ኢትዮጵያ የግድቡን ውዝግብ “ለጊዜ መግዣነት እየተጠቀመችበት ነው” ስትል ግብፅ ከሰሰች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኢትዮጵያ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን ውዝግብ ግድቡን ለመሙላት እንደ “ጊዜ መግዣ እየተጠቀመችበት ነው” ስትል ግብፅ ከሰሰች።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ ስምምነት ሳይደረስ ግዙፉን ግድብ በውሃ መሙላቷን ለመቀጠል የሚካሄደውን ድርድር “ለጊዜ መግዣነት እየተጠቀመችበት ነው” ብለዋል።
በአፍሪካ ትልቁ የሚባለውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን እየገነባች ያለችው ኢትዮጵያ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት ግድቡን በውሃ ስትሞላ ቆይታለች።
በዚህ ዓመትም በመጪዎቹ የክረምት ወራት ለአራተኛ ጊዜ የግድቡን የውሃ ሙሌት ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።
ግብፅ እና ሱዳን ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ግዙፍ ግድብን በውሃ መሙላት ከመጀመሯ በፊት አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት በማለት ሲወተውቱ ቢቆዩም፣ ኢትዮጵያ ሳትቀበለው ለሦስት ዙር ግድቡ ውሃ እንዲይዝ አድርጋለች።
ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ በግድቡ ዙሪያ እየተጀመረ ሲቋረጥ የቆየ ድርድር ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን፣ ሱዳን እና ግብፅ የግድቡን የውሃ ሙሌት እና ቀጣይ ሥራን በተመለከተ አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈረም ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ግን በሁለቱ አገራት በኩል የሚቀርቡ የስምምነት ሐሳቦች አብዛኛው ውሃው ከግዛቷ የሚመነጨውን የአባይ ወንዝን በሚያስፈልጋት ሁኔታ ጥቅም ላይ እንዳታውል የሚገድብ ነው ስትል ሳትቀበለው ቀርታለች።
ምክትል ሚኒስትሩ ረቡዕ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ ግብፅ የሕዳሴ ግድብ ውዝግብን “ፖለቲካዊ” እያደረግቸው ነው በሚል ከኢትዮጵያ በኩል የተሰነዘረውን ክስ አውግዘዋል።
ይህንንም ተከትሎ በግብፅ መገናኛ ብዙኃን በኩል የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ መልሶ መነጋገሪያ ሆኗል። በግብፃውያን በኩል ግድቡ አገራቸው ከአባይ ወንዝ የምታገኘውን የውሃ ጠንን በመቀነስ ጉዳት ያስከትልባታል የሚል መከራካሪያ ሲቀርብ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያ ግን የአባይ ውሃን የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት እንዳለት በመግለጽ፣ ግድቡ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን የውሃ አቅርቦት በማይጎዳ ሁኔታ የኤሌክትሪክ ኃይልን ለማመንጨት እንደምታውለው ስትገልጽ ቆይታለች።
ግንባታው ከተጀመረ ከአስር ዓመት በላይ የሆነው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ 90 በመቶው መጠናቀቁ የተገለጸ ሲሆን፣ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለጎረቤት አገራት ኃይል ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ላለፉት ሦስት ዓመታት በተከታታይ የውሃ ሙሌቱ ሲካሄድ የነበረው ግድብ ባለፈው ዓመት በተወሰነ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታ መጀመሯን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ ከግብፅ እና ከሱዳን በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማት ሲሆን፣ የግድቡ ጉዳይም ከአፍሪካ ኅብረት ባሻገር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ሦስቱ አገራት በግድቡ ዙሪያ በተለያዩ ጊዜያት በአፍሪካ ኅብረት እና በአሜሪካ አደራዳሪነት ንግግር ቢያደርጉም ሁሉንም ከሚያግባባ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ቆይተዋል።
ተጠናቆ ሥራውን ሲጀምር በአፍሪካ ግዙፉ እንደሆነ የሚነገርለት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አገሪቱ አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ከራሷ በማውጣት እያከናወነች ነው።












