በሱዳን የአሜሪካ ተሽከርካሪ ላይ ተኩስ ሲከፈት የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር ጥቃት ደረሰባቸው

ካርቱም

የፎቶው ባለመብት, AFP

ትላንት ሰኞ በሱዳን የአሜሪካ የዲፕሎማቶች አጃቢ መኪና ላይ ተኩስ ተከፍቶ እንደነበር የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን ገለጹ።

ሆኖም ሰዎች ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ብለዋል።

ለቡድን ሰባት ሀገራት ስብሰባ ጃፓን የሚገኙት ኃላፊው “ይህ ድርጊት ግዴለሽነት የተሞላበት፣ ኃላፊነት የጎደለውና በርግጥም ደህንቱ ያልተጠበቀ ነው” ብለዋል።

በሌላ በኩል በሱዳን የአውሮፓ ህብረት አምባሳደሩ ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ በተቀናቃኝ ሃይሎች ውጊያ ውስጥ ባለችው ካርቱም በሚገኘው ቤታቸው ጥቃት ደርሶባቸዋል።

አየርላንዳዊው ዲፕሎማት አይደን ኦሃራ “የከፋ ጉዳት” እንዳልደረሰባቸው የሀገራቸው ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሚሼል ማርቲን አረጋግጠዋል።

ሚኒስትሩ ጥቃቱን ዲፕሎማቶችን የመጠበቅ ግዴታ እየተጣሰበት ነው ሲሉ ገልጸውታል።

በሱዳን ከሶስት ቀናት በፊት በተቀሰቀሰው ውጊያ 185 የሚጠጉ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከ1 ሺህ 800 የሚልቁ ሰዎች ደግሞ ለጉዳት ተዳርገዋል።

ከተማዋ በአየር ጥቃትና በቀላል የቡድን መሳሪያዎች የተገዙ ውጊያዎችን እያስተናገደች ነው።

ተቀናቃኞቹ የሀገሪቱ ጦርና የፈጥኖ ደራሽ ሃይል ነዋሪዎች ፍንዳታዎችን ሸሽተው የተጠለሉባቸውን ቁልፍ የካርቱም ቦታዎች ተቆጣጥረናል ይላሉ።

የአየርላንድ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጥቃት የደረሰባቸው አምባሳደር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የአውሮፓ ህብረትን እያገለገሉ ያሉ የተዋጣላቸው የአየርላንድና የአውሮፓ ዲፕሎማት ናቸው ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

አምባሳደሩ “ እየሰጠ ላለው አገልግሎት እናመሰግናለን” ያሉት የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ “በሱዳን በፍጥነት ግጭት እንዲቆም እና ውይይት እንዲቀጥል” አሳስበዋል።

ቀደም ብሎ የአውሮፓ ህብረት የውጪ ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል የዲፕሎማቲክ ቦታዎችን እና ሰራተኞችን መጠበቅ የሱዳን ባለስልጣናት ቀዳሚ ኃላፊነት ነው ብለው ነበር።

በሱዳን የአውሮፓ ህብረት አምባሳደር አይደን ኦሃራ

የፎቶው ባለመብት, FACEBOOK/EUROPEAN UNION IN SUDAN

የአውሮፓ ህብረት ቃል አቀባይ ናቢያ ማሳራሊ ጥቃቱን ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት በሱዳን የሚገኙ ሰራተኞቹን ከሱዳን እንዳላስወጣ ገልጸዋል። የሰራተኞቻችን ደህንነት ቅድሚያ የሚጠው ነው ያሉት ቃል አቀባይዋ የደህንንት እርምጃዎች ፍተሻ እየተደረገባቸው ነውም ብለዋል።

በሱዳን ያለው ግጭትና የካርቱም አየር ማረፊያ መዘጋት ስጋት ቢጭርም የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤትም አሜሪካዊ ዜግንት ያላቸውን ሰዎች ከሱዳን የማስወጣት ዕቅድ እንደሌለ ገልጸዋል።

ሆኖም ሁሉም አሜሪካውያን ጉዳዩን “በከፍተኛው ክብደት”ና በጥንቃቄ እንዲይዙት አሳስቧል።

በሱዳን ያለው ግጭት በርካታ ሲቪል ሰዎች ሊያስከትል የሚችለውን ችግር በመሸሽ በቤታቸው የተሸሸጉ ሲሆን ግጭቱ ሀገሪቱን ጥልቅ ወደ ሆነ ትርምስ ውስጥ እንዳይከታት ተሰግቷል።