ንግሥት ክሊዮፓትራ በኔትፍሊክስ ፊልም ላይ እንደ ጥቁር መሳሏ በግብጽ ውዝግብ አስነሳ

የፎቶው ባለመብት, NETFLIX
በአንድ ወቅት ግብጽን የመራችው ንግሥት ክሊዮፓትራ ሰባተኛን በሚያሳየው የኔትፍሊክስ ፊልም ጥቁር አፍሪካዊት ተደርጋ በመሳሏ በግብጽ ውዝግብ አስነሳ።
አንድ ግብጻዊ ጠበቃም ጥናታዊ ድራማ የሆነውን ‘አፍሪካን ኩዊንስ፡ ኩዊን ክሊዮፓትራ’ የሚል ርዕስ የተሰጠውን ፊልምም የሚዲያ ህጎችን በመጣስ ክስ አቅርበዋል።
የህግ ባለሙያው ኔትፍሊክስ በዚህ ፊልም “የግብጽን ማንነት ለማጥፋት” ሞክሯልም የሚል ቅሬታም አቅርበዋል።
ሌላኛው የቅሪተ አካል ጥናት ተመራማሪው በበኩላቸው ክሊዮፓትራ “የቆዳዋ ቀለም ቀይ የነበረች እንጂ ዘሯ ጥቁር አይደለም” ሲሉም አጥብቀው ይከራከራሉ።
የፊልም ፕሮዲውሰሯ በበኩሏ የክሊዮፓትራ የዘር አመጣጥ አከራካሪ ነው ብላለች።
የክሊዮፓትራን ገጸ ባህርይ ወክላ የተጫወተችው ተዋናይት በበኩሏ “የተመረጡትን ተዋናዮች ካልወደዳችሁ ፊልሙን አትመልከቱ” ስትልም ለተቺዎች በትዊተር ገጿ ላይ ጽፋለች።
አዴሌ ጄምስ የተባለችው ተዋናይት በዚህ ፊልም ላይ በመተወኗ የደረሱባትን የዘረኝነት ስድቦችና አስተያየቶችንም ፎቶዎች በትዊተር ገጿ በማካተትም ነው አስተያየቷን ያሰፈረችው።
ንግሥት ክሊዮፓትራ የተወለደችው በግብጿ አሌክሳንድሪያ በ69 ዓመተ ዓለም ነበር።
በታላቁ አሌክሳንደር ዘመን ወቅት የመቄዶኒያው ጄነራል ፕቶለሚ የተመሰረተው የግሪክ ቋንቋ ተናጋሪ ስርወ መንግሥት የመጨረሻዋ ንግሥት ነበረች።
አባቷን ፕቶለሚ 12ኛን በ51 ኛው ዓመተ ዓለምም በመተካት እስከሞተችበት 30 ዓመተ ዓለምም ግብጽን ገዝታለች። ከንግሥት ክሊዮፓትራ ሞትም በኋላ ግብጽ በሮማውያን አገዛዝ ቁጥጥር ስር ወደቀች።
የክሊዮፓትራ እናት ማንነት የማይታወቅ ሲሆን የታሪክ ተመራማሪዎች በኩላቸው እናቷ የግብጽ ተወላጅ ወይም ከሌላ የአፍሪካ አገር የመጣች ልትሆን እንደምትችልም አስቀምጠዋል።
የኔትፍሊክስ አጋር ድረ-ገጽ የሆነው ቱዱም ከነጭና ጥቁር የተወለደችውን ተዋናይት አዴሌ ጄምስን በአዲሱ ዘጋቢ ፊልም ክሊዮፓትራን ገጸ ባህርይ እንድትተውን መመረጧም “ለዘመናት የዘለቀው የንግሥቲቷ ዘርንም አከራካሪነት የመለሰ ነው ይላሉ።
የፊልሙ ዋና አዘጋጅ እና ተራኪ የሆነችው አሜሪካዊቷ ተዋናይት ጃዳ ፒንኬት ስሚዝ በበኩሏ “ስለ ጥቁር ንግሥቶች የሚያወሱ ታሪኮችንም ማየትም ሆነ መስማትም የተለመደ አይደለም። ይህ ለእኔም፣ ለልጄም እንዲሁም ለማህበረሰባችን በርካታ ጥቁር ንግሥቶች እንደነበሩና የነሱን ታሪኮች ማወቅ መቻላቸው በጣም ጠቃሚ ነው” ብላለች።
ሆኖም የክሊዮፓትራ ፊልም ማስተዋወቂያ ባለፈው ሳምንት መውጣቱን ተከትሎ ግብጻውያንን አወዛግቧል።












