው ከፍተኛ የሆነ አደጋ ሊኖረው ይችላል።
የኤርትራና የቻድ ሁኔታም ሌላ የሚነሳው ጉዳይ ነው። “በምስራቅ በኩል ሱዳንን ከኤርትራ ጋር የሚያገናኛት ነገር ብዙ ነው። የኤርትራ መንግሥት እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም። የኤርትራና የቻድ መንግሥታት ከሄምቲ ጋር የሚወግኑ ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ነገሮችን ግጭቱን ሊያወሳስቡ ይችላሉ” ሲሉ አቦ ሓሽም ያስረዳሉ።
የሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ ጦሯን ወደ ትግራይ ማንቀሳቀሷን ተከትሎ የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በመግባት ዘልቆ በመግባት የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን በርካታ አካባቢዎች መቆጣጠሩ ይታወሳል።
ይህንን ከግምት በማስገባት ኢትዮጵያ አሁን እነዚህን አካባቢዎች መልሳ ለመቆጣጠር ዕድል አላት የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ።
እነዚህን ቦታዎች በዚህ ወቅት መልሶ የመውሰዱ እሳቤ “ጉዳዩን በሠላም ከመፍታት አንጻር፤ ግድቡን በሚመለከት ካለን ግንኙነት፤ ሰፊ ድንበር የምንጋራ ጎረቤት አገር እንደመሆናችንና በዓለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ያለንን ተቀባይነት ሊያዳክም የሚችል” በመሆኑ አካባቢውን በኃይል መልሶ ለመያዝ ጥረት ማድረጉ አዋጭ አለመሆኑን አደም ያስረዳሉ።
የተሻለው አማራጭ ለጉዳዩ በሠላማዊ በንግግር ቋሚ መፍትሔ ማበጀት መሆኑን ይጠቁማሉ።
ሱዳን እና እጣ ፈንታዋ
ለአቦ ሓሽም ጉዳዩ የዜሮ ድምር ውጤት ሆኗል።
“[ሁለቱም ወገኖች] ዜሮ ሳም ጌም [የዜሮ ድምር ውጤት] ውስጥ ገብተዋል። ይህ ማለት አንደኛው ማሸነፍ አለበት። ሁለቱም እያሉ ያሉትም እንደዚያ ነው። አንደኛው ሌላውን ለማጥፋት ወይም ደግሞ በቁጥጥር አውሎ ለማሰር እያሰበ ነው ያለው” ሲሉ አቦ ሓሽም ያስረዳሉ።
“በእርግጥ ሱዳናዊያን የሚለዩበት የእርቅ ባህል አላቸው” የሚሉት አቦ ሐሽም “እርቅ የማውረድ አቅም አላቸው። አሁን በተፈጠረው ሁኔታ ግን ወደዚያ የሚወስድ ዕድል ያላቸው አይመስለኝም። ስለዚህ አንዳቸው ማሸነፍ አለባቸው።“
“ምናልባትም መሸናነፍ የማይችሉ ከሆነ፤ በሁለቱም መካከል ዕርቅ ተፈጥሮ ይቅር ተባብለው ወታደሩ በአጠቃላይ ከስልጣን እንዲርቅ ስምምነት ላይ የሚደርሱ ከሆነ ብቻ ለአገሪቱ መልካም ዕድል ይሆናል” ይላሉ።
ህዝቡም ሲቪል አስተዳደር ስለሚፈልግ ዓለም አቀፍ ጫና ተጨምሮበት ከስምምነት ከደረሱ ተስፋ አለ።
“ይህ ካልሆነ ልክ ሶማልያ ውስጥ የሆነው ዓይነት የእርስ በእርስ ግጭትና መበታተን ሊያጋጥም ይችላል” ሲሉ አቦ ሓሽም ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ሱዳን እና የኢትዮጵያ ሚና
ይህ ግጭት ለሌሎችም ዕድል ሊፈጥር ይችላል።
ግጭቱ በሠላም እስከ አልተጠናቀቀ ድረስ ለኢትዮጵያም ሆነ ለኤርትራ አደጋ አለው።
“በኢትዮጵያ በኩልም ሰፊ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። እንደ ኢትዮጵያም ይህንን ነገር ተገንዝቦ ጥበቃውም ሁሉም ነገር የተደራጀ ይሆናል ብዬ አስባለሁ” የሚሉት አቶ አደም፤ ኢትዮጵያ ግጭቱ በሠላም አንዲጠናቀቅ ግፊት ብታደርግ የተሻለ እንደሚሆን ያስረዳሉ።
ግጭቱ እንዲቆም በተናጥል ካልሆነም ከኢጋድ፣ ከአፍሪካ ህብረት እና ሌሎች አጋሮች ጋር ግፊት በማድረግ ሁለቱም ወገኖች ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመጡ ማድረግ እንደሚጠበቅባት ያነሳሉ።
“ለኢትዮጵያ የሚጠቅመውን፤ ለሱዳናውያንን የተሻለ የሚሆነው አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትገባ እገዛ ማድረግ ነው። ለራሳችንም ሠላምን የሚያመጣው ዴሞክራሲ ነው። ሌላም ሃገር ውስጥ እንደ መርህና ስትራቴጂ አድርገን መከተል ያለብን ከአንድ አምባገነን ወይም የጦር መሪ ጋር ሠላም እየፈጠርን ጥቅማችን ከማስቀጠል ይልቅ ቋሚ የሆነ የሱዳንን ጥቅም የሚጠብቅ ግልጽ የሆነ ስርዓት ቢፈጠር ነው የሚሻለው። በመጀመሪያ ጦርነቱ እንዲቆም ከዛ ባለፈ ደግሞ ሱዳናውያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገቡ ያለንን ድጋፍ መስጠት ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ” ይላሉ አቶ አደም።












