ኮማ ውስጥ ባለ ስፖርተኛ ስም የታተመ የኤአይ ቃለ ምልልስን ቤተሰቡ ተቃወመ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ማይክል ሹማከር ታዋቂ የፎርሙላ 1 መኪና ውድድር ኮከብ ነበር። እአአ በ2013 በበረዶ ላይ መሸራተት ላይ አደጋ ከገጠመው በኋላ ኮማ ውስጥ ይገኛል።
ሰባት ጊዜ የፎርሙላ 1 አሸናፊው ኮማ ውስጥ ቢሆንም፣ ልክ ከሱ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ በማስመሰል በኤአይ አማካይነት ቃለ ምልልስ ተዘጋጅቶ በመጽሔት ታትሟል።
የማይክል ሹማከር ቤተሰቦች በመጽሔቱ ኅትመት የተሰማቸውን ቁጣ ገልጸው፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ሊወስዱት እንዳቀዱም ገልጸዋል።
ስፖርተኛው ጭንቅላቱ ላይ ጉዳት ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ኮማ ውስጥ ነው ያለው።
‘ዳይ አኩቴ’ የተባለው የጀርመን መጽሔት የፊት ገጹ ላይ የ54 ዓመቱን ስፖርተኛ ፎቶ አትሟል።
“ማይክል ሹማከር፡ የመጀመሪያው ቃለ ምልልስ” ሲልም ለዘገባው ርዕስ ሰጥቷል።
“ሊያሳስት በሚችል ደረጃ እውነት ይመስላል” በሚልም ነው የተዋወቀው።
ቃለ ምልልሱ የተሠራው ‘ካራክተር ዶት ኤአይ’ በተባለ የሰው ሠራሽ ክህሎት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) መተግበሪያ ነው።
ልክ ስፖርተኛው ሊል እንደሚችለው ስለ ጤናው እና ቤተሰቡ የሰው ሠራሽ ክህሎቱ መልስ ሰጥቷል።
“ቡድኔ በሚያደርግልኝ ድጋፍ ታግዤ መቆም እና ቀስ በቀስም መራመድ እንደምችል አምናለሁ። ልጆቼና ባለቤቴ በረከቶቼ ናቸው። እነሱ ባይኖሩ አልችለውም ነበር። በደረሰብኝ ነገር ሁላ አዝነዋል” የሚለው ከቃለ ምልልሱ አንዱ መስመር ነው።
የስፖርተኛው ቤተሰቦች ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደገለጹት፣ መጽሔቱን ለመክሰስ አቅደዋል።
የመጽሔቱ አታሚዎች አሁን ስለ ጉዳዩ አስተያየት እንደማይሰጡ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ስፖርተኛው እአአ በ2014 ኮማ ውስጥ እንዳለ ሆኖ በቤቱ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ ስለ ጤናው ብዙም ቤተሰቡ መረጃ አልሰጠም።
ሁለት ጊዜ ፎርሙላ 1 ያሸነፈው በቤንተን ሥር ሆኖ ሲሆን አምስት ጊዜ ያሸነፈው በፌራሪ ሥር ሆኖ ነው።
በ2006 እራሱን ከስፖርቱ ቢያገልም እአአ በ2010 ወደ ውድድሩ ተመልሶ ነበር።
ከሁለት ዓመት በፊት በኔትፍሊክስ በተላለፈ ዘጋቢ ፊልም ላይ የስፖርተኛው ባለቤት ኮሪና “አብረን በቤታችን እየኖርን ነው። ሕክምና እየተሰጠው ነው። ምቾት እንዲሰማው የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን” ስትል አስተያየት ሰጥታለች።
“ቤተሰብ ሆነን ለመቀጠን እየሞከርን ነው። የግል ሕይወታችን የግላችን ነው። እስከዛሬ እሱ ሲንከባከበን እንደኖረው አሁን እኛ እየተንከባከብነው ነው” ስትልም አክላለች።












