ስሙ የናኘው የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል

የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አባል የጫነ መኪና የሄምቲን ምስል ለትፎ ይታያል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ በተቃዋሚዎች እና ማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ በሚወስደው ጭካኔ የተመላበት እርምጃ ስሙ ደጋግሞ ይነሳል

ራፒድ ሰፖርት ፎርስ ተብሎ የሚጠራው የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል የሱዳንን የወደፊት እጣ ፈንታ መወሰን የሚችል ኃይል ሆኗል።

ይህ ቡድን በአገሪቱ የሲቪል አስተዳደር በመመስረት ሱዳንን ወደ ዘላቂ ሰላም ለመውሰድ በሚደረገው ጥረት በተከሰተው አለመግባባት ውስጥ ማዕከል ሆኗል።

እአአ 2021 ላይ የአገሪቱ ጦር ከሲቪል አስተዳደር ጋር በስልጣን ክፍፍል አገር ሲያስተዳደር የነበረውን ሲቪል መንግሥት ከስልጣን አስወግዶ ነበር።

ከዚያ በኋላ የዴሞክራሲ ስርዓትን የሚናፍቁ ሱዳናውያን በየሳምንቱ አደባባይ እየወጡ ጦሩ እጁን ፖለቲካ ውስጥ ማስገባቱን አጥብቀው ሲቃወሙ ቆይተዋል።

ከዚህ በኋላም ልዩ ኃይል እና የአገሪቱን ጦር የሚመሩት የጦር ጀነራሎች ስልጣን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማስተላለፍ ከስምምነት ደርሰው ነበር።

ይሁን እንጂ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አባላቱ ወደ አገሪቱ ጦር የሚቀላቀሉበት ጊዜ እና ጦሩን ማን ይመረዋል የሚለው አለመግባበትን ፈጥሯል።

ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይልን የሚመሩት እና የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ጀነራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ኃይላቸው ጦሩን የሚቀላቀልበትን ሁለት ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው ነበር።

ሄምቲ በሚለው ቅጽል ስማቸው በስፋት የሚታወቁት ጀነራሉ፤ በአል-በሽር አስተዳደር ወቅት ጦሩ ውስጥ የነበረው እስላማዊ አጀንዳን የሚያራምዱ አመራሮች ከጦሩ መባረር አለባቸው ከማለታቸውም በተጨማሪ ሁለቱን ኃይሎች ለማዋሀድ ከ5-10 ዓመታት ጠይቀዋል።

ይሁን እንጂ የሉዓላዊ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት እና የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጀነራል አል-ቡርሃን ግን ሁለቱን ኃይሎች ማዋሀድ ያለብን በሁለት ዓመት ውስጥ ነው ይላሉ።

ባለጸጋው እና የጦር አበጋዙ ሄምቲ በዚህ ቢስማሙ በሱዳን ያላቸው ፖለቲካዊ ተጽእኖ ያከትማል።

ስለዚህ ይህ ለሄምቲ የሚዋጥ አይደለም።

ሄምቲ እአአ 2019 ላይ ከካርቱም 60 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ መንደር ለደጋፊዎቻቸው ሰላምታ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሄምቲ እአአ 2019 ላይ ከካርቱም 60 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ መንደር ለደጋፊዎቻቸው ሰላምታ ሲሰጡ

ቁልፍ እውነታዎች

ፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል በይፋ ተመስርቷል የሚባለው እአአ 2013 ነው።

ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሲመሰረት አብዛኛው አባላቱ የነበሩት በዳርፉሩ ግጭት በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት የሚከሰሱት የጃንጃዊድ ሚሊሻ አባላት ናቸው።

ይህ ኃይል በአውሮፓውያኑ 2014 እና 2015 በሱዳን በሚንቀሳቀሱ አማጺያን ላይ ኦፕሬሽኖችን አካሂዷል። ታዲያ በእነዚህ ኦፕሬሽኖች ቡድኑ ከሕግ ውጪ በሆነ ግድያ፣ በአስገድዶ መድፈር፣ በማስቃየት እና በዘረፋ ስሙ ተደጋግሞ ይነሳል።

የሄምቲ ልዩ ኃይል ጉልበቱ የጨመረው ከሳዑዲ ጎን ተሰልፎ በየመን መዋጋት ሲጀምር ነው።

ወደ 40ሺህ የሚጠጉ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አባላቱ ከሳዑዲ አረቢያ እና ከተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ድጋፍ እያገኘ በየመን የሁቲ አማጺያንን ወግቷል።

ይህ ኃይል በየመን ብቻ አልተገደበም። በሊቢያም ተዋግቷል። 1ሺህ ያክል የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አባላቱ ጀነራል ካሊፍ አፍጣር ጎን ተሰልፎፈው በሊቢያ ምድር ተዋግተዋል።

ሄምቲ በጉልበታቸው በዳርፉር የሚገኙ ማዕድን ማውጫዎችን ከሌሎች የሚሊሻ መሪዎች ከነጠቁ በኋላ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በወርቅ ንግድ ሃብት አካብቷል።

አርኤስኤፍ ከዳርፉር እልቂት እስከ እስከ አሁን ድረስ በከፋ የሰብዓዊ መብት ጥስት ይከሰሳል።

ይህ ቡድን በተሳተፈባቸው ውጊያዎች በከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ይከሰሳል።

እአአ 2019 ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በአገሪቱ እንዲኖር ለመጠየቅ አደባባይ የወጡ 120 ዜጎችን በመግደልም የሄምቲ ኃይል ተጠያቂ ይደረጋል።

ሄምቲ ግን “እናት አገርን እና እራሳቸውን መከላከል የማይችሉትን ለመጠበቅ” ሲባል አስፈላጊው እርምጃ ተወስዷል ይላሉ።