አሜሪካ በቲክቶክ ላይ የወሰደችውን እርምጃ ቻይና ተቃወመች

ቲክቶክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ የፈደራል መንግሥቱ ሠራተኞች ለሥራ በተሰጣቸው ስልኮች ላይ የጫኗቸውን የቲክቶክ መተግበሪያዎችን እንዲያስወግዱ ማዘዟን የቻይና መንግሥት ተቃወመ።

ቻይና፣ አሜሪካ የተንቀሳቃሽ ምስል ማጋሪያ መድረክ የሆነውን ቲክቶክን በተመለከተ ከተገቢው በላይ የሆነ እርምጃ ወስዳለች በማለት ነው ተቃውሞዋን የገለጸችው።

ሰኞ ዕለት የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው ትዕዛዝ መሠረት ተቋማቶቹ በ30 ቀናት ውስጥ የመንግሥት በሆኑ መገልገያዎች ላይ ያሉ የቲክቶክ መተግበሪያዎችን እንዲያስወግዱ አዟል።

ባለፉት ቀናት የአውሮፓ ኅብረት እና ካናዳ የቻይናውያን ንብረት በሆነው መተግበሪያ ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ወስደዋል።

የአሜሪካን ውሳኔ ተከትሎ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በሰጡት ምላሽ፣ አሜሪካ የመንግሥት ሥልጣንን የውጭ ኩባንያዎችን ለመጫን እየተጠቀች ነው ሲሉ ከሰዋል።

“ይህንን የተሳሳተ እርምጃ በጽኑ እንቃወማለን። የአሜሪካ መንግሥት የነጻ ውድድርን እና የገበያ መርኅን በማክበር ለውጭ ድርጅቶች ከመድልዎ ነጻ ሁኔታን እንዲፈቅድ እንጠይቃለን” ብለዋል ቃል አቀባይዋ ማኦ ኒንግ።

ምዕራባውያን ባለሥልጣናት በቻይናው ተቋም ባይትዳንስ ባለቤትነት ስር የሚተዳደረውን ታዋቂ የቪዲዮ ማጋሪያ የማኅበራዊ ሚዲያ መተግበሪያ የሆነውን ቲክቶክ በተመለከተ ስጋት ተፈጥሮባቸዋል።

ቲክቶክ የተጠቃሚዎቹን መረጃዎች በመሰብሰብ ለቻይና መንግሥት አሳልፎ ይሰጣል በሚል የሚከሰስ ሲሆን፣ የደኅንነት ተቋማትም መተግበሪያው በመንግሥታዊ መገልገያዎች ላይ በሚጫንበት ጊዜ ጥበቃ የሚፈልጉ መረጃዎችን ለማሹለክ በር ይከፍታል ብለው ይሰጋሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ነገር ግን ቲክቶክ የተጠቃሚዎቹን መረጃ አሳልፎ እንዲሰጥ የሚቀርብለትን ጥያቄን ፈጽሞ እንደማይቀበል እና ከሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተለየ ተግባራትን እንደማይፈጽም ገልጿል።

የአሜሪካ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ሻላንዳ ያንግ ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የመንግሥት በሆኑ ስልኮች ላይ ያሉ ምስጢራዊ መረጃዎችን ለመጠበቅ እንዲቻል የቲክቶክ መተግበሪያን እንዲያጠፉ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ይህም “በቲክቶክ ምክንያት ለአደጋ የተጋለጡ የመንግሥት መረጃዎችን ለመጠበቅ ወሳኝ የሆነ እርምጃ ነው” ተብሏል በተላለፈው መመሪያ ላይ።

የፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት - ዋይት ሐውስን፣ መከላከያን፣ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ አንደንድ የፌደራል መንግሥቱ ተቋማት ቀደም ብለው ከመገልገያዎቻቸው ላይ የቲክቶክ መተግበሪያዎችን እንዲወገዱ አድርገዋል።

የአሁኑ ትዕዛዝ የወጣው ባለፈው ታኅሣሥ ወር የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት ቲክቶክ በመንግሥት ስልኮች ላይ እንዳይጫን ዕገዳ በማስተላለፍ በ60 ቀናት ውስጥ መንግሥት መመሪያ እንዲያወጣ ማዘዙን ተከትሎ ነው።

በአሜሪካ ምክር ቤት ውስጥ ያሉ ሪፐብሊካኖች ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በአገሪቱ ውስጥ ቲክቶክን ለማገድ የሚያስችላቸውን ሥልጣን የሚሰጥ ተጨማሪ ሕግ በሚቀጥሉት ሳምንታት ያወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የካናዳ መንግሥትም ቲክቶክ “በግላዊ መረጃ እና ደኅንነት ላይ ተቀባይነት የሌለው አደጋ ስላለው” በሚል ከዛሬ ማክሰኞ ጀምሮ መተግበሪያው በመንግሥት መገልገያዎች ላይ ጥቅም ላይ እንዳይውል አግዷል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶም፣ ቲክቶክን በተመለከተ በቂ የደኅንነት ስጋት ስላለ ለውጥ ማስፈለጉን እና “ይህም የመጀመሪያው እና ብቸኛው እርምጃ ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ ኮሚሽን እና የአውሮፓ ምክር ቤት ሠራተኞቻቸው “ኮሚሽኑን ከመረጃ መረብ ጥቃት ለመጠበቅ” በሚል የቲክቶክ መተግበሪያን ከስልኮቻቸው እና ከድርጅቱ መገልገያዎች ላይ እንዲያስወግዱ አዟል።