ለአራተኛ ቀን የቀጠለው የሱዳን ውጊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተኩስ አቁም እንዲካሄድ ከሚደረገው ግፊት በተቃራኒ በሁለቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል የሚደረገው ውጊያ ለአራተኛ ቀን ቀጥሎ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም አሁንም የተኩስ ድምጽ እየተሰማ ነው።
በካርቱም የፍትህና ዲሞክራሲ ተሟጋቿ ሃላኣ አልቃሪብ አሁንም እሷ ባለችበት አካባቢ ከፍተኛ ተኩስ እንደሚሰማ ለቢቢሲ ተናግራለች።
“ወዴትም መሄድ አይቻልም ምክንያቱም መውጣት ከፍተኛ አደጋ አለው። ደህንነቱ የተጠበቀ ምንም መንገድ ” የለም ያለችው ሃላኣ በካርቱም ያለው ሁኔታ “እጅግ አሳሳቢ” እየሆነ እንደመጣ ተናግራለች።
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የሚገኘውን የወታደራዊ ዋና መስሪያ ቤት ለመቆጣጠር በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች መካከል ከፍተኛ ውጊያ አሁንም ድረስ እየተካሄደ ነው።
በጠቅላይ ማዘዢያው አከባቢ ከፍተኛ የቦምብ ድብደባና የከባድ መሳሪያ ደምጾች እንደሚሰማ አል አረቢያ ቲቪ ዘግቧል።
በካርቱም አየርማረፊያና በሌሎችም ቦታዎች ውጊያዎች እንዳሉ ሪፖርቶች እያመላከቱ ነው።
ሁለቱም ተቀናቃኞች የጦሩን ዋና ማዘዣና አየር ማረፊያውን ተቆጣጥረናል ይላሉ።
አራተኛ ቀኑን የያዘውን እና ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች የተገደሉበትን ውጊያ እንዲቆም በርካታ ዓለም አቀፍ ጥሪዎች እየቀረቡ ነው።
የመንግስታቱ ድርጅት ልዩ መልዕክተኛና የሱዳን ተቀናቃኝ መሪዎች ግንኙነት
በተያያዘ የመንግስታቱ ድርጅት የሱዳን መልዕክተኛ ከሁለቱ ተቀናቃኝ ቡድን መሪዎች ጋር በየቀኑ እንደሚገናኙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የተመድ ልዩ መልዕክተኛው ቮልከር ፔርተስ የሱዳንን ስልጣን ለመቆጣጠር ከሚዋጉት ሁለቱ ጄነራሎች ጋር በየዕለቱ መረጃ እንደሚለዋወጡ ነው የተናገሩት።
ልዩ መልእክተኛው መሪዎቹ ከተመድ ጋር ግንኙነት ቢኖራቸውም እርስ በእርሳቸው እንዳልተነጋገሩም አክለዋል።
ቮልከር ፔርተስ ጨምረው ሲቨል ሰዎች ከአደጋ እንዲድኑ ውጊያው ለሰብአዊነት እንዲገታና በተጨማሪም የተሟላ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚያደርጉትን ውትወታ እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል።
ተደረሰ የተባለው የተኩስ አቁም ባለፈው ዕሁድና ሰኞ ሙሉ በሙሉ ተተግብሮ አልታየም።
የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከንም የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ሃይል አዛዦችን ማነጋገራቸውን እና ደም አፋሳሹን ውጊያ እንዲያቆሙ መጠየቃቸው ተዘግቧል።
የሱዳን ዶክተሮች የሟቾች ቁጥር ወደ 200 መጠጋቱን የገለጹ ሲሆን ትክክለኛው የሞት ቁጥር ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ተገምቷል።












