የሱዳን ጀነራሎች ደረስንበት ያሉት የተኩስ ማቆም ስምምነት ሳይከበር ቀረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሱዳኑ ግጭት እየተዋጉ ያሉት ሁለቱ የጦር ጀነራሎች ለ24 ሰዓታት የሚዘልቅ ተኩስ የማቆም ስምምነት ደርሰናል ቢሉም ስምምነቱ ሳይከበር ቀረ።
ነዋሪዎች በካርቱም እና በሌሎች ከተሞች በአገሪቱ ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ መካከል የሚደረግ ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ድምጽ እንደሚሰማ፤ ተዋጊ የጦር ጀቶችም ዒላማዎቻቸውን እየመቱ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሁለቱ ተዋጊዎች በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ትናንት ማክሰኞ ከሰዓት 12 ሰዓት በኋላ ጀምሮ ለ24 ሰዓታት ተግባራዊ የሚደረግ ተኩስ የማቆም ስምምነት ለይ ደርሰናል ሲሉ በተናጠል ተናግረው ነበር።
ለሰብዓዊነት ሲባል ለ24 ሰዓት ተኩስ የሚቆመው የተጎዱትን ወደ ጤና ተቋም ለመውሰድ እና ለሰላማዊ ሰዎች የመተላለፊያ ኮሪዶር ለመክፈት ነው ተብሎ ነበር።
ይሁን እንጂ ከ12 ሰዓት በኋላም በካርቱም የጦር ማዘዣ ጣቢያ እና አየር ማረፊያ አቅራቢያ ግጭት እንደነበረ ተነግሯል።
አምስተኛ ቀኑን በደፈነው የሱዳን ግጭት ቢያንስ 200 ሰላማዊ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ነዋሪዎች ያለ ውሃ እና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከቤት መውጣት አልቻሉም። በርካቶችም በቤት ውስጥ ሆነው የሚበሉት ማጣታቸውን ገልጸዋል።
ዱአ ታሪቅ የተባለች አንድ የካርቱም ነዋሪ በቤት ውስጥ አንድ እሽግ ውሃ ብቻ መቅረቱን እና የቀረውን ውሃ ለሁለት ዓመት ልጇ ብቻ ብላ ማስቀመጧን ትናገራለች። “በጣም ብዙ ሰዎች በተባረሪ ጥይት እና በሚሳኤሎች እየተመቱ በቤታቸው ውስጥ ተገድለዋል” በማለት በቤቷ ውስጥ ባለ ጠባብ ኮሪዶር የቤተሰብ አባላቱ ተሸሽገው እንደሚገኙ ተናግራለች።
በካርቱም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተጠልሎ የሚገኘው ተማሪ ደግሞ አንድ ተማሪ ተባራሪ ጥይት ከመታው በኋላ ሕይወቱ ማለፉን ተናግሯል።
ተማሪው የተገደለው ለተቀሩት ተማሪዎች ምግብ ለማምጣት ከተሸሸጉበት ቦታ ከወጡ በኋላ መሆኑን የሕግ ተማሪው ሞሳብ ሸሪፍ አስተድቷል።
ይህ በዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገደለው ተማሪን አውጥቶ መቅበር ስላልተቻለ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ መቀበሩ ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ቃል አቀባይ ካርቱምን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች የሚደረገው ውጊያ መቀጠሉን እና ተዋጊ ኃይሎች ግጭት ለማቆም ስምምነት ተገዢ የመሆን ምልክት እንዳላሳዩ ተናግረዋል።
ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች እንደ አየር ማረፊያ፣ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያዎችን፣ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ እና ቤተ-መንግሥትን ለመቆጣጠር ባለፉት ቀናት ሲዋጉ ቆይተዋል።
ለሥልጣን ሽሚያ በሚደረገው ውጊያ ውስጥ ጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን እና ጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ዋነኛ ተዋናዮች ናቸው።
በግጭቱ ተሳታፊዎች በጀነራል አብደል ፈታህ አል-ቡርሃን የሚመራው የአገሪቱ መደበኛ ጦር ሠራዊት እና በጀነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ የሚሊሻ አባላት ናቸው።
እነዚህ ሁለት የጦር ጀነራሎች በሱዳን ሥልጣን ለሲቪል አስተዳደር ለማስተላለፍ ተስማምተናል ያሉ ቢሆንም፤ ጀነራል ዳጋሎ የሚመሩት የልዩ ኃይል አባላት ወደ አገሪቱ ጦር በሚቀላቀልበት ሁኔታ መስማማት አልቻሉም።
ሁለቱ የጦር ጀነራሎች ወደ ውይይት ተመልሰው ልዩነቶቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ እየቀረበላቸው ይገኛል።












