በሱዳን የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ እየተፋለሙ ያሉት ሁለቱ ጄነራሎች

የሱዳን ጦር ኃይል መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) መሪ ጄኔራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በርካታ ፍንዳታዎች፣ ጥቁር ጭስ ያጨለመው ሰማይ፣ የሚወነጨፉ ሮኬቶች እንዲሁም ፍርሃት መንገስ የሱዳን የዕለት ተዕለት መራር ሁኔታ ከሆነ ቀናትን አስቆጠረ።

በሱዳን መዲና ካርቱም እንዲሁም በሌሎች በርካታ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ የሚሊዮኖች ህይወት ድንገተኛና በጣም አስገራሚ በሆነ ሁኔታ ተገለባብጧል፤ ወደከፋ ሁናቴም እየተቀየረ ነው።

የሚሊዮኖች ህይወት ስጋት ውስጥ በገባበት በዚህ ግጭት መሃል ሁለት ጄኔራሎች በባላንጣነት በጽንፍ ስፍራ ተቀምጠዋል።

የሱዳን ጦር ኃይል መሪ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መሪ ጄነራል መሃመድ ሃምዳን ዳጋሎ ወይም ሄምቲ ተፋጠዋል።

በፖለቲካ ዘላቂ ወዳጅ የለም የሚባለው ማሳያ የሆኑት ሁለቱ ጄነራሎች በአንድ ወቅት በአንድ ጎራ ተሰልፈው መፈንቅለ መንግሥት አካሂደዋል።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ የሚያደርጉት የበላይነት ፍልሚያ ሱዳንን ብጥብጥ ውስጥ ከቷታል።

የአንድ ወቅት አጋር የአሁን ባላንጣ ጄነራሎች ግንኙነት ረጅም ጊዜን አስቆጥሯል።

ሁለቱም በአውሮፓውያኑ 2003 በሱዳን ምዕራባዊ ክፍል በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ላይ ተሳትፈዋል። አገሪቷ በዳርፉር አማጽያን ላይ አካሄድኩት ባለችው የጸረ ሽምግ ውጊያም ቁልፍ ሚና እንደተጫወቱ ይነገራል።

ጄነራል ቡርሃን በዳርፉር የሚገኘውን የሱዳን ጦርም ተቆጣጥረው ነበር።

ሄምቲ የአረብ ሚሊሻዎች ስብስብ የሆነው የጃንጃዊድ አዛዥ ነበሩ። የሱዳን መንግሥት በአብዛኛው አረብ ያልሆኑትን የዳርፉር አማጺ ቡድኖችንም ለመደምሰሰስ ጃንጃዊድ ዋነኛ መሳሪያ ነበር።

በወቅቱ የብሔራዊ መረጃና ደኅነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት ማጃክ ዲ ሁለቱንም ጄነራሎች የሚያውቋቸው በዳርፉር ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2011 ደቡብ ሱዳን ስትገነጠል የመከላከያ ምክትል ሚኒስትር የሆኑት ማጃክ የአሁኖቹ ባላንጣ ጄነራሎች በወቅቱ ጥሩ የስራ ግንኙነት ነበራቸው ይላሉ።

ነገር ግን ሚኒስትሩ ለቢቢሲ እንደገለጹት ጄነራሎቹ የአገሪቷን የመሪነት ስፍራ ይቆናጠጣሉ የሚል ግምት እንዳልነበራቸው ነው።

ሄምቲ በዋነኝነት የሚሊሺያ መሪ ነበሩ ሚናቸውም “ጦሩን በመርዳት የጸረ-ሽምቅ ትግሉንም ከሚመሩት አንዱ ነበሩ።

ጄነራል ቡርሃን የረጅም ዘመን ወታደር ናቸው። ሆኖም ጦሩ በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ ባለው ስፍራ አድራጊና ፈጣሪ ነው።

ሱዳን ከብሪታንያ ቅኝ ግዛት ከተላቀቀች በኋላም እየተመራች ያለችው በአብዛኛው በጦሩ ነው። የድህረ ነጻነት ታሪኳም ገዥ ሆኖ ቆይቷል።

ሱዳንን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን በመተንተን የሚታወቁት አሌክስ ደ ዋል የሱዳን መንግሥት ሽምቅን ለመከላከል በሚል ማንኛውንም መሳሪያ ተጠቅሟል ይላሉ።

በዳርፉር የነበሩ አማጺያኑን ለመሰባበር መንግሥት መደበኛ ወታደሮችን፣ የጎሳ ሚሊሻዎችን እና የአየር ኃይልን ማጣመሩን ይናገራሉ። እነዚህንም ስልቶች ሲጠቀም በሲቪሎች ላይ ሊደርስ የሚችለውንም ጉዳት ምንም ግምት ውስጥ አላስገባም፤ በርካታ ንጹሃንም ተጨፍጭፈዋል።

የዳርፉር እልቂት በ21ኛው ክፍለ ዘመን የደረሰ አንደኛው አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተብሎም ተፈርጇል። ጃንጃዊድ በዘር ማጽዳት፣ ጅምላ መድፈርን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም ክስ ይቀርብበታል።

ሄምቲ በመጨረሻም የጃንጃዊድ ተከታይ ተብሎ ሊገለጽ የሚችለው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች አዛዥም ሆኑ።

የሱዳኑ ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሄምቲ በየመን ውስጥ ሳዑዲ አረቢያ ለምትመራው ጥምር ጦር የሚዋጉ ወታደሮችን በገፍ ማቅረብ መጀመራቸውን ተከትሎ በስልጣንም ደረጃ አዛዥ ናዛዥ ሆነዋል።

በወቅቱ የሱዳኑ ወታደራዊ ገዥ የሆኑት ኦማር አል በሽር ሄምቲ እና የሚመሩትን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ይተማመኑበት ነበር። የታጠቁ ኃይሎችንም ለማዳከምና የእርሳቸውን ስልጣን እንዳይገዳደሩም ሄምቲ ድጋፍ ሆነውላቸው ነበር።

በመጨረሻም በአውሮፓውያኑ 2019 ለወራት ከቀጠለው ህዝባዊ ተቃውሞም በኋላ ጄነራሎቹ አል በሽርን ከስልጣን ለመገርሰስ ተባበሩ።

በዚያው ዓመትም በሲቪል የሚመራና ሉዓላዊው ምክር ቤት በበላይነት የሚያየው የሲቪልና ወታደራዊ ጥምር መንግሥት ለመመስረት ከተቃዋሚዎች ጋር ስምምነት ተፈራርመዋል።

ምክር ቤቱ በጀነራል ቡርሃን የሚመራ ሲሆን ምክትሉ ደግሞ ጄነራል ሄምቲ ሆኑ።

ይህ አመራር እስከ አውሮፓውያኑ 2021 ድረስ ለሁለት ዓመታትም ዘልቋል። ሆኖም ጦሩ ስልጣኑን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ጄነራል ቡርሃን የሱዳን መሪ ሲሆኑ ሄምቲም ምክትላቸው ሆኑ።

ሲዲግ ታወር የሉዓላዊው ምክር ቤት ሲቪል አባል የነበሩ ሲሆን ከሁለቱም ጄነራሎች ጋር በመደበኛነት ይገናኙ ነበር።

ከ2021 መፈንቅለ መንግሥት በፊት በሁኔታዎች ላይ አለመግባባቶች እንዳላዩ ይናገራሉ።

ሆኖም “ጄነራል ቡርሃን አክራሪ ሙስሊሞችንና የቀድሞ አገዛዝ አመራሮችን ወደ ወደ ቀደመ ቦታቸው መመለስ ጀመሩ” ሲሉም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“የጄነራል ቡርሃን እቅድ የቀድሞውን የኦማር አልበሽርን አገዛዝ ለመመለስ እየሰሩ መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጣ” ይላሉ።

ሲዲግ እንደሚሉት የአል በሽር አመራሮች በጄነራል ሄምቲ ላይ እምነት የላቸውም የሚል ስሜትም ስላሳደረባቸው ሄምቲ ጥርጣሬ ውስጥ መግባት የጀመሩት በዚህ ወቅት ነበር።

የሱዳን ፖለቲካ ማዕከል ያደረገው በካርቱም እና በናይል ወንዝ ዙሪያ ካሉ ብሄሮች የተውጣጡ ልሂቃንን ነው።

ሄምቲ ትውልዳቸው ዳርፉር ሲሆን የሱዳን ልሂቃን እሳቸው እና ወታደሮቻቸውን የሚመለከቱት ባቃለለ መልኩ ነው።

ሄምቲንም ሲጠሯቸው “የገጠር ዱባ” በማለት ሲሆን መንግሥትንም ለመምራት ብቁ አይደሉም ይሏቸዋል።

ሆኖም ጄነራል ሄምቲ ባለፉት ሁለት እና ሶስት አመታት ራሳቸውን እንደ ብሄራዊ መሪም እንዲሁም የተገለሉ ማህበረሰቦችም ተወካይም አድርገው ነበር ራሳቸውን የሚያዩት።

በአንድ ወቅት ለመደምሰስ ሲሞክሩ ከነበሩት የዳርፉር እና የደቡብ ኮርዶፋን አማፂ ቡድኖች ጋር አጋርነት ለመፍጠርም ሞክረዋል።

እሳቸው የሚመሩት ኃይል አሰቃቂ በሚባል ሁኔታ ሰላማዊ የሆኑ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ለመግታት ቢሞክርም ስለ ዲሞክራሲ አስፈላጊነት አጽንኦት በመስጠት ሲናገሩ ይሰማል- ጄኔራል ሄምቲ።

በሱዳን የሲቪል መንግሥት ለመመስረት የተያዘው ቀነ ገደብ ሲቃረብም በመደበኛው ጦር እና በፈጥሮ ደራሽ ኃይሉ መካከል ያለው ውጥረት እየጨመረ መጣ።

ለዚህም ትርምስ ምክንያቱ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ከዋናው ጦር ጋር እንዴት መልሶ ማዋቀር ይችላል በሚለውም ጉዳይ ላይ ከማተኮሩ ጋር የተያያዘ ነው።

የሱዳኑ ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እናም ጦርነቱ ተጀመረ። ሱዳንንም ለመቆጣጠር ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ፤ ከመደበኛው ጦር ጋር፤ ጄኔራል ቡርሃን ከጄኔራል ሄምቲ ጋር።

ጄነራል ሄምቲ ቢያንስ በአንድ መንገድ እየተዋጉ ያሉትን ጦር ፈለግ ተከትሏል። ሄምቲ ሰፊ የንግድ ኢምፓየር ገንብተዋል በወርቅ ማዕድን እና ሌሎች በርካታ ዘርፎችም ላይ ለመሰማራትም ፍላጎት እንዳላቸውም ተገልጿል።

ሁለቱም ጄነራሎች በዳርፉር እና በሌሎች አካባቢዎች አካባቢ በነበሩ ግጭቶች ሰለባ ለሆኑ ሰላማዊ ዜጎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ተደጋጋሚ ጥሪ ቀርቦባቸዋል።

በአሁኑ ወቅት የአገሪቷ ትርምስ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳይደርስ ስጋት የደቀነ ሲሆን ሁለቱ የቀድሞ አጋሮች፣ የአሁኖቹ ባላንጣ ጄነራሎች ወደኋላ የማይሉበት በርካታ ምክንያቶች አሏቸው።