በሩሲያ በስለላ ክስ የታሰረው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ፍርድ ቤት ቀረበ

አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ኢቫን ጌርሽኮቪች

የፎቶው ባለመብት, AFP

አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ኢቫን ጌርሽኮቪች የእስሩን ሁኔታ ይግባኝ ለማለት ሞስኮ በሚገኘው ፍርድ ቤት ቀረበ።

ለዋል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ በዘጋቢነት ሲሰራ የነበረው ኢቫን የካተሪንበርግ በተባለች ከተማ በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በስለላ ወንጀል ተከሷል።

ጋዜጠኛው በዛሬው ችሎት ፍርድ ቤት ሲቀርብ ሰማያዊ መስመር ያለበት ሸሚዝ ለብሶና እጆቹንም በደረቱ ላይ አጣጥፎም ታይቷል።

ፎቶውን እያነሱ ለነበሩት የጋዜጠኞች ቡድን ምንም አልተናገረም።

በሩሲያ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ሊን ትሬሲ በፍርድ ቤቱ ተገኝተው ነበር።

የ31 አመቱ ኢቫን በቁጥጥር ስር የዋለው ባለፈው ወር ሲሆን በስለላ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖም ከተገኘ እስከ 20 አመታት እስር ሊጠብቀው ይችላል።

ሩሲያ ጋዜጠኛው ለአሜሪካ መንግስት ሚስጥራዊ የመከላከያ መረጃዎችን ለማግኘት እየሞከረ ነበር ስትል ወንጅላዋለች።

ሩሲያ ከሶቪየት ሕብረት አስተዳደር ዘመን ጀምሮ የአሜሪካን ጋዜጠኛ በስለላ ስትከስ የመጀመሪያዋ ነው። ድንበር የለሽ የጋዜጠኞች ቡድን ጋዜጠኛው የሩሲያ ተዋጊ ቅጥረኛ ቡድን በሆነው ዋግነር ዘገባ እያጠናቀረ ነበር ብሏል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት በበኩላቸው አሽከርካሪው በአንድ ሬስቶራንት ውስጥ ካደረሰው ከሁለት ሰዓት በኋላም ስልኩ መስራት እንዳቆመ ገልጸዋል።

የዋል ስትሪት ጆርናል ጠበቆች ሊጎበኙት የቻሉ ሲሆን ተቋሙም “ለኢቫንና ለቤተሰቦቹ የሚችለውን ድጋፍ ሁሉ እያደረገ” እንደሆነም አስታውቋል።

አሜሪካ “በስህተት ነው የታሰረው” ስትል የፈረጀች ሲሆን ከእስር ለማስፈታትም በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ነው።

ፕሬዚዳንት ባይደንን ጨምሮ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለስልጣናት የጋዜጠኛውን እስር አውግዘዋል።

የቢቢሲ የሩሲያ አዘጋጅ ስቲቭ ሮዝንበርግ ኢቫን ጎበዝ ጋዜጠኛ እና በመርህ የሚመራ ሲሉ ገልጸውታል። ቢያንስ 65 አሜሪካውያን በውጭ ሃገር ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ታስረው እንደሚገኙም የጄምስ ፎሌ ሌጋሲ ፋውንዴሽን ሪፖርት አመልክቷል።