አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምን እያጥለቀለቁ ያሉት የቻይና መተግበሪያዎች

ሞባይል የሚጠቀሙ ወጣት ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ ውስጥ ስመ ገናና ለመሆን የበቃው ቲክቶክ ከሰሞኑ ዋነኛ መነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል። ከሚያቀርባቸው ይዘት ይልቅ ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጋር ግንኙነት አለው በሚል ነው መወዛገቢያ የሆነው።

የቲክቶክ ኃለፊ ሾው ዚ ቺው ኮንግረስ ፊት ቀርቦ በአሜሪካ ፖለቲከኞች ጥያቄዎች ቀርቦለታል። እናት ኩባንያው ባይትዳንስ ከመተግበሪያው የሚሰበስበውን መረጃ ምን ያህል ያጋራል? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተውበታል።

ከቲክቶክ በተጨማሪ በቻይና ባለቤትነት ስር ያሉ በርካታ መተግበሪያዎች የምዕራባውያንን ገበያዎች በማጥለቅለቅ ላይ ይገኛሉ።

አፕቶፒያ የተባለው የመረጃ ተቋም እንደገመተው ከሆነ በዩናይትድ ስቴትስ በነጻ ከሚገለገሉባቸው 10 ምርጥ የሞባይል መተግበሪያዎች ውስጥ ሦስቱ በቻይና ኩባንያዎች የተያዙ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ በዩናይትድ ኪንግደም በከፍተኛ ቁጥር ስልክ ላይ የተጫኑ ናቸው።

ለመሆኑ እነዚህ መተግበሪያዎች ምንድን ናቸው? የቻይና መተግሪያዎችን በጣም ስኬታማ የሚያደርጋቸው ምንድነው?

ካፕከት

ካፕከት የቪዲዮ ኤዲትንግ መተግበሪያ ነው። ብዙውን ጊዜም ቲክቶከሮች ቪዲዮዎቻቸውን ኤዲት የሚያደርጉበት ነው። በየካቲት ወር ብቻ 13 ሚሊዮን ጊዜ ስልኮች ላይ መጫኑን ሴንሰር ታወር አስታውቋል።

የቪዲዮ ኤዲቲንግ መተግበሪያው ለሞባይል ኤዲቲንግ የተመቻቸ ነው። ታዋቂ ዘፈኖችን፣ ቪዲዮ ማሳመሪያዎችን እና ሌሎች የኤዲቲንግ ሥራዎችን በማከናወን ቪዲዮዎች በስፋት እንዲታዩ ያግዛል።

ቲክቶክን የሚያስተዳድረው ሆነው ባይትዳንስ የካፕከትም ባለቤት ነው።

ሞባይል የምትመለከት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሼይን

ሼይን እአአ በ2012 የተመሠረተ ዓለም አቀፍ የፋሽን ብራንድ ነው። አሁን ወደ 15 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሃብት እንዳለው ፎርብስ ዘግቧል።

የተመሠረተው በቻይናዊው ቢሊየነር ክሪስ ሹ ሲሆን መቀመጫውንም በሲንጋፖር አድርጓል።

በቲክቶክ እና በኢንስታግራም ላይ በርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ይጽፉለታል። የአዲሱን ትውልድ ዒላማ ያደረገ ነው።

መተግበሪያው በየዕለቱ ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ምርቶችን በማኅበራዊ ሚዲያዎች ያሰራጫል።

ቲሙ

ይህ የግዢ መተግበሪያ በአሜሪካ ከተዋወቀ አንድ ዓመት እንኳን በቅጡ አልደፈነም። ነገር ግን በፍጥነት ስመ ገናናዎቹን አማዞንን እና ዋልማርትን በልጧል።

የበይነ መረብ መነገጃ መተግበሪያው ከአልባሳት እስከ ኤሌክትሮኒክስ ያሉ ነገሮችን በሙሉ ይሸጣል። ገዢዎች መደብሮችን አልፈው በቀጥታ ከቻይና አምራቾች እንዲሸምቱ ያስችላቸዋል።

በዘንድሮው ሱፐር ቦውል ላይ ማስታወቂያ ከወጣ በኋላ ዋጋው በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ በርካታ አሜሪካውያን “ቲሙ ሕጋዊ ነው ወይ” ብለው በይነ መረብ ላይ ሲያስሱ ነበር።

የኩባንያው ዋና መሥሪያ ቤት ቦስተን ነው። መተግበሪያው በቻይና ባለቤትነት የተያዘው የፒዲዲ ሆልዲንግስ ቅርንጫፍ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሜሪካ ውስጥ የቻይና መተግበሪያዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ካደረጓቸው ምክንያቶች አንዱ የአሜሪካ መተግበሪያዎች በተከለከሉበት በቻይና ገበያ ባለው ከባድ ውድድር መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

“ከቻይና የሚመጡ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በአገራቸው ውስጥ ጠንካራ የውድድር ጊዜ አሳልፈው ስለሚመጡ የተሻሉ ሆነዋል” ሲል በቻይና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረቱን ያደረገው ጋዜጠኛ እና ተመራማሪው ዜዪ ያንግ አስታውቋል።

እነዚህ የቻይና ኩባንያዎች የተጠቃሚዎችን ፍላጎት ለማሟላት በከፍተኛ ደረጃ የተዘጋጁ ናቸው። እንደ ቲክቶክ እና መልዕክት መለዋወጫ መተግበሪያው ዊቻት ያሉት በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው።

በቻይና ባለቤትነት የተያዘ እና በዓለም አቀፍ ገበያ ትልቅ ስኬትን ያገኘው የመጀመሪያ መተግበሪያ ቲክቶክ ነው።

የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች እና የደኅንነት ባለሙያዎች ደግሞ በቻይና ባለቤትነት የተያዙ መተግበሪያዎች በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ለግላዊ መረጃ ጥሰት እና ለሳንሱር ሊጋለጡ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃሉ።

ይኸው ስጋት ነው ከመንግጅት ሠራተኞች ስልክ ቲክቶክ እንዲታደግ የአውሮፓ ኮሚሽን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ካናዳ ቲክ ቶክን ቀጭን ትዕዛዝ እንዲያስተላልፉ ያስገደዳቸው።

“አሜሪካ እና ሌሎች ዲሞክራሲያዊ አገራት የመናገር ነጻነትን እና ዓለም አቀፍ የመረጃ ነጻነትን ሳይጋፉ እንደ ቲክቶክ ያሉ መተግበሪያዎችን የሚይዙበት መንገድ ትልቅ መዘዝ አለው" ሲሉ ፖል ሻር የተባሉ የፎር ፓወር ኢን ዘ ኤጅ ኦፍ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፀሐፊ ተናግረዋል።

መቀመጫቸውን በአሜሪካ ያደረጉ እንደ አፕል ያሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች መንግሥት የተጠቃሚዎቻቸውን መረጃ እንዳያገኝ ለረዥም ጊዜ በፍርድ ቤት ተከራክረዋል። በቻይና ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ዕድሎች የሉም ሲሉ ሻር አስታውቀዋል።

“የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ (የቻይና ንብረት የሆነ ኩባንያው) እንዲሠሩ የሚያዛቸውን ያደርጋሉ። ሌላ ምንም አማራጭ የላቸውም” ብለዋል።

የቲክቶኩ ኃላፊ ሹ ዚ ቺው አሜሪካውያንን ለመጠበቅ “ፋየርዎል (መረጃ መከላከያ)” እንዳለ በማስረዳት ሕግ ባለሙያዎች በደኅንነት ዙሪያ ያላቸውን ስጋት ለመቅረፍ ሞክሯል።

ቲክቶክ ለቢቢሲ በላከው መግለጫ የአሜሪካ የተጠቃሚዎች መረጃ የውጭ መንግሥታት በማይደርሱበት ቦታ እንዳለ አስታውቋል። ቢቢሲ አስተያየት እንዲሰጡት ሌሎች መተግበሪያዎችንም አነጋግሯል።

ሻር እንዳሉት ከሆነ የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች የግላዊነት ሕጎችን እስካላስተላለፉ ድረስ በየትኛውም አገር ስር ያለ መተግበሪያ ለመረጃ ጥሰት ተጋላጭ ሊሆን ይችላል።

“ማንኛውም ቻይና የነካቸው ነገር መጥፎ ነው የሚል አስደንጋጭ አደጋ አለ” ብለዋል።

“ሰዎች በሁሉም መተግበሪያዎች ዙሪያ ጠርጣራ መሆን አለባቸው ብዬ አስባለሁ። ሰዎች ምን እንደሚቀበሉ፣ ኩባንያው ምን መረጃ እያገኘ እንደሆነ ወይም እንዴት እንደሚጠቀምበት በደንብ ሳይረዱ ከስልካቸው ብዙ መረጃዎችን አሳልፈው ይሰጣሉ” ብለዋል።