ፑቲን በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ሥር የምትገኘውን የዩክሬን ኼርሶን ግዛትን ጎበኙ

የፎቶው ባለመብት, KREMLIN
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጦራቸው ቁጥጥር ሥር የሚገኘውን የዩክሬን ኼርሶን ግዛትን ጎበኙ።
እንደ ክሬምሊን ከሆነ ፕሬዝዳንቱ በግዛቱ የተገኙት ከጦር መኮንኖች የሚቀርብ ሪፖርትን ለመስማት በተጠራ ስብሰባ ላይ ተሳታፊ ለመሆን ነው።
ፑቲን ከኼርሶን በተጨማሪ የሩሲያ ጦር ከአንድ ዓመት በፊት ጠቅልሎ በያዛት ሉሃንስክ ግዛት ጉብኝት ማድረጋቸው ተገልጿል።
ምንም እንኳ ፑቲን ከሳምንታት በፊት ትልቅ ውጊያ አስተናግዳ የነበረችውን ማሪዮፖል ከተማን ጎብኝተው የነበረ ቢሆንም መሰል ጉብኝቶች ግን የተለመዱ አይደሉም።
የፑቲን ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፔስኮቭ ጉብኝቱ የተካሄደው ትናንት ሰኞ ሚያዚያ 9 ነው ቢሉም የጉብኝቱ ቀን በክሬምሊን ድረ-ገጽ ላይ ከወጣው የፑቲን ንግግር ጋር ይጻረራል።
ድረ-ገጹ ላይ ፑቲን ጉብኝት ላይ ሳሉ ንግግር ሲያደርጉ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ወጥቶ የነበረ ሲሆን ፑቲን በንግግራቸው “የትንሳዔ በዓል እየመጣ ነው” ሲሉ ይደመጣሉ። በኦርቶዶክስ ክርስትና የትንሳዔ በዓል የተከበረው ሚያዚያ 8 እንደመሆኑ የፑቲን ጉብኝትም ከዛ በፊት የተደረገ እንደሆነ ታምኗል።
በድረ-ገጹ ላይ የነበረው ተንቃሳሽ ምስል በሌላ የተተካ ሲሆን አዲስ በተጫነው ቪዲዮ ላይ ፑቲን የትንሳዔ በዓል “እየመጣ ነው” የሚለው ንግግራቸው ተቆርጦ ወጥቷል።
ፑቲን ከጦር አመራሮች ጋር በነበራቸው ስብሰባ፣ ሞስኮ የእኔ አካል ነው ስለምትለው ዛፖሬዢያ ግዛት ጥያቄዎችን ሲጠይቁ ነበር ተብሏል።
በኼርሶን ግዛት በነበረው ስብሰባ ፑቲን የጦር አመራሮቹን “ሥራችሁ ማስተጓጎል ባልፈልግም፤ የእናንተን አመለካከት መስማት ለእኔ ጠቃሚ ነው፤ ሁኔታዎች እንዴት እንደሆኑ፤ መረጃ ለመለዋወጥ ከእናንተ መስማት እፈልጋለሁ” ስለማለታቸው ተገልጿል።
የሩሲያ ጦር ዩክሬንን ከወረረ በኋላ የግዛቷ መዲና የሆነችውን ኼርሶንን መቆጣጠር ቢችልም መዲናዋን ለቅቆ ማፈግፈግ ግድ ሆኖበት ነበር። ይሁን እንጂ የሩሲያ ጦር አሁንም የተወሰነ የኼርሶን ግዛት አካልን ተቆጣጥሮ ይዟል።
ክሬምሊን የፑቲን ጉብኝትን የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አውጥቷል። በቪዲዮ ላይ ፑቲን ከጦር ሄሊኮፍተር ወርደው ታጅበው ወደ መኪና ሲገቡ፤ የጦር ማዘዣ ክፍል ውስጥ በጦር መኮንኖች መካከል ሆነው ንግግር ሲያደርጉ ይታያል።
ቀጥሎ ፑቲን የተለየ ልብስ ለብሰው ወደ ምሽግ በጦር መኮንኖች ታጅበው ሲገቡ አሳይቷል። ቢቢሲ ፑቲን የሚታዩበት ምስል የት እና መቼ እንደተቀረጸ አላረጋገጠም።
ክሬምሊን የአገሪቱ መከላከያ ሚንስትር ሰርጌ ሾይጉ እና የጦር ኃይሎች አዛዥ ቫሌሪ ጌራሲሞዝ ከፑቲን ጋር በዚህ ጉብኝት አብረው እንዳልተጓዙ ገልጿል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የሩሲያ ዋነኛ ኮማንደሮችን በአንድ ላይ በአንድ ጦር ግንባር መገኘታቸው “ትልቅ አደጋ” ስለሚኖረው ነው ብሏል።












