ሰሜን ኮሪያ እስካሁን ያልታየ አዲስ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል መሞከሯን አስታወቀች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰሜን ኮሪያ እስካሁን ከሞከረቻቸው አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳኤሎች ሁሉ “በጣም ኃያል” ያለችውን አዲስ ሚሳኤል መሞከሯን አስታወቀች።
የአገሪቱ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ሐሙስ ዕለት የተደረገውን የሚሳኤል ሙከራ “ተዓምራዊ ስኬት” ሲሉ አሞካሽተውታል።
ይህ ሚሳኤል አረሩን ለማስወንጨፍ ጠጣር ነዳጅ መጠቀሙ ከሌሎቹ የተለየ ያደርገዋል። ሚሳኤሉ ፈሳሽ ነዳጅ ከሚጠቀሙት በፈጠነ ሁኔታ የመተኮስ አቅም ያለው ሲሆን፣ በፀረ ሚሳኤል ለመከላከልም አዳጋች ነው ተብሏል።
ነገር ግን የሰሜን ኮሪያ ጎረቤቷ ደቡብ ኮሪያ እንደምትለው ሰሜን ኮሪያ ይህንን አዲስ አይነት አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ሠርታ ጥቅም ላይ ለማዋል ገና ረጅም ጊዜ ያስፈልጋትል ብላለች።
ሰሜን ኮሪያ በጠጣር ነዳጅ የሚተኮሱ የአጭር ርቀት ሚሳኤሎችን ለዓመታት ስትሞክር ከቆየች በኋላ ነው፣ ይህንን የረጅም ርቀት ሚሳኤል ለመጀመሪያ ጊዜ የሞከረችው።
ባለሙያዎች ይህ የሚሳኤል ሙከራ በሰሜን ኮሪያ የመሳሪያ ግንባታ መረሃ ግብር ውስጥ ታላቅ እመርታ መሆኑን በመግለጽ፣ ሚሳኤሉ በድንገት ያለምንም ማስጠንቀቂያ አሜሪካንን ለመምታት ያስችላታል ብለዋል።
የደቡብ ኮሪያ መከላከያ ሚኒስቴር ግን የሚሳኤል ቴክኖሎጂው አዲስ አለመሆኑን በመግለጽ፣ የሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ሙሉ ለሙሉ ያልተጠናቀቀ በሂደት ላይ ያለ ነው ብሏል።
በሙከራው ላይ ከሴት ልጃቸው፣ ከባለቤታቸው እና ከእህታቸው ጋር የተገኙት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን፣ የአዲሱ የሚሳኤል ሙከራ ጠላቶቻቸውን “በከፍተኛ ፍርሃት እና ጭንቀት ውስጥ ይከታል” ብለዋል።
ህዋሶንግ-18 የተባለው የሚሳኤል ሙከራ በሰሜናዊ ጃፓን ውስጥ ግራ መጋባትን በመፍጠር ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዲወጡ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ምክንያት ሆኗል።
በዚህም ሳቢያ በጃፓኗ ሆካይዶ ደሴት የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ትምህርት ዘግይቶ የተጀመረ ሲሆን፣ አንዳንድ የባቡር አግልግሎቶችም እንዲቋረጡ ተደርጎ ነበር።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ሠራዊታቸው ጠላቶቻቸው አገራቸውን ከማጥቃት እንዲታቀቡ በሚያደርጉ ወታደራዊ ተግባራት ላይ እንዲያተኩር ካዘዙ ከቀናት በኋላ የተደረገውን ይህንን ሙከራ፣ የጃፓን፣ የደቡብ ኮሪያ እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት አውግዘውታል።
ተንታኞች እንደሚሉት ይህ የሰሜን ኮሪያ አዲስ እና ኃያል የሚሳኤል ሙከራ በድንገት የተከሰተ ሳይሆን ለዓመታት በአጭር ርቀት ሲደረግ የቆየው ሙከራ ውጤት ነው።
ሰሜን ኮሪያ ባለፉት ዓመታት ያሏትን የኑክሌር ጦር መሳሪያዎች ለማሳደግ እና እጅግ የረቀቁ የጦር መሳሪያዎችን ለመገንባት ስትሰራ ቆይታለች።
በተጨማሪም ጎረቤት ደቡብ ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን ወታደራዊ ልምምድ በአካባቢው ያለውን ውጥረት የሚያባብስ ነው በማለት ስትቃወም ነበር።
ይህ ሳምንት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሥልጣን ከያዙ 11ኛ ዓመት የሚከበርበት በመሆኑ፣ ጊዜውን አገሪቱ የደረሰችበትን ወታደራዊ ደረጃ ለማሳየት ልትጠቀምበት ትችላለች ተብሏል።
የአሁኑ የሚሳኤል ሙከራ የተደረገው በሰሜን ኮሪያ ውስጥ ከሚከበሩት ብሔራዊ በዓላት መካከል ትልቁ የሆነው የአገሪቱ መሥራች ከኪም ኤል ሱንግ ልደት ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ የተደረገ ነው።












