ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ተቃውሞ እንደሌላት አስታወቀች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ጄኔራል አል ቡርሐን ካርቱም ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, @PMEthiopia

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና ጄኔራል አል ቡርሐን ካርቱም ውስጥ

ሱዳን እየተጠናቀቀ ባለው የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ ተቃውሞ እንደሌላት የሱዳን የሽግግር ሉአላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር የሆኑት ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን ተናገሩ።

ሊቀመንበሩ ይህንን ማለታቸው የተገለጸው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በካርቱም ያደረጉትን የአንድ ቀን ጉብኝት ተከትሎ ምክር ቤታቸው ባወጣው መግለጫ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን የካርቱም ጉብኝት ተከትሎ ሁለቱ መሪዎች በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ መነጋገራቸው የተገለጸ ሲሆን “ሱዳን እና ኢትዮጵያ የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከቱ ሁሉም ጉዳዮች ላይ እንደሚስማሙ እና እንደሚደጋገፉ. . . ቡርሃን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል” ብሏል መግለጫው።

ግንባታው ከተጀመረ አስር ዓመታት ያስቆጠረው ግዙፉ ግድብ ለሦስት ዙር የውሃ ሙሌት ተካሄዶ በተወሰነ ደረጃ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወቃል።

በዚህ ሂደት ውስጥ ግብፅ እና ሱዳን ግድቡ አብዛኛው ውሃው ከኢትዮጵያ የሚመነጨው ከአባይ የሚያገኙት የውሃ መጠን ላይ ተጽእኖ ስለሚኖረው በውሃ ሙሌቱ ላይ እና በግድቡ አስተዳደር ዙሪያ አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት እንዲደረግ ሲጥሩ ቆይተዋል።

የቀድሞው የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ አገሪቱ በግድቡ ዙሪያ ያላት አቋም ተቀይሮ ከግብፅ ጋር በጋራ በመቆም ጥያቄ ስታቀርብ ቆይታለች።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ከተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ሥልጣን የጨበጡት ጄኔራል አልቡርሃን በተለያዩ አጋጣሚዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መገናኘታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የድንበር እና የግድቡ ጉዳይ ላይ መነጋገራቸው ተገልጾ ነበር።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ማጠቃላያ ላይ በጋራ በወጣው መግለጫ ላይም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ እና የድንበር ጉዳይን በተመለከተ የሕዝቦቻቸውን ጥቅም በሚያስከብር ሁኔታ በንግግር እና በመግባባት መፍትሔ ለመስጠት መስማማታቸውን አሳውቀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበራቸውን በአግባቡ ለመለየት እና ለአወዛጋቢ አካባቢዎች መፍትሄ ለማበጀት የጋራ የድንበር ኮሚሽን አቋቁመው ለዓመታት ንግግር ሲያደርጉ ቢቆይም፣ ከሁለት ዓመት በፊት ትግራይ ውስጥ ጦርነት ሲቀሰቀስ ሱዳን ሠራዊቷን በማሰማራት ይገባኛል ያለችውን ሰፊ ለም መሬት መቆጣጠሯ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥትም የሱዳንን እርምጃ በመቃወም ሠራዊቷን እንድታስወጣ እና በንግግር መፍትሄ እንዲሰጥ ሲጠይቅ ቢቆይም፣ በርካታ አርሶ አደሮች የተፈናቀሉበት አካባቢ አሁንም በሱዳን ሠራዊት እጅ ስር ይገኛል።

አሁን በሁለቱ አገራት መሪዎች መካከል የተደረገው ንግግር ምናልባትም የድንበር ኮሚሽኑ ሥራውን እንዲጀምር እና ለድንበር ይገባኛል ጥያቄው መፍትሄ ለመስጠት ያስችል ይሆናል።

የሕዳሴ ግድብን በተመለከተም ሱዳን ያላትን ተቃውሞ እና ጥያቄ የምታነሳ ከሆነ፣ በቀጣይ የግድቡ ውሃ አያያዝ እና አጠቃላይ ሥራ ላይ ግብፅን በማካተት ተቋርጦ የቆየው ንግግር እንዲጀመር ሊያደርገው ይችላል።

በየዓመቱ ከአባይ ወንዝ በሚነሳ ካባድ ጎርፍ ለመትጥለቀለቀው ሱዳን ውሃውን በመቆጣጠር ረገድ የህዳሴ ግድብ ሊጠቅማት እንደሚችል ብታምንም፣ በውሃ ሙሌቱ እና በተለያዩ ወቅቶች ሊከሰት በሚችል የዝናብ እጥረት ወቅት ከግድቡ ውሃ በሚለቀቅበት ሁኔታ ላይ ከስምምነት እንዲደረስ ስትጠይቅ ቆይታለች።

ግብፅ እና ሱዳን አሳሪ ሕጋዊ ስምምነት ሳይደረግ ኢትዮጵያ ግድቡን በውሃ የመሙላት ሥራ እንዳታከናውን በተደጋጋሚ ቢጠይቁም፣ ተቀባይነት ሳያገኙ ግድቡ ውሃ እንዲይዝ ተደርጎ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ደረጃ ኤሌክትሪክ የማመንጨት ሥራ ጀምሯል።

ኢትዮጵያ ለግንባታው ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ያደረገችበት በአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሆነው ግድብ ከአምስት ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል በማመንጨት ሱዳንን ጨምሮ ለሌሎች አገራት ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።