በየመን ለረመዳን እርዳታ ሲታደል በተፈጠረ መጨናነቅ 78 ሰዎች ሞቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በየመን ዋና ከተማ ሰንአ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ የረመዳን ወርን በማስመልከት ሲደረግ የነበረ ድጋፍን ተከትሎ በተፈጠረ ትርምስ ቢያንስ 78 ሰዎች መሞታቸውን ባለስልጣናት ገልጸዋል።
በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚዘዋወሩ ቪዲዮዎች በከተማዋ ባብ አል የማን በተባለ ቦታ የነበረውን ግርግር አሳይተዋል።
በስፍራው በነፍስ ወከፍ ሲታደል የነበረውን 9 ዶላር ወይም 485 ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለመቀበል በመቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በተጨናነቀ ሁኔታ በትምህርት ቤት ውስጥ ተሰባስበው እንደነበር ሮይተርስ ዘግቧል።
ከአውሮፓውያኑ 2015 ጀምሮ ከተማዋ በሁቲ አማጽያን ቁጥጥር ስር ወድቃለች።
እርዳታውን ሲያድሉ የነበሩ ሰዎች ታስረው ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ገልጿል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ እርዳታውን ከአከባቢው አስተዳደር ጋር ሳይቀናጁ በዘፈቀደ ለማደል መሞከሩ የችግሩ ምንጭ ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል።
በአደጋው በከርካታ ሰዎችም እንደተጎዱና 13 ሰዎች ደግሞ ለህይወት በሚያሰጋ ሁኔታ እንደሚገኙ በሰንአ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ገልጸዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሁቲ ባለሰልጣን ከሟቾች ውስጥ ሴቶችና ህጻናት እንደሚገኙበት ለፈረንሳይ የዜና ወኪል ገልጸዋል።
ሁለት የዓይን እማኞች ደግሞ ትርምሱን ለመቆጣጠር የሁቲ ታጣቂዎች ወደ ሰማይ እንደተኮሱና ከኤሌክትሪክ ገመድ ጋር በተፈጠረ ንክኪ ፍንዳታ እንደተሰማ ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል።
ይህም ለእርዳታ በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ በፈጠረው ፍርሃት ምክንያት መጨናነቅን እንደፈጠረ ጨምረዋል።
ይህ ክስተት ያጋጠመው የረመዳን ወር ሊጠናቀቅ ቀናት በቀረበበት ጊዜ ነው።
የመን እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 በተባባሰው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት ውስጥ የገባች ሲሆን የሁቲ አማጽያን አብዛኛውን የሀገሪቱን ምእራባዊ ክፍል ተቆጣጥረዋል።
ስምንት ዓመታትን ያስቆጠረውን ጦርነት ለማክተም ተቀናቃኝ ሃይሎች ጥረት እያደረጉ ሲሆን ባለፈው ሰምንት ያደረጉት የእስረኞች ልውውጥ የዚሁ አካል ነው።
የሁቲ አማጽያን የበላይ ኃላፊ ሞሀመድ አሎ አል ሁቲ ትላንት እርዳታ ሲሰጥ ላጋጠመው ችግር በሀገሪቱ ያለው የሰብአዊ ቀውስ ምክንያት ነው ብለዋል።












