‘ልጄ የተቀበረ ፈንጂ ሰለባ እንድትሆን አልፈልግም’ ፈንጂ አምካኟ

የፎቶው ባለመብት, Mines Advisory Group
ለዓመታት በጦርነት አዙሪት ውስጥ የቆየችው ኢትዮጵያ ፀረ ሰው ፈንጂ በጣም በከፍተኛ ደረጃ ከሚገኝባቸው የዓለማችን አገራት ትመደባለች።
በጦርነት ውስጥ ካሉት ከዩክሬን፣ ከኢራቅ፣ ከአፍጋኒስታን፣ እና የመን ጋር በቀዳሚነት ተቀምጣለች።
በትግራይ ተከስቶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተዛመተው እና የመቶ ሺዎችን ሕይወት የቀጠፈው ደም አፋሳሽ ጦርነት ከተቋጨ ወራት ብቻ ነው የተቆጠሩት።
በዚህ ጦርነት ጥቅም ላይ የዋሉ የተቀበሩ ፈንጂዎች እና ቦምቦች ዳፋ ገና አልተገመገም።
ሆኖም ኢትዮጵያ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጀምሮ ያልመከኑ ፈንጂዎች መገኛ እንዲሁም ከአውሮፓውያኑ 1998 አስከ 2000 ከኤርትራ ጋር ያደረገችው ጦርነትም በርካታ ፀረ ሰው ፈንጂዎችን አሸክሟታል።
የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ በአውሮፓውያኑ 2004 በተደረገ ጥናት የተቀበሩ ፈንጂዎች ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ የአገሪቱ ዜጎች ላይ አደጋ እንደጋረጠ የተባበሩት መንግሥታት አስታውቋል።
ከ2000 አስከ 2004 ባለው ጊዜ በተቀበሩ ፈንጂዎች ምክንያት 588 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ወደ 1 ሺህ 300 የሚጠጉ ጉዳቶችም ነበሩ።
በፀረ ሰው ፈንጂ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱት ክልሎችም ትግራይ፣ አፋር እና ሶማሌ ሲሆኑ፣ በርካታ አደጋ የደረሰባቸውም ከብት በመጠበቅ ላይ የተሰማሩ ወይም በግብር እና የሚተዳደሩ ሰዎች ናቸው።
በአውሮፓውያኑ 2000 የአልጀርስ የሰላም ስምምነት እስኪፈረም ድረስ የተቀበሩ ፈንጂዎችን የማጽዳት ሥራ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ያልተጀመረ ሲሆን፣ የሰላም ሂደቱን ተከትሎ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ሌሎች ተቋማት አማካኝነት የተለያዩ የማምከንና የማጽዳት ሥራዎች ተጀምረዋል።
የፀረ ሰው ፈንጂ በከፍተኛ ሁኔታ ወደሚገኝባት ሌላኛዋ መካከለኛዋ አፍሪካዊት አገር አንጎላ እናምራ።

ለ27 ዓመታት የዘለቀው ደም አፋሳሹ የአንጎላ የእርስ በርስ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል።
ጦርነቱ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2002 ነበር የተቋጨው።
ጦርነቱ ከቆመ በኋላም ጥሎት ያለፈው አሻራ የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ ነው።
ከጦርነቱ በኋላ የተወለዱትም ባልመከኑ ፈንጂዎች እና በየቦታው በተቀበሩ ቦምቦች ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ታዳጊዎቹም የጦርነቱ ውርስ ገፈት ቀማሽ ሆነዋል።
በየዓመቱ መጋቢት 26 የሚከበረውን የፈንጂ ማምከን ግንዛቤ ዕለትን አስመልክቶ የወደፊቱን ትውልድ ሕይወት ብሩህ ለማድረግ በፈንጂ ማምከን ሥራ የተሰማሩ ሴቶችን ቢቢሲ አነጋግሯል።
***
ሄለና ካሶንጎ ስለ ሦስት ዓመት ሴት ልጇ ስታወራ ፊቷ ይበራል፤ ፈገግታዋም ያላትን ጥልቅ ፍቅር ያሳያል። ልጇ ምን ያህል እናቷ መስዋዕት እየከፈለች እንደሆነ እንዲሁም ሕይወቷን አደጋ ላይ የጣለ ሥራ እየሰራች እንደሆነ ለመረዳት ገና ህጻን ናት።
ቢሆንም ትንሿ ልጇ እናቷ ፈንጂ አምካኝ ወይም በአገሬው ቋንቋ (ሳፓዶራ) እንድትሆን ያደረጋትን ምክንያት ወደፊት እንደምትረዳ ሄለና ሙሉ እምነት አላት።
“ልጄ ወይም ሌሎች ልጆች ያልመከነ ፈንጂ ሰለባ እንዲሆኑ አልፈልግም” ስትል የ25 ዓመቷ ሄለና ለቢቢሲ ተናግራለች።
ጦርነቱ ቢያከትምም መግደሉን ቀጥሏል
ሦስት አስርት ዓመታት ያህል የዘለቀው የአንጎላው ጦርነት የራሱን ዳፋ ጥሏል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ያልመከኑ ፈንጂዎች እና ቦምቦች እዚህም እዚያም ተበታትነው ተቀብረው ይገኛሉ።
የአንጎላ መንግሥት በአውሮፓውያኑ 2014 ባካሄደው ብቸኛው ብሔራዊ ቆጠራ ወደ 88 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በተቀበሩ ፈንጂዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ፈንጂ መቅበርን ለመከላከል የሚሟገተው ዓለም አቀፉ ድርጅት ተጎጂዎችን አስመልክቶ የአንጎላ መንግሥት ያወጣው ቁጥር አናሳ እንደሆነ እና ክትትልም ስለማያደርጉ አሃዙ በጣም ከፍ ያለ ነው ብሏል።
በተቀበሩ ፈንጂዎች እና ቦምቦች አብዛኛውን ጊዜ የሚጠቁት ህጻናት ናቸው። በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ ሞክሲኮ በተሰኘችው ግዛት ባልመከነ ፈንጂ በደረሰ ፍንዳታ አንዲት የስድስት ዓመት ህጻን ልጅ ሕይወት የተቀጠፈ ሲሆን፣ ስድስት ህጻናት ቆስለዋል።
የአሪቱ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ህጻናቱ ሜዳ ውስጥ ባገኙት ቦምብ እየተጫወቱ ነበር። “ይህ በተደጋጋሚ የሚያጋጥም ጉዳይ ነው” ትላለች ሄለና።
“በአንጎላ ውስጥ በፈንጂ ቢያንስ አንድ የተጎዳ ሰው እናውቃለን። ለሕዝባችን እና ለአገራችን ጥቅም ስንል ይህንን አዙሪት ልናስቆመው ይገባል” በማለትም ምክሯን ለግሳለች።

የፎቶው ባለመብት, Mines Advisory Group
በሺዎች የሚቆጠሩ ‘ገዳይ የእግር ኳስ ሜዳዎች’
ሄለና ከአውሮፓውያኑ 1989 ጀምሮ የተቀበሩ ፈንጂዎችን በማምከን እና ፈንጂዎችን በማጽዳት የሚታወቀው ማይንስ አድቫይዘሪ ግሩፕ (ማግ) ለተባለው መንግሥታዊ ላልሆነ ድርጅት ትሰራለች።
ተቋሙ አንጎላን ጨምሮ በ70 አገራት ውስጥ ይሰራል። በአንጎላ 7 ሺህ 300 ሄክታር ወይም 10 ሺህ የእግር ኳስ ሜዳ የሚሆን ስፋት ያለው መሬት ከፈንጂ መጸዳት እንዳለበትም ተቋሙ አስታውቋል።
ፈንጂዎቹ አደጋን ከማስከተል ባለፈ በተቀበሩባቸው አካባቢዎች ግብርና እና ግንባታን ጨምሮ መሠረታዊ እንቅስቃሴዎችን ይገድባሉ።
ይህም ሁኔታ ምጣኔ ሃብቱን እየጎዳው ይገኛል። ከግማሽ በላይ የሚሆኑት አንጎላውያን በቀን 2 ዶላር ያነሰ ገቢ በማግኘት የዓለም ባንክ ካስቀመጠው ከዓለም አቀፍ የድህነት ወለል በታች ይኖራሉ።
ከጦርነቱ በኋላ የአገሪቱ የነዳጅ ኢንዱስትሪ በከፍተኛ ሁኔታ እየተመነደገ ቢገኝም በርካቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ኑሯቸውን ለመግፋት ተገደዋል።
“የተቀበሩ ፈንጂዎች የሰው ሕይወትን ይቀጥፋሉ፣ አካልን ያጎድላሉ። ከዚህም በላይ ልማትን ያደናቅፋሉ እንዲሁም በጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደየቀያቸው እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆነዋል” በማለት የማግ ሥራ አስፈጻሚ ዳረን ኮርማክ ይናገራሉ።
“ማኅበረሰቡን በፍርሃት ብቻ ሳይሆን በድህነት አጣብቂኝ ውስጥ ይከቱታል” ሲሉም ያክላሉ።
ለዚህም ነው እንደ ሄለና ያሉ በርካታ ሴቶች ፈንጂ አምካኝ (ሳፓዶራ) ለመሆን ምክንያት የሆናቸው። በዚህ ሥራ ከ440 እስከ 660 ዶላር ደመወዝ ያገኛሉ። ከፈንጂ መጸዳት ያለበትም መሬት መጠነ ሰፊ በመሆኑ ሥራው ማቆሚያ የለውም።
በአንጎላ በፈንጂ ማምከን የተሰማሩት ማግ እና ሃሎ ትረስት ተቋማት 40 በመቶ የሚጠጉት ፈንጂ አምካኞቹ ሴቶች ናቸው። ሃሎ ትረስት የተሰኘው ተቋም ከሁለት ዓመት በፊት 100ኛውን ፈንጂ አምካኝ (ሳፓዶራ) መመልመሉንም አክብሯል።
“ፈንጂ የማምከን ሥራ በተለምዶ ወንዶች የሚሰማሩበት ዘርፍ ነበር። ለዚህም ምክንያት የነበረው የፈንጂ እና ተቀጣጣዮች አወጋገድ ሙያ ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ብዙዎቹም በወታደርነት ያለፉ ናቸው” ሲሉ ኮርማክ ያስረዳሉ።
“በዘርፉ ውስጥ ያለውን የሥርዓተ ጾታ አለመመጣጠንን ለመቅረፍ ስትራቴጂ በመንገድ በሁሉም ፕሮግራሞቻችን ሴት ፈንጂ አምካኞች ለመልመል እና ለማሠልጠን በንቃት ሰርተናል” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Mines Advisory Group
“ፍርሃት ዘላቂ ጓደኛ ነው”
ሄለና እና ባልደረቦቿ በሳምንት ስድስት ቀናት፣ በቀን በአማካኝ ስድስት ሰዓታትን በመፍጀት ፈንጂዎችን ሲያመክኑ ይውላሉ።
እነ ሄለና ብዙ ጊዜ ሴቶች በማያዘወትሩት ሥራ ላይ በመሰማራት የማኅበረሰቡን የቆዩ የሥርዓተ ጾታ አመለካከቶችን እየተገዳደሩ ይገኛሉ።
“እናቴ እና ወንድሞቼ 'ሳፓዶራ' እንድሆን ፈጽሞ አልፈለጉም። ሴቶች ፍጹም የሚሰማራበት ሥራ ነው ብለው አያስቡም” ስትልም የማግ ፈንጂ አምካኝ የሆነችው ሌላኛዋ የ27 ዓመቷ ጆአኩዊና ባርቦሳ ትናገራለች።
“ለአምስት ዓመታት ያህል ሥራ አጥ ነበርኩ። በሕይወቴ ትርጉም ያለው ሥራም ለመሥራት እፈልግ ነበር። እንደ ዕድል ሆኖ ይህንን ሥራ መሞከሬንም ሆነ የሚያቆመኝ የትዳር አጋር የለኝም። ለወደፊቱ በዚህ አደገኛ ሥራ መሰማራቴን የሚቀበል ወንድ እፈልጋለሁ” ስትልም በሳቅ በታጀበ ሁኔታ ተናግራለች።
ጽናታቸው፣ ድፍረታቸው ጥያቄ ውስጥ ባይገባም ሳፖዶራዎች ከፍርሃት ነጻ አይደሉም። ለአምስት ዓመታት ያህል በፈንጂ አምካኝነት የተሰማራችው የ35 ዓመቷ ንጎይ ግራካ ሙሉንዳ የሥራው አደገኝነት ሁሌም እንደሚያቃጭልባት ትናገራለች።
“ትንሽ ዘና የምለው መሳሪያዎቼን ካስቀመጥኩ በኋላ ብቻ ነው። ፍርሃት ዘላቂ የሆነ ጓደኛ ቢሆንም ስህተት ላለመፈጸምም በትኩረት እንድንሠራ የሚያደርገን ጉዳይ ነው” ትላለች ንጎይ።
“በዚህ ሥራ የመጀመሪያዋ ስህተት የሕይወትህ መጨረሻ ልትሆን ትችላለች” በማለትም የሥራውን አደገኛነት ታስረዳለች።
አደጋዎች ብዙ ጊዜ ባያጋጥሙም አንዳንዴ ማጋጠማቸው አልቀረም። ከማግ በተገኘው መረጃ መሠረት ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ ሁለት ጉዳቶች ቢያጋጥሙም ሞት ግን አልተከሰተም።
አንጎላ ያሏትን ፈንጂዎች ለማጽዳት ገና በርካታ ሥራዎች ይቀሯታል። አገሪቱ ከአውሮፓውያኑ 1997 ጀምሮ የፀረ ፈንጂ ስምምነት አባል ሆናለች።
በዚህ ስምምነት መሠረት የአንጎላ መንግሥት ያለውን ፈንጂ አጽድቶ ማጠናቀቅ የነበረበት በአውሮፓውያኑ 2013 ቢሆንም፣ ይህ የጊዜ ገደብ ተራዝሞ በ2028 ይጠናቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ለዚህ መዘግየት ምክንያት ከሆኑት መካከል አንዱ የተቀበሩ ፈንጂዎችን ለማምከን የሚሰሩ ሥራዎች ገንዘብ ምንጭ የሆነው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ማነሱ እንደሆነ ነው ማግ የሚናገረው።
ችግሩ ዓለም አቀፋዊ ሲሆን፣ መጠነ ሰፊም ነው። በአውሮፓውያኑ 2021 ቢያንስ 5 ሺህ 544 የዓለማችን ዜጎች ባልመከኑ ፈንጂዎች መገደላቸውን ወይም መቁሰላቸውን አንድ ፀረ ሰው ፈንጂ ዓለም አቀፍ ተቋም ገልጿል። አብዛኛዎቹ ሰለባዎች ሲቪሎች ሲሆኑ፣ ከእነዚህም ግማሾቹ ደግሞ ህጻናት ናቸው።
ሳፓዶራዎች በበኩላቸው በአገራቸው ውስጥ ያለውን ፈንጂ አምክነው ወደ ሌሎች አገራት የመሰማራት ህልምንም ሰንቀዋል።
“ሌሎች አገራት የተቀበሩ ፈንጂዎቻቸውን እንዲያመክኑ እና በርካቶችን ከሞት ወይም ከአካል መጉደል መታደግ እፈልጋለሁ” ትላለች ሄለና።
“ይህንን ስሜት በትክክል ሊረዱት የሚችሉት በአደጋ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ብቻ ናቸው” ብላለች።












