ሩሲያ በስህተት የራሷ ከተማ ላይ ቦምብ ጣለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያ ተዋጊ ጀት በስህተት ከዩክሬን ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ ያለ ከተማው ላይ ቦምብ መጣሉን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ገለጹ።
ቤልጎሮድ የተባለ ከተማ ላይ ነው ቦምብ በስህተት የተጣለው።
የቀጠናው አገረ ገዢ ቫቼስላቭ ግላድኮቭ እንዳሉት ፍንዳታው በከተማው ማዕከል 20 ሜትር የሚሰፋ ጉድጓድ ፈጥሯል።
ሁለት ሴቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው እና ብዙ ሕንጻዎች እንደተመቱም ገልጸዋል።
ሱ-34 የተባለው ቦምብ ጣይ ተዋጊ ጀት በድንገት ቦምቡን እንደጣለ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ክስተቱ የተፈጠረው ትላንት ሲሆን የሩሲያ መገናኛ ብዙኃን እንዳሉት ምርመራ እየተካሄደ ነው።
በማኅበራዊ ሚዲያ የተለቀቁ ፎቶዎችና ተንቀሳቃሽ ምሥሎች መኖሪያ ቤቶች በፍንዳታው ተጎድተው ያሳያሉ።
አንድ ምሥል ደግሞ ሕንጻ ጣሪያ ላይ የወጣ መኪና ያሳያል።
ቤልጎርድ 370,000 ሰዎች የሚኖሩበት ከተማ ነው። ከዩክሬን ድንበር 40 ኪሎ ሜትር ይርቃል።
ከዩክሬን ከተማ ካርኪቭ በስተ ሰሜን በሚገኘው በዚህ ከተማ ከዩክሬን የሚሰነዘር የአየር ጥቃትን የሸሹ ነዋሪዎች ይገኛሉ።
የሩሲያ ጀቶች ወደ ዩክሬን ሲበሩ የሚያልፉትም በዚህ ከተማ በኩል ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images












