ምዕራባውያን በዐይነ ቁራኛ እየተከታተሉት ያለው ቲክቶክ ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ ሾ ዢ ቺው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ፤ ቻይና ሠራሹን መተግበሪያ ቲክቶክ ልታግድ ነው የሚሉ ወሬዎች መስፋፋት ጀምረዋል።
አሁን ትኩረቱ የቲክቶክ ሥራ አስኪያጅ ወደሆነው ሲንጋፖራዊው ዋን ሥራ አስኪያጁ፤ ሾ ዢ ቺው ላይ ሆኗል።
ፊቱን አይቶ ማንበብ ይከብዳል የሚሉለት የ40 ዓመቱ የቲክቶክ አለቃ በዩናይትድ ስቴትስ ኢነርጂ እና ንግድ ኮሚቲ ፊት ቀርቦ ቃሉን ሰጥቷል።
ሥራ አስኪያጁ ዕለተ ሐሙስ በአሜሪካ ምክር ቤቱ ፊት ቀርቦ የመተግበሪያውን የመረጃ ደኅንነት እና ከቻይና መንግሥት ጋር ያለውን ቁርኝት በተመለከተ አስረድቷል።
ለአራት ሰዓት ተኩል በምክር ቤቱ ውስጥ በነበረው የጥያቄ እና መልስ ጊዜ ቺው ቲክቶክ የተመለከቱ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውለታል።
በተለይም የተጠቃሚዎች መረጃ ጥበቃ እና የቻይና መንግሥት ከዚሁ መተግበሪያ ጠቃሚ መረጃዎችን ማግኘቱን በተመለከተ በጥብቅ ተተይቋል።
ግለሰቡ ሥራውን እንዴት እንደሚያከናውን አሊያም በኩባንያው ውስጥ ያለው ሥልጣን ምን ያህል እንደሆነ ብዙም መረጃ የለም።
ከዚህ ቀደም የቲክቶክ ዋና የኦፕሬሽን ኃላፊ የሆነችው ቫኔሳ ፓፓስ ነበረች ጎልታ የምትታየው።
ቫኔሳ ባለፈው መስከረም በአሜሪካ ኮንግረስ ፊት ቀርባ የአሜሪካ መረጃ ወደ ቻይና እየፈለሰ ነው በሚል በጥያቄ ስትዋከብ ተስተውላለች።
ኒው ዮርክ ታይምስ የተሰኘው ጋዜጣ የቀድሞ ቲክቶክ እና የባይትዳንስ (የቲክቶክ እናት ኩባንያ) ሥራ አስኪያጆችን ዋቢ አድርጎ፤ ቺው ብዙም ሥልጣን እንደሌለው ዘግቧል።
ጋዜጣው እንደሚለው ከቺው ይልቅ የባይትዳንስ መሥራች የሆነው ዣንግ ይሚንግ የቲክቶክ ፈላጭ ቆራጭ እንደሆነ ፅፏል።
አሁን ቲክቶክ ቺውን የኩባንያው መለዮ አድርጎታል። ቲክቶክ ደግሞ ከቻይና መንግሥት ጋር ይሠራል በሚል ወቀሳ በዓለም መንግሥታት ቅሬታ እየቀረበበት ነው።
ሲንጋፖርት ተወልዶ ያደገው ቺው የቱጃሮች የቻይና ትምህርት ቤት ውስጥ ነው የተማረው። ማንዳሪን እና እንግሊዝኛ አቀላጥፎ ይናገራል።
ትልቅ ደረጃ በሚሰጠው በሲንጋፖር ጦር ሠራዊት የጦር መኮንን ሆኖም አገልግሏል።
ከለንደን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በኢኮኖሚክስ ድግሪ ጭኗል። ወደ ሃርቫርድ ቢዝነስ ትምህርት ቤት በማቅናት ደግሞ ማስተርስ ድግሪውን ይዟል።
ቺው፤ ፌስቡክ ገና ታዳጊ ድርጅት እያለ ተለማማጅ (ኢንተርን) ሆኖ ሠርቷል።
ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት ቺው ዲኤስቲ ለተባለ የኢንቨስተመንት ኩባንያ ለአምስት ዓመት ያገለገለ ሲሆን፣ ይህ ኩባንያ የባይትዳንስ የመጀመሪያው ኢንቨስተር ነው።
አልፎም ጎልድማን ሳክስ ለተሰኘው ግዙፉ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ድርጅት ለሁለት ዓመት ያህል ሠርቷል።
ከዚህ በኋላ ነው ወደ ቻይና በማቅናት ዢያዎሚ የተሰኘው የስማርስት ስልክ ኩባንያ ዋን የፋይናንስ ሥራ አስኪያጅ ከመሆን ባለፈ፣ የዓለም አቀፍ ንግድ ፕሬዝዳንት በመሆን ለድርጅቱ ዕድገት ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
መጋቢት 2021 (እአአ) ወደ ባይትዳንስ በማቅናት የድርጅቱ የመጀመሪያው ዋና የፋይናንስ ሥራ አስኪያጅ በመሆን ተቀጠረ።
ከሁለት ወራት በኋላ የቲክቶክ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ኬቪን ሜየርስን ተክቶ ተሾመ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትልቁ ፈተና
ቺው በቲክቶክ ዋና ሥራ አስኪያጅነቱ ትልቁን ፈተና ሊጋፈጥ ተዘጋጅቷል። የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች መተግበሪያውን ከአሜሪካ ገበያ ሊያግዱት ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።
በቻይና መንግሥት የሚተዳደረው ግሎባል ታይምስ ባለፈው ማክሰኞ ባተመው የግል አስተያየት አምድ ላይ ቲክቶክ እንዲዘጋ እየገፋ ያለው “መርዛማው የአሜሪካ ፖለቲካ ምኅዳር ነው” ብሎ መተግበሪያውን መዝጋት “ነፃ ሐሳብን መግታት ነው” ሲል ፅፏል።
“በአሜሪካ ባለሥልጣናት እና በፖለቲከኞች ዐይን ቲክቶክ ቻይና ሠራሽ መሆኑ ‘ኃጥያት’ ነው” ይላል በአምዱ ላይ ሰፈው ጽሁፍ።
ከብዙ አቅጣጫ ጫና እየበረታበት ያለው ቲክቶክ ሥራ አስኪያጅ ቺው፤ ከቅርብ ወራት ወዲህ አዎንታዊ ምስል ይዞ ብቅ ብሏል።
ሥራ አስኪያጁ ምንም እንኳ ድርጅቱን የተቀላቀለው መጋቢት 2021 ቢሆንም፣ የቲክቶክ ገፅ ባለፈው ወር ከፍቶ የግል ሕይወቱን የሚያሳዩ ቅንጭብጫቢ ምስሎችን መልቀቅ ጀምሯል።
18 ሺህ ገደማ ተከታዮች ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ የአሜሪካ ‘ፉትቦል’ እና ቅርጫት ኳስ ጨዋታዎችን ሲታደም ተስተውሏል።
አልፎም እንደ ቢል መሪ ያሉ ታዋቂ ተዋንያንን አግኝቶ ሲጨብጥ እና ከዘፋኟ ሲያራ ጋር ለመደነስ ሲጥር ታይቷል።
በቅርቡ ባደረገው ቃለ-መጠይቅ ጎልፍ መጫወት እንደሚወድ እና የኮመዲያን ኬቪን ሃርት አድናቂ እንደሆነ ይፋ አድርጓል።
ልክ እንደሱ የአንድ ኢንቨስትመንት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆነችው ባለቤቱ እና ቺው ሁለት ልጆች አሏቸው።
ባል እና ሚስት ልጆቻቸው ‘ገና ሕፃናት ስለሆኑ’ ቲክቶክ እንዲጠቀሙ አንፈቅድላቸውም ይላሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እየቀረበ ቲክቶክ የአሜሪካን ፍላጎት እንደማይነካ ሲናገር ተደምጧል።
አልፎም ባለፈው ሰኞ በቲክቶክ ገፁ በለቀቀው ምስል ቲክቶክ ተጠቃሚ አሜሪካዊያንን “ለአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ምን ማለት ትፈልጋላችሁ” ሲል ጠይቋል።
ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ‘ላይክ’ ባደረጉት ምስል ላይ “ይህ ለሁላችንም ወሳኝ ጊዜ ነው። ከ150 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቲክቶክን ላያገኙት ይችላሉ” ብሏል።












