በቲክቶክ የሚሰራጩ ይዘቶች ቁጥጥር እና በኢትዮጵያ ሊፈጥሩ የሚችሉት ስጋት

ቲክቶክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ፌስቡክ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተጠቃሚ ያለው የማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር መድረክ ሲሆን፣ በሚቀርቡት ይዘቶች ላይ ተገቢውን ቁጥጥር አላደረገም በሚል በተደጋጋሚ ሲተች ቆይቷል።

የቀድሞው የፌስቡክ ሠራተኛ ፍራንሲስ ሐውገን ከአንድ ዓመት በፊት በአሜሪካ ኮንግረስ ፊት ቀርበው ድርጅቱ በኢትዮጵያ እና በምያንማር ግጭት ቀስቃሽ እና ሐሰተኛ መረጃዎችን ሳያስቆም ቀርቷል ሲሉ መመስከራቸው ይታወሳል።

አንዳንዶንቹ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ጉዳት ከደረሰ በኋላ ቢሆንም ባለሙያዎችን ቀጥረው የይዘት ቁጥጥር ጀምረዋል።

አሁን አሁን ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሰፊ ተወዳጅነት እያተረፈ የመጣው ቲክቶክ ነው።

ቲክቶክ አብዛኛው ሕዝብ ወጣት የሆነባቸው አንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ተወዳጅነቱ ይበልጥ እየጨመረ ነው። በአራቱም አቅጣጫ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር እየተመነደገ ነው።

አጫጭር ቪዲዮዎችን በማጋራት የሚታወቀው ቲክቶክ፣ አዝናኝ እና ቁምነገር አዘል መረጃዎችን በሙዚቃ ተዋዝቶ የሚቀርብበት መድረክ ነው።

ቲክቶክ ከዚህ ባለፈ ለብዙዎችም የገቢ ምንጭ ሆኗል። ይህም ለተወዳጅነቱ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ከሰሞኑ ግን ቲክቶክ የመገናኛ ብዙኃንን ርዕስ የያዘው ከተለያዩ መንግሥታት በሚደርስበት ጫና ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተለይም የተጠቃሚዎች መረጃ ጥበቃ እና የቻይና መንግሥት ከዚሁ መተግበሪያ ጠቃሚ መረጃዎችን ማግኘቱን በተመለከተ ከአሜሪካ እስከ እስከ ዩናይትድ ኪንግደም እየተብጠለጠለ ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ውስጥ ደግሞ ይዘቱ ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር ደካማ በመሆኑ የሚያደርሰው ጉዳት ቀላል የሚባል አይደለም የሚሉም በርካቶች ናቸው።

ቲክቶክ ይዘቱን የሚቆጣጠርበትን ፖሊሲ አውጥቶ መሥራት የጀመረው ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ላይ ነው።

በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚቀርቡ ይዘቶችን የሚቆጣጠሩ የቲክቶክ ባለሙያዎች ቁጥራቸው በቂ ባለመሆኑ የጥላቻ ንግግሮች እና የሕዝቡን ባህል የሚቃረኑ ቪዲዮዎች በስፋት እንደሚሰራጩ ባለሙያወች ይናገራሉ።

ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ አንድ የቲክቶክ ሠራተኛ [የኢትዮጵያ ቋንቋዎችን ይዘት የሚቆጣጠር ባለሙያ ነው] በቂ ባይሆንም ተቋሙ የይዘት ቁጥጥር ላይ መሥራት መጀመሩን ይናገራል።

ናይሮቢ ኬንያ ሥራ የጀመረው በወርሃ መጋቢት ሲሆን መጀመሪያ ወደ ሥራ ከመግባታቸው በፊት ለሁለት ሳምንታት ሥልጣና ተሰጥቷቸዋል።

ሥልጠናው ከጾታዊ ጥቃት እና ዝሙት ጋር ከተያያዙ ይዘቶች ጀምሮ አስከ እንስሳት መብቶች የሚደርሱ፣ እንዲሁም ከአመጽ ቀስቃሽ እና ጸያፍ የሚባሉ ተግባራትን እና አገላለጾችን የሚያሳዩ ቪድዎችን ማስወገድን ያካትታል።

በተለይ ደግሞ ጾታዊ ግንኙነትን የሚያሳዩና ለዝሙት የሚገፋፉ እንዲሁም ደግሞ ግድያን የሚያሳዩ፣ ደም ወይም ደግሞ መሰል ዘግናኝ (ግራፊክ) የሆኑ ይዘቶች ወደ ተመልካቾች ከመድረሳቸው በፊት እንዲወገዱ ይደረጋል።

በተጨማሪም ጥላቻን እና ዘረኝነትን የመሳሳሉ፤ ግጭትን እና አመጽን የሚያነሳሱ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን እንዲሁም መሰል ጉዳዮችን ማሰራጨትም በቲክቶክ ፖሊሲ የተከለከሉ ናቸው።

እንዲህ ዓይነት ነገሮችን የያዙ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከመሰራጨታቸው በፊት እንዲወገዱ የቲክቶክ ፖሊሲ ይደንግጋል። አንዴ ካመለጠ ደግሞ በተቻለ መጠን ወደ ብዙ ሰዎች ከመሰራጨቱ በፊት የማስወገድ እርምጃ እንዲወሰደባቸው ይደረጋል ብሏል።

“አንዳንድ ጊዜ ሪፖርት ከተረደገ በኋላ እንደርስበታለን። ብዙ ጊዜ ሊያመልጠን ይችላል። አንዳንዶቹ ብዙ የተወደዱ እና በርካታ አስተያያቶች የተሰጠባቸው ሆነው እናገኛቸዋለን። ስለዚህም ብዙ ሰው አይቷቸዋል ማለት ነው። አንዳንዱ ግን ለተጠቃሚው ከመድረሱ በፊት እንደርስበታልን” ሲል የቲክቶክ ባለሙያው ለቢቢሲ ገልጿል።

የቲክቶክ ይዘቶችን መቆጣጠር ይቻላል?

አቶ ቶሌራ ፍቅሩ ጋዜጠኛ እና የማኅበራዊ ሚዲያ ባለሙያ ናቸው። በፋክት ቼክ (የይዘቶችን እውነትነት ማጣራት) ላይም ይሠራሉ።

አቶ ቶሌራ በአሁኑ ወቅት ተጠቃሚው እየበዛ የመጣው እና የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩን በመቆጣጠር ላይ ያለው የቲክቶክ ቪዲዮዎች “የዓለም ስጋት ናቸው” በማለት ይናገራሉ።

ፌስቡክ ከኢትዮጵያ አንጻር ካየነው ይዘቶቹን መቆጣጠር የጀመረው ጉዳት ካደረሱ በኋላ ነው የሚሉት አቶ ቶሌራ፣ ቲክቶክ ግን ከዚህ መማር አልቻለም ይላሉ።

የቲክቶክ ይዘቶች በተለይም አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታ “በጣም አደገኞች ናቸው” የሚሉት አቶ ቶሌራ፣ ምክንያቱ ደግሞ ሰዎች ከማንበብ ማየትን እየመረጡ በመሆኑ ነው ይላሉ።

እነዚህ አጫጭር የቲክቶክ ቪዲዮዎች በጣም ብዙ ሰዎች ጋር በመድረስ የመታየት ዕድል ስላላቸው፣ አደገኛ ይዘቶቻቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ የዓለምን ዳርቻዎች ማዳረስ ይችላሉ።

“ቲክቶክ በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ላይ እያደረገ ያለው የይዘት ቁጥጥር በጣም ደካማ ነው። አጸያፊ ጥላቻ ንግግሮች፣ የዘር ጥላቻዎች፣ ግለሰብ እና ብሔር ላይ ያተኮሩ ቪዲዮዎች በብዛት ተሰርተው ይሰራጩበታል” ይላሉ አቶ ቶሌራ።

ቁጥጥሩ ደካማ እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ከሠው ሠራሽ አስተውሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚጠቅሱት ባለሙያው “ይህ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ሥርዓት በራሱ አደገኛ እና የጥላቻ ንግግሮችን ለይቶ አላስፈላጊ ይዘቶችን የሚያስወግድበት ነው።”

ነገር ግን ከዚህ ቴክኖሎጂ አንጻር ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ደግሞ በዚህ ደረጃ ዝግጁ ስላልሆኑ፣ ሠው ሠራሽ አስተውሎቱ እነዚህን አላስፈላጊ ይዘቶችን ለይቶ ማስቀረት አይችልም እንደማይችል አቶ ቶሌራ ይጠቅሳሉ።

ሌላው ችግር ደግሞ በይዘት ቁጥጥር ላይ ቲክቶክ ከሚያሠራቸው ባለሙያዎች ጋር ተያያዘ ነው ይላሉ። ለዚህም የባለሙያዎች ቁጥር ማነስ እና የብቃት ጉዳይ በይዘቶች ጥራት ላይ የእራሱ ተጽእኖ አለው ይላሉ።

አቶ ቶሌራ “ይዘት የመቆጣጠር ሥራ በግልጽነት ኃላፊነት ባለው መልኩ እና በሃቀኝነት መሠራት አለበት። አሁን ግን ባለሙያዎቹ በፖለቲካ ተጽዕኖ ስር ወድቀው ይሁን ወይም በሌላ በትክክል ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ምክንያቱም በይዘት ቁጥጥር ላይ የግልጽነት ጉድለት ስለሚታይ ነው” ይላሉ።

ቢቢሲ ያነጋገረው የቲክቶክ ይዘት ተቆጣጣሪ ባለሙያ ደግሞ፣ ሙሉ ለሙሉ ይዘቶችን መቆጣጠር እንደማይችል ተናግሮ ከዚህ በላይ ለማሻሻል ግን በቂ የሰው ኃይል ሊኖር ይገባል የሚል እምነት አለው።

በየዕለቱ የሚያዩት ይዘቶች የሚያስደነግጡ እና የሚረብሹ እንዲሁም እንግዳ ነገሮች ስለሚሆኑ፣ ሥራው በይዘት ተቆታጣሪዎቹ ላይም ተጽዕኖ ያሳርፋል። ሆኖም የሥነልቦና ባለሙያ (ሳይካትሪስት) ተቀጥሮላቸው በፈለጉት ሰዓት ምክር እና እርዳታ የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱን አስረድቷል።

እንዲህ አይነት ይዘቶች ደግሞ እንዲሁ ያለቁጥጥር የሚለቀቁ ወይም ሾልከው የሚያልፉ ከሆነ፣ በሺዎች ወይም በአስር ሺዎች በሚቆጠሩ ተጠቃሚዎች ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉት ውጤት ቀላል ሊሆን አይችልም።

ለዚህም ነው የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ይዘቶቻቸው በተጠቃሚው ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊት ቁጥጥር እና ማጣራት ሊደረግባቸው ይገባል የሚባለው።

ቲክቶክ ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች መካከል በአሁኑ ጊዜ የይዘት ቁጥጥር የሚያደርገው በአማርኛ እና በኦሮምኛ ቋንቋዎች ላይ ነው። ነገር ግን ትግርኛ የሚችሉ የይዘት ተቆጣጣሪዎች ስላሉ ትግርኛ ከአማርኛ ጋር ተጣምሮ እንደሚታይ ቢቢሲ ተገንዝቧል።

ቲክቶክ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

“የቲክቶክ ይዘቶች ከጦር መሣሪያ ያነሱ አይደሉም”

ሰሞኑን አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና አውስትራሊያን የመሳሰሉ ምዕራባውያን ቲከቶክን በመንግሥት ስልኮች ላይ መጠቀምን አግደዋል።

ምክንያያታቸው ደግሞ ብሔራዊ የደኅንት ስጋት በመፍጠራቸው መሆኑን አቶ ቶሌራ ተናግረው፣ በኢትዮጵያ ግን “በሕይወት ከመኖር እና ካለመኖር ጉዳይ ጋር ስለሚያያዝ ስጋቱ ከእነዚህ አገራትም በላይ ነው” ይላሉ።

“በቲክቶክ ላይ የሚቀርቡ ይዘቶች በሕዝቦች መካከል ጥላቻ እና ግጭትን ከማስፋፋት እና ከማበረታታት፣ እንዲሁም በወጣቶች ባህሪ ላይ ከሚያስከትለው አሉታዊ ተጽእኖ አንጻር አደጋን እየደቀነ ነው።”

ኢትዮጵያ በቅርቡ የጥላቻ ንግገሮችን ለማስቀረት በሚል አዋጅ ማውጣቷ ይታወሳል። ነገር ግን አተገባበሩ ላይ ጉድለቶች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ቶሌራ፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘቶችን ለመቆጣጠር የቴክኖሎጂ እጥረቶች እንዳሉ ይናገራሉ።

ስለዚህም መንግሥት ቲክቶክን የመሳሰሉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች የደቀኑትን አደጋን ለመከላከል በቴክሎጂ፣ በፋይናንስ እና በሎጂስቲክ የዜጎቹን ደኅንንት ለመጠበቅ ሰፊ ሥራ መስራት እንደሚጠበቅበትም ያስረዳሉ።

ሌላኛው እንቅፋት ብለው ያነሱት ሃሳብን በመነጻነት ከመግለጽ ጋር የሚያያዝ መሆኑን ነው። ከማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር መብት እና ግዴታዎች አብረው ይመጣሉ፤ ከትስስር መድረኮቹ በተጨማሪ ተጠቃሚውም ይህንን መገንዘብ አለበት ብለዋል።

ስለዚህ መንግሥት ሐሳብን በነጻነት የመግለጽን መብት በማይጋፋ ሁኔታ ጠንከር ያለ ፖሊሲ አውጥቶ በሕዝብ እና በአገር ደኅንነት ላይ አደጋ በሚደቅኑ ይዘቶች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት ይመክራሉ።

ቲክቶክ ይዘት ቁጥጥር ከኢትዮጵያ አንጻር

በኢትዮጵያ ያለው የተጠቃሚዎቹ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ የጨመረው ቲክቶክ፣ ለየት ባደረጉት አጫጭር የቪዲዮ ይዘቶቹ ምክንያት በተለይ በወጣቶች ዘንድ ተመራጭ እየሆነ ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎን ከቁጥር አዳጋች የሆኑ አሉታዊ መልዕክቶች በስፋት ይቀርባሉ። የድርጅቱ የይዘቶችተቆጣጣሪም “በርካታ ተገቢነት የሌላቸው ይዘቶች እየተሰራጩ እንደሆነ” ይነገራል።

“እውነት ለመናገር እነዚህን ይዘቶች ለመቆጣጠር አልተቻለም። ብዙ የሰው ኃይል ያስፈልጋል። በጣም አድካሚ ነው። አንድ ሰው ቢያንስ በቀን እስከ አምስት መቶ መስሎችን ይመለከታል” ይላል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የሚሰሩ የይዘት ተቆጣጣሪዎች ቁጥራቸው አስር የሚደርስ ሲሆን፣ ከይዘት ቁጥጥር አንጻር ትኩረት የተሰጠው የህጻናት እና የሴቶች ጉዳይ ነው ብሏል።

በአሁኑ ጊዜ ጥቃትን ከሚጋብዙ እና ጥላቻን ከሚያስፋፉ ይዘቶች አንጻር በኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎች የሚሰራጩ ይዘቶች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚያስፍልግ ያምናል።

ተጠቃሚዎች ቲክቶክ ላይ ይዘቶችን በሚያቀርቡባቸው የአገሪቱ ቋንቋዎች “በርከት ያሉ የይዘት ተቆጣጠሪዎች ማደራጀት ከተቻለ ለውጥ ሊመጣ ይችላል።”

ባይትዳንስ በተባለው የቻይና ድርጅት የሚተዳደረው ቲክቶክ በምዕራባውያኑ ዘንድ ለቻይና የመረጃ መሾለኪያ መስመር ሆኖ ያገለግላል የሚል ስጋትን አስከትሎባቸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ደግሞ ቲክቶክ ውጥረት በሞላበት በኢትዮጵያ ፖለቲካ እና የማኅበረሰቦች ግንኙነት ውስጥ የጥላቻ እና ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶች የሚተላለፉበት ተጨማሪ መድረክ እየሆነ ነው የሚል ስጋት አለባቸው።