የሱዳን ጄነራሎችን ለማደራደር ወደ ካርቱም ሊያቀኑ የነበሩት መሪዎች ጉዟቸውን ሰረዙ

ከግራ ሳልቫ ኪር፣ ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና ዊሊያም ሩቶ
የምስሉ መግለጫ, ከግራ ሳልቫ ኪር፣ ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና ዊሊያም ሩቶ

በሱዳን ከአምስት ቀናት በፊት የተከሰተውን ጦርነት ለማርገብና ሁለቱን ጄነራሎች ለማደራደር ዛሬ ሚያዝያ 11/ 2015 ዓ.ም ካርቱም ይገባሉ የተባሉት የሶስት አገራት መሪዎች ጉዟቸውን ሰረዙ።

የሱዳን ጎረቤት የሆኑት የኬንያ፣ የደቡብ ሱዳን እና የጂቡቲ መሪዎች የዛሬው የካርቱም ጉዞ የተሰረዘ ሲሆን በቀጣይም መቼ እንደሚያመሩ የተባለ ነገር የለም።

ለአምስት ቀናት የቀጠለው ግጭት ጋብ ቢል የሶስቱ አገራት መሪዎች ጄነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሸ ኃይሉ አዛኝ መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎን ለማደራደር ወደ ሱዳን እንዲገቡ ሁኔታውን ያመቻች ነበር ተብሏል።

የግጭቱ ተሳታፊዎች ለ24 ሰዓታት የሚዘልቅ ተኩስ ለማቆም ተስማምተናል ቢሉም በአገሪቱ መደበኛ ጦር ሠራዊት እና ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ መካከል የሚደረገው የተኩስ ልውውጥ ለአምስተኛ ቀን መቀጠሉን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ሁለቱ ተዋጊዎች በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ትናንት ማክሰኞ ከሰዓት 12 ሰዓት በኋላ ጀምሮ ለ24 ሰዓታት ተግባራዊ የሚደረግ ተኩስ የማቆም ስምምነት ለይ ደርሰናል ሲሉ በተናጠል ተናግረው ነበር።

ነገር ግን ዛሬ ውጊያው በጦር ሰራዊቱ ዋና መስሪያ ቤት እና ግጭቱ ከተነሳበት ጀምሮ ከተዘጋው በካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዙሪያ ነው።

ለቢቢሲ ቃላቸውን የሰጡ ነዋሪዎችም በካርቱም የጦር ማዘዣ ጣቢያ እና አየር ማረፊያ አቅራቢያ ጨምሮ በመኖሪያ መንደሮች የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ ተናግረዋል።

መሪዎቹን ለማደራደር ካርቱም ዛሬ እንደሚገቡ ሲጠበቁ የነበሩት የኬንያው ዊሊያም ሩቶ፣ የደቡብ ሱዳኑ ሳልቫ ኪር እንዲሁም የጂቡቲው ኢስማኤል ኦማር ጊሌ መቼ እንደሚያመሩ የተባለ ነገር የለም።

ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች ዝግ በሆኑባት ሱዳን፤ ዊሊያም ሩቶ፣ ሳልቫ ኪር እና ኢስማኤል ኦማር ጌሌ ካርቱም መቼ ሊደርሱ እንደሚችሉ ማወቅ አልተቻለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቀደም ሲል ግብጽ እና ደቡብ ሱዳን በሱዳን እየተዋጉ ያሉትን ኃይሎች ለማደራደር ጥያቄ አቅርበው ነበር።

የግብጽ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ ከሱዳን ጎረቤት ደቡብ ሱዳን ጋር በመሆን የአገሪቱን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አባላቱን ለማደራደር ጥያቄ ማቅረባቸውን ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ሁለቱ አገራት የማደራደር ጥያቄን ያቅርቡ እንጂ ከተዋጊ ኃይሎች የተሰጣቸው ምላሽ ስለመኖሩ የተባለ ነገር የለም።

ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች የሚመሩት ጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን እና ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ትናንት ማክሰኞ ከሰዓት 12 ሰዓት በኋላ ጀምሮ ለ24 ሰዓታት ተግባራዊ የሚደረግ ተኩስ የማቆም ስምምነት ለይ ደርሰናል ሲሉ በተናጠል ተናግረው ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ የተኩስ አቁም ስምምነት ሳይከበር ቀርቷል።

የአፍሪካ ኅብረት የሦስቱ አገራት መሪዎች ካርቱም ከደረሱ በኋላ ከሁለቱ የጦር ጀነራሎች ጋር መነጋገራቸው ተኩስ እንዲቆም ሊያደርግ ይችላል የሚል እምነት ነበረው።

እስካሁን ድረስ ምዕራባውያን፣ የአረብ አገራት እና የአፍሪካ ኅብረት ሁለቱ ተዋጊዎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም ውጊያው እንደቀጠለ ነው።

የአረብ ሊግ እና አሜሪካ ሥልጣንን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ ንግግር መጀመር አለበት ብለዋል።

የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ያደረጓቸው የሽምግልና ጥረቶች ያልተሳኩ ሲሆን ሱዳን ወደ እርስበርስ ጦርነት ልትገባ ትችላለች የሚለው ስጋት እየጨመረ ነው።

አምስተኛ ቀኑን በደፈነው የሱዳን ግጭት እስካሁን 270 ሰዎች መሞታቸውንና ጉዳት የደረሰባቸው በሺዎች የሚቆጠር መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት እና የሱዳን ዶክተሮች ህብረት አስታውቀዋል።

በመዲናዋ ካርቱም የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሆስፒታሎች ዝግ ናቸው። ሆስፒታሎቹ የከባድ መሳሪያ ጥቃት አስተናግደዋል ወይም ተዘርፈዋል።

የካርቱም ነዋሪዎችም ያለ ውሃ እና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከቤት መውጣት አልቻሉም። በርካቶችም በቤት ውስጥ ሆነው የሚበሉት ማጣታቸውን ገልጸዋል።