የተሳሳተ በር ያንኳኳውን ጥቁር ታዳጊ በጥይት የመታው አሜሪካዊ ተከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአሜሪካ ሚዙሪ ግዛት የተሳሳተ ቤት ያንኳኳው ጥቁር ታዳጊን የተኮሰበት አሜሪካዊ ተከሰሰ።
ታዳጊው ታናናሽ ወንድሞቹን ለመውሰድ የተሳሳተ የበር የመጥሪያ ደወል በመደወሉም ነው የተተኮሰበት።
ተኳሹ የ84 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋው አንድሪው ሌስተር ጥቃት በማድረስ እንዲሁም በትጥቅ የወንጀል ክስ እንደቀረበበት አቃቤ ህግ ተናግሯል።
ነጭ የሆነው ጥቃት አድራሽ ባለፈው ሐሙስ ምሽት ራልፍ ያርል የተባለውን የ16 ዓመት ጥቁር ታዳጊ ጭንቅላቱ ላይና ክንዱ ላይ በጥይት የመታው። ታዳጊው ሁለት ጊዜ በጥይት ቢመታም ህይወቱ መትረፍ ችሏል።
አቃቤ ህግ ጥቃቱ “ዘረኝነት” ላይ ያነጣጠረ ሊሆን እንደሚችልም አስታውቋል።
ሆኖም ግለሰቡ በጥላቻ ወንጀል ያልተከሰሰ ሲሆን የክስ ሰነዶቹም ላይ የዘር አድልዎ አልተጠቀሰም።
የክሌይ ግዛት አቃቤ ህግ ዛቻሪ ቶምፕሰን ሰኞ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ለህብረተሰቡ የማስተላልፈው መልዕክት በግዛታችን ህግ እናስከብራለን፣ በህግም እንመራለን። የሰዎች ማንነት፣ ዘራቸው ወይም ያላቸው ገንዘብ በህግ ዓይን ልዩነት የለውም” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ፖሊስ መጀመሪያ ላይ አንድሪው ሌስተርን ጥያቄ ካቀረበለት በኋላ ለቆት የነበረ ሲሆን ይህም ሁኔታ እሁድ ዕለት በመላው ከተማዋ ከፍተኛ ተቃውሞን አስነስቷል።
ሰኞ እለትም ከተጠርጣሪው ቤት ውጭ የተሰበሰቡ ተቃዋሚዎች “ጥቁሮች እየተጠቁ ነው”፣ “ተነሱ፣ ታገሉ” የሚሉ መፈክሮችን እያሰሙ እንደነበርም በማህበራዊ ትስስር ገጾች የወጡ ቪዲዮዎች ያሳያሉ። በተጨማሪም የአንድሪው ቤትም ውድመት ደርሶበታል ተብሏል።
የታዳጊው ቤተሰብ ጠበቃ ቤንጃሚን ክረምፕ “አንድ ሰው በር ላይ ብቻ ስላንኳኳ መተኮስ አይቻልም። በር ላይ ስላንኳኳ ተኩሼያለሁ የሚለው ምክንያታዊ አይደለም” ብለዋል።
የታዳጊው ቤተሰቦች እንደተናገሩት ራልፍ ታናናሽ መንታ ወንድሞቹን ከጓደኛቸው ቤት ምሽት 4 ሰዓት ላይም ለመውሰድ በሚል ነበር ተሳሳቶ የአንድሪው ቤት ያንኳኳው።
ራልፍ 115 ቴራስ የሚባለውን ጎዳና በማሳሰት 115ኛ ጎዳና በመሄድ የግለሰቡን የበር መጥሪያ ደወል ሁለት ጊዜ ደውሏል። ታዳጊው ከተተኮሰበት በኋላም በአቅራቢያው የሚገኙ ቤት ባለቤቶችም ረድተውታል ብለዋል።












