የህንድ የህዝብ ቁጥር በቅርቡ ከቻይና እንደሚበልጥ ተመድ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ህንድ በህዝብ ቁጥሯ የዓለማችን የቁንጮነት ቦታ ልትይዝ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው መረጃ አሳየ።
በዚህም መረጃ መሰረት ህንድ ከቅርብ ወራት በኋላ ለዘመናት በአንደኛ ስፍራ ተቀምጣ የነበረችውን ቻይናንም በህዝብ ቁጥር ትቀድማለች ተብሏል።
የህንድ የህዝብ ቁጥር 1 ቢሊዮን 428 ሚሊዮን 600 ሺህ ይደርሳል የተባለ ሲሆን የቻይና የህዝብ ቁጥር ደግሞ 1 ቢሊዮን 425 ሚሊዮን 700 ሺህ እንደሚደርስ ይጠበቃል።
ህንድ ከእስያዋ ጎረቤቷ ቻይና በበለጠ 2.9 ሚሊዮን ሰዎች ይኖሯታል።
ህንድና ቻይና እያንዳንዳቸው ከ1.4 ቢሊዮን በላይ የህዝብ ቁጥር ያላቸው ሲሆን ለሰባት አስርታትም የዓለምን ህዝብ አንድ ሶስተኛውን ይዘው ቆይተዋል።
ህንድ ለመጨረሻ ጊዜ የህዝብ ቆጠራ ያደረገችው በአውሮፓውያኑ 2011 ሲሆን ከዚያ በኋላም ቆጠራ ባለመደረጉ የህዝብ ቁጥሯ በግምት የተመሰረተ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት የቻይናን የህዝብ ቁጥር ግምት ሲያስቀምጥ ሁለቱን ራስ ገዝ አስተዳደሮች ሆንግ ኮንግና ማካው እንዲሁም ታይዋንን አላካተተም።
ቻይና ታይዋንን እንደ ተገንጣይ ግዛት የምታያት ሲሆን አንድ ቀንም ትቀላቀላች የሚልም እሳቤ አላት። ታይዋን በበኩሏ ከቻይና የተለየች ሉዓላዊት ግዛት እና የራሷ ህገ መንግሥት እንዲሁም በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ መሪዎች አላት።
በህዳር ወር የዓለማችን የህዝብ ቁጥር ከ8 ቢሊዮን በላይ ሆኗል። ነገር ግን የህዝብ ቁጥር እድገቱ እንደ ቀድሞው ፈጣን እንዳልሆነና ከአውሮፓውያኑ 1950 ወዲህ አዝጋሚ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ህንድ እና ቻይናም ቢሆኑ የወሊድ እድገት መቀነስ ታይቶባቸዋል።
ቻይና በአውሮፓውያኑ 2016 በአንድ ልጅ መወሰን ፖሊሲዋን ትታ ባለትዳሮች ሁለት እና ከዚያ በላይ ልጆች እንዲወልዱ ማበረታቻ እጀምራለሁ ብትልም ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የህዝብ ቁጥሯ መቀነስ ይጀምራል ተብሏል።
በህንድ ውስጥም በአስርት ዓመታት ወዲህ የውልደት መጠን በእጅጉ ቀንሷል፤ በአውሮፓውያኑ 1950 አንዲት ሴት በአማካኝ ትወልድ የነበረው 5.7 የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወደ 2.2 አሽቆልቁሏል።












