ምስጢራዊ መረጃ ለመለዋወጥ ተመራጩ መተግበሪያ የቱ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቴሌግራም የገነባውን ምስጢራዊ የመረጃ ማከማቻ ቁልፍ ሰብሮ ለሚገባ መረጃ ሰርሳሪ 300 ሺህ ዶላር ሽልማት እንደሚሰጥ ገልጾ ነበር።
ሰብሮ መግባት የቻለ መረጃ ሰርሳሪ ስላልተገኘ ቴሌግራም ጥያቄውን ሰርዟል።
ሆኖም ግን አሁንም ድረስ የደኅንነት ባለሙያዎች ቴሌግራም ላይ ከመረጃ አጠባበቅ ጋር የተያያዘ ክፍተት ካገኙ ከ500 እስከ 100 ሺህ ዶላር እንደሚከፍል ቃል ገብቷል።
ይህ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ደኅንነታቸው ምን ያህል አስተማማኝ እንደሆነ የሚፈትሹበት መንገድ ነው።
በየጊዜው መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች ሲሠሩ የግል መረጃችን እንደሚጠበቅ ቃል ይገቡልናል። መንግሥታትን ጨምሮ ተቋማት ወይም ሌላ ሦስተኛ ወገን መረጃችንን ማግኘት እንደማይችልም ይምላሉ።
ጥያቄው፣ ይሄ ምን ያህል እውነት ነው? የሚለው ነው። የምንለዋወጠውን የጽሑፍ፣ የድምጽ፣ የምሥል፣ የተንቀሳቃሽ ምሥል እና የሰነድ መረጃ መተግበሪያ ሠሪዎቹ ወይም ሌላ ወገን ማግኘትስ አይችልም?
በእነዚህ ጥያቄዎች መነሻነት መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች የደኅንነት መጠበቂያ በራቸውን ሲያጠብቁ ቆይተዋል። አሁንም ድረስ ሽንቁሮች አሉ ብለው የሚተቹ ባለሙያዎች ግን አሉ።
ከግል መረጃ አጠባበቅ ጋር በተያያዘ የተሻሉ የሚባሉት መተግበሪያዎች የትኞቹ ናቸው? በተለይ ምስጢራዊ መረጃ መለዋወጥ ስንፈልግ የትኛውን መተግበሪያ ብናዘወትር ይመረጣል? ስንል ላለፉት አሥር ዓመታት በሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) እንዲሁም ተያያዥ የቴክኖሎጂ ዘርፎች የሠራው የአይኮግ ላብስ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ጌትነት አሰፋን ጠይቀናል።
መረጃን በመልዕክት ላኪ እና ተቀባይ መካከል ብቻ የሚቆልፍ ሥርዓት (end-to-end encryption) የሚጠቀሙ መተግበሪያዎች መጠቀምን ይመክራል።
በኢትዮጵያ በርካታ ተጠቃሚ ያፈራው ቴሌግራም ነው። አምና ቴሌግራምን በመጠቀም ኢትዮጵያ ከዓለም 11ኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠችው።
ምክንያት ተደርገው ከሚጠቀሱት አንደኛው የኢንተርኔት ትስስር ደካማ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ቴሌግራምን ለመጫን የሚያስፈልገው 49 ሜጋባይትስ መሆኑ ተመራጭ አድርጎታል የሚለው ነው።
ከሌሎች መተግበሪያዎች ጋር ብናነጻጽረው ለዋትስአፕ 103 ሜጋባይትስ፤ ለሜሴንጀር ደግሞ 125 ሜጋባይትስ ያስፈልጋል።
ጌትነት በበኩሉ ቴሌግራም በኢትዮጵያ ያለውን ተመራጭነት ከሕዝባዊ ንቅናቄ መነሳትና ማኅበራዊ ሚዲያዎች መዘጋት ጋር ያስተሳስረዋል።
“. . . እንደ አብዛኛው የአፍሪካ አገራት በኢትዮጵያ የቴሌኮም መሠረተ ልማት የተገነባው በቻይና ተቋማቱ ሁዋዊ እና ዜድቲኢ ልገሳ ነው። የምንጠቀመው ሀርድዌር ኤሌክትሮኒክስ እና ሶፍትዌሮችም የነሱ ናቸው። ፖለቲካዊ ንቅናቄ ሲነሳና ማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘጋ እነ ሜሴንጀር፣ እና ቫይበር ሲቋረጡ ሰው ወደ ቴሌግራም ሄደ። ምክንያቱም የቻይና ሰርቨሮች ቴሌግራምን አያዩትም” ሲል ያብራራል።
በርካታ ተጠቃሚዎች ያሉት ቴሌግራም ምን ያህል ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው?
ቴሌግራም መረጃን በመልዕክት ላኪ እና ተቀባይ መካከል ብቻ የሚቆልፍ ሥርዓት ቢኖረውም ይህንን ለማግኘት ተጠቃሚዎች ወደ ምስጢራዊገጽ መግባት አለባቸው።
የተላከው መልዕክት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ እንዲጠፋ ማድረግም ይቻላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአንድ የቴሌግራም ቡድን ውስጥ መካተት የሚችሉ ሰዎች ቁጥር እስከ 100 ሺህ መሆኑ (ዋትስአፕ የሚያካትተው እስከ 256 ሰው ነው) እንዲሁም አንድ የቴሌግራም ገጽ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ሊኖሩት መቻሉ ቴሌግራምን ምቹ አማራጭ አድርጓል።
በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን እና ማስታወቂያ ገጾች ወደ ቴሌግራም እየተሻገሩ ያሉትም ለዚህ ነው።
በሌላ በኩል ‘ኢንድ ቱ ኢንድ ኢንክሪፕሽን’ ያልተደረገባቸውን መረጃዎችን ቴሌግራም ማግኘት ወይም ለሕግ አካል አሳልፎ መስጠት ቢያስፈልገው ይህን ያደርጋል ቢባልም ቴሌግራም ግን ይህ ፈጽሞ እንደማይሆን ይገልጻል።
ጌትነት ለመልዕክት ልውውጥ የሚመርጠው ዋትስአፕን ነው።
“ዋትስአፕ ኢንድ ቱ ኢንድ ኢንክሪፕሽን ስለሚጠቀም የጽሑፍ መልዕክት፣ ተንቀሳቃሽ ቪድዮ፣ ምሥል ለመላላክ አማራጭ ነው። የተሠራውም ኢንክሪፕሽን ለመፍቀድ ነው” ይላል።
ሌሎች መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎችም የራሳቸውን ‘ኢንድ ቱ ኢንድ ኢንክሪፕሽን’ አማራጭ ሲሰጡ፣ ተጠቃሚዎች ኢንክሪፕትድ የሆነ መልዕክት ይላክልኝ የሚለውን እንዲመርጡ ይመክራል።
ሆኖም ግን በኤሌክትሮኒክስ የሚዘዋወሩ መረጃዎችን ለመጥለፍ የሚውሉ መተግበሪያዎች (Malwares) ሰርገው እንዳይገቡ ጥንቃቄ ያሻል።
“ዋትስአፕ ስንጠቀም በስልካችን የተለያዩ ማልዌር ዳታዎች እያስገቡ የምናወራቸውን እና የተለዋወጥናቸውን መረጃዎች ማግኘት የሚችሉበት መንገድ አለ። ኢንድ ቱ ኢንድ ኢንክሪፕሽን ከመምረጥ በተጨማሪ በዳታቸው ማልዌር እንዳይኖር መጠንቀቅ አለባቸው” ይላል ባለሙያው።
ተጠቃሚዎች የማያውቁትን ድምጽ፣ ተንቀሳቃሽ ምሥል ወይም ሌላም መልዕክት ባለመክፈት የመረጃ ደኅንነታቸውን መጠበቅ ይችላሉ።
በመላው ዓለም በርካታ ተጠቃሚዎች ያለው ዋትስአፕ ከ ‘ኢንድ ቱ ኢንድ ኢንክሪፕሽን’ በተጨማሪ፣ በዋትስአፕ ቡድን ውስጥ የሚላኩ መልዕክቶችን ተደራሽነት ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት አለው።
በተጨማሪም ተጠቃሚዎቹ የሚላላኳቸውን መልዕክቶች በተወሰነ ጊዜ ውስጥ እንዲጠፋ ያስችላል።
ዋትስአፕ፣ ፌስቡክን በሚያስተዳድረው ሜታ ሥር መሆኑ ብዙዎች ጥያቄ እንዲያነሱበት ቢያደርገውም በየጊዜው የግል መረጃ ደኅንነት አጠባበቅን እያሻሻለ እንደመጣ ይገልጻል።
ዋትስአፕ መረጃዎችን ክላውድ ላይ ሲያከማች መረጃው በመንግሥታት፣ በሦስተኛ ወገን ወይም በመረጃ መንታፊዎች ሊገኝ ይችላልየሚል ስጋት ነበር። ዋትስአፕ በበኩሉ መልዕክቶችን በሰርቨሩ እንደማያከማች እንዲሁም በኢንክሪፕሽን ለተቆለፉ መልዕክቶች መክፈቻ እንደሌለው ይናገራል።
የዋትስአፕ የቢዝነስ ገጽ ‘ኢንድ ቱ ኢንድ ኢንክሪፕሽን’ የለውም።
ዊከር ሚ፣ ቫይበር፣ ትሬማ፣ ደስት እና ሌሎችም መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎች በተለያዩ አገራት ጥቅምላይ ይውላሉ።
ጌትነት እንደሚለው ከሆነ፣ መተግበሪያዎች “አንዳች ለውጥ እስከሚደረግባቸው ድረስ ደኅንነታቸው የተጠበቀ ሆነው ይቆያሉ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን መረጃ በሆነ መንገድ መውጣቱ አይቀርም”።
መረጃ በዓለም የሚዘዋወርበት ፍጥነት እየጨመረ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ በተለይም ከኢንተርኔት ጋር የተገናኘ ነገር “ደኅንነቱ የተጠበቀ ነው” ብሎ መደምደም እንደማይቻል ያስረዳል።
ከኢንተርኔት ጋር የተገናኙ ማንኛውም ኤሌክትሮኒክሶች “ለጥቃት ክፍት ናቸው” ሲልም ያክላል።
በየጊዜው የመረጃ ምዝበራ የሚፈጸምበት ረቂቅነት እየተራቀቀ ስለሚሄድ መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያዎችን እስከወዲያኛው “አስተማማኝ” ለማለት ያስቸግራል።
“ደኅንነታቸው [ለተወሰነ ጊዜ] ቢጠበቅም እንደዛ ሆነው ይቆያሉ ማለት አይደለም። ደኅንነታችን የተጠበቀ ብለው የሚያስተዋውቁ ቢኖሩም ይህ የማስታወቂያ መንገድ ነው” ሲል ባለሙያው ያስረዳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከግል መረጃ ጥበቃ ጋር በተያያዘ ስማቸው በግንባር ቀደምነት ከሚጠራ መካከል ኤድዋርድ ስኖውደን ይገኝበታል።
የመንግሥታትን ያልተፈቀደ የግለሰቦች መረጃ ስለላ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ተቋማትን ስውር የግል መረጃ ማከማቸት በይፋ በመተቸት ይታወቃል።
ስኖውደን ምስክርነቱን ከሰጠላቸው መተግበሪያዎች አንዱ ሲግናል ነው።
ብዙ ቴክኖሎጂ ነክ ድረ ገጾችም እስካሁን ባለው ሲግናልን ደኅንነቱየተጠበቀ መልዕክት መለዋወጫ ብለው ያስቀምጣሉ።
ሲግናል የዘረጋው ሥርዓት በጣምጠንካራ ስለሆነ ዋትስአፕ እና ሜሴንጀርምይጠቀሙታል።
ሲግናል ለትርፍ የተቋቋመ ስላልሆነ “የግል መረጃ ለመውሰድ ምክንያት የለውም” ተብሎ በባለሙያዎች ይገለጻል።
ጌትነት እንደሚለው፣ በሂደት የብሎክቼን መተግበሪያዎች ሲኖሩ ሰዎች የግል መረጃቸውን ራሳቸው ኢንክሪፕት አድርገው የሚከፍቱት ቁልፍም ማስቀመጥ ይችላሉ።
“. . .ብዙዎችብሎክቼን ላይ ኢንቨስት እያደረጉ ሲሄዱ ዳታዎች ‘ፕራይቬት ኪ’ እና ‘ፐብሊክ ኪ’ ተብለው፣ ሰዎች ዳታቸውን ራሳቸው ኢንክሪፕት አድርገው የሚከፍቱት ቁልፍ ማስቀመጥ ይችላሉ። ሌላ ሰው መረጃውን ማግኘት በሚፈልግበት ጊዜ ለምንፈልገው ሰውብቻ ቁልፉን በመስጠት መረጃችንን እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል” ይላል።
በባለሙያው አስተያየት፣ ብሎክቼንበሂደት የደኅንነት ጥያቄን ይመልሳል።
ማንኛውም የቴክኖሎጂ ተቋም የኛን መረጃ በመሸጥ እስከሆነ ድረስ ገቢ የሚያገኘው “በምንምተአምር መረጃችንን ከመጠቀም ወደኋላ የሚሉበት ምክንያት የለም” ሲልም ያክላል።
እስከዚያው ድረስ፣ ምስጢራዊ መረጃ ለመለዋወጥ የተመረጡ መተግበሪያዎችን መጠቀም እንዲሁም እየተጠቀምናቸው ያሉ መተግበሪያዎች ከግል መረጃ አጠባበቅ ጋር በተያያዘ የሚሰጧቸውን አማራጮች መከተል ይመከራል።












