የዓለምን የጦርነት ገጽታ ይቀይራል የተባለው የሩሲያው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል

የሩሲያ ሚሳኤሎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ ሚሳኤሎች

በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በሁለቱ ሠራዊቶች መካከል ከሚካሄደው ውጊያ ባሻገር ዓለማችን የምታስተናግዳቸው ጦርነቶች ይዘት እየተቀየረ መሆኑን እያመለከተ ነው።

ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ የዓለም ኃያላን አገራት በዘመናዊ የጦር መሳሪያ ግንባታው መስክ የነበራቸው የተቀዛቀዘ ፍላጎት መልሶ እያንሰራራ መሆኑን ምልክቶች እየታዩ ነው።

ሩሲያ እና የኔቶ አገራትም በዩክሬን ጦርነት ሰበብ ያላቸውን የጦር መሳሪያ አቅም ለማሳየት ዳር ዳር እያሉ ነው። በዚህም ወደፊት በዓለም ላይ የሚካሄዱ ጦርነትን ገጽታ የሚቀይሩ መሳሪያዎች የሚሞከሩበት እየሆነ ነው።

ሩሲያ ሃይፐርሶኒክ የተባለው እጅግ ዘመናዊ ሚሳኤል መጠቀሟ ለዚህ ማሳያ ምስክር ነው።

ሚሳኤሉን ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ በከፈተችበት የመጀመሪያ ወራት ተጠቅማዋለች። ይህም ሃይፐርሶኒክ የተባለው ሚሳኤል በዓለም ጦርነት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለበት ነው ተብሏል።

ሩሲያ በዩክሬን ይዞታዎች ላይ ጥቃቷን ባጠናከረችበት ጊዜ፣ ባለፈው መጋቢት ሚሳኤሉን ተጠቅማለች። በጥቃቱ ቢያንስ 9 ሰዎች መገደላቸው እና በመሠረተ ልማቶች ላይ ሰፊ ውድመት መድረሱ ተዘግቧል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢጎር ኮናሼንኮ ሚሳኤሉ ጥቅም ላይ መዋሉን አረጋግጠዋል። “ኪንዣል ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልን ጨምሮ፣ ለይተው በሚመቱ ረጅም ርቀት በሚጓዙ መሳሪያዎች የዩክሬንን ቁልፍ ወታደራዊ ተቋማት ተመትተዋል” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የሩሲያው ፕሬዝዳንት አገራቸው ይህንን ሃይፐርሶኒክ የተባለ እጅግ ፈጣን እና ኢላማውን በመምታት የማያጠራጥረውን ሚሳኤል ለመገንባት ትኩረት መስጠቷን ተናግረው ነበር።

ይህንን ሚሳኤል በመገንባት በኩል ግን ሩሲያ ብቸኛዋ አይደለችም። አሜሪካ፣ ኢራን እና ቻይናን የመሳሰሉ አገራትም ወሳኙን የጦር መሳሪያ ለመገንባት እና ለመታጠቅ በየበኩላቸው ሲጥሩ ቆይተዋል።

ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ምንድን ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሩሲያውያን ያላቸውን ዘመናዊው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልን “ኪንዣል” የሚል ስም የሰጡት ሲሆን፣ በስፓኒሽ ቋንቋ ጩቤ ማለት ነው።

የሩሲያ መንግሥት እንደሚለው ሚሳኤሉ በሰዓት 6,000 ኪሎ ሜትሮችን የሚወነጨፍ ሲሆን፣ በ2,000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ኢላማን ማውደም ይችላል።

ሚሳኤሉ የሚያስወነጭፋቸው ሮኬቶች ስምንት ሜትር ርዝመት አላቸው። በከፍተኛ ደረጃ አቅጣጫቸውን የሚቀያይሩ ሲሆኑ፣ ይህም ማለት አንድ ጊዜ ከተተኮሱ በኋላ አየር ላይ እንዳሉ አቅጣጫ እንዲቀይሩ እና እንዲያስተካክሉ ማድረግ ይቻላል።

የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ዋነኛ መለያው ደግሞ የሚጓዝበት ለዕይታ አስቸጋሪ የሆነው ፍጥነቱ ነው። እንደሚባለው ሚሳኤሉ በሰከንድ 1.6 ኪሎ ሜትር ያህል የመጓዝ ፍጥነት አለው።

ዘርፈ ብዙ ብቃት ያለው ይህ ሚሳኤል ከመደበኛ ተተኳሾች በተጨማሪ የኑክሌር አረሮችን ማስወንጨፍ ይችላል። በተጨማሪም ሚሳኤሉን ከአየር፣ ከባሕር እና ከየብስ ለመተኮስ በሚያስችል ሁኔታ ሊጠመድ ይችላል።

የቢቢሲ የደኅንነት ዘጋቢ ፍራንክ ጋርድነር እንደሚለው “ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ሁለት አይነት ሲሆን፣ አንዱ የሚወነጨፍ ሌላኛው ደግሞ የሚያንዣብብ አይነት ነው።”

“ሩሲያ በርካታ ተወንጫፊው አይነት ሚሳኤል ያላት ሲሆን፣ ከአውሮፕላን ላይ ተወንጭፎ ከ1,900 ኪሎ ሜትር በላይ በሆነ ርቀት ላይ የሚገኝ ኢላማን መምታት ይችላል። የሚያንዣብበው የሚሳኤል አይነት ደግሞ ወደ ሰማይ ተወንጭፎ በማይጠበቅ ሁኔታ ወደ መሬት ተንሳፎ በመመለስ ኢላማውን የሚመታ ነው” ይላል ጋርድነር።

ከዚህ ሚሳኤል ጥቅም ላይ መዋል ጋር ተያይዞ የውጤታማነቱ ጉዳይ በባለሙያዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል።

ሩሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልን ጥቅም ላይ ስታውለው፣ በካርኒጌ የዓለም አቀፍ የሰላም ተቋም ውስጥ የኑክሌር ፖሊሲ ባለሙያ የሆኑት ጄምስ አክሽን የሚኖረው ተጽእኖ እምብዛም አልታያቸውም። ለሩሲያ ያመጣል የሚባለውንም የበላይነት በጥያቄ ነበር የተመለከቱት።

በስዊትዘርላንድ ዙሪክ የደኅንነት ጥናት ማዕከል ውስጥ ባለሙያ የሆኑት ዶሚኒካ ኩኔርቶቫ እንደሚሉት ደግሞ የሚሳኤሉ ጥቅም ላይ መዋል “ለምዕራቡ አንዳች ምልክት ነው” ይላሉ። ነገር ግን “ሩሲያ በርካታ ሱፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ስለሌሏት” ብዙም የሚያስመካ አይደለም ይላሉ።

ኪንዣል የተባለውን የተባለውን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል የታጠቀ የሩሲያ ተዋጊ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኪንዣል የተባለውን የተባለውን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል የታጠቀ የሩሲያ ተዋጊ አውሮፕላን

ሃይፐርሶኒክ ከሌሎች ሚሳኤሎች በምን ይለያል?

በእርግጥ የሃይፐሶኒክ ሚሳኤል ቴክኖሎጂ ለጦር መሳሪያ ግንባታው ዘርፍ አዲስ እሳቤ አይደለም።

በዓለም የኑክሌር ጦር መሳሪያ ዘርፍ ውስጥ የሚካተቱት ቀደም ያሉት አህጉር አቋራጭ ተወንጫፊ ሚሳኤሎች፣ ከፍጥነት አንጻር ከሱፐርሶኒክ ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው።

ዋነኛው ልዩነታቸው ግን አህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎች አንድ ጊዜ ከተወነጨፉ ሊገመቱ በሚችሉ አቅጣጫዎች ነው የሚጓዙት። ሱፐርሶኒኮች ግን ከተተኮሱ በኋላ ፍጥነታቸውን እንደጠበቁ የመወንጨፊያ ከፍታቸውን እና አቅጣጫቸውን ሊቀያይሩ ይችላሉ።

ባለሙያዎች እንደሚሉት እንደ ቻይና እና አሜሪካ ሁሉ ሩሲያ እያዘጋጀች ያለው ቀጣዩ ዘመናዊ ሱፐርሶኒክ ሚሳኤል ለዓለም ሰላም እና ደኅንነት ከፍተኛ ስጋትን ይደቅናል።

ሩሲያ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች የኑክሌር አረሮችን ሊሸከሙ ይችላሉ ትላለች። ይህ “እውነትም ሆነ ሐሰት” በአገራት መካከል ውጥረትን በመጨመር የዲፕሎማቲክ መስመሮችን ያጠባል፣ የሚሉት በአሜሪካ ኮሎራዶ ዩኒቨርስቲ የአየር በረራ ኢንጂነሩ ኢያን ቦይድ ናቸው።

“የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ፍጥነት የሚከሰቱ ፍጥጫዎችን እና ጦርነቶችን አሳሳቢነት የበለጠ ያወሳስበዋል፤ ምክንያቱም ግጭቶችን ለማስቀረት የሚደረጉ የመጨረሻ ሰዓት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን ዕድል ስለሚነፍግ ነው” ሲሉ ቦይድ ጽፈዋል።

ይህ ሚሳኤል ሰላምን በማናጋት በኩል ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረው በመግለጽ፣ አሜሪካ እና አጋሮቿ ከሩሲያ እና ከቻይና ጋር በእነዚህ መሳሪያዎች ላይ ዲፕሎማሲያዊ መንገድን ለመከተል እና ለመደራደር “የራሳቸውን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን ይፋ ማድረግ አለባቸው” ይላሉ።

የሌሎች አገራት ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች

ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን እየገነቡ መሆናቸውን ከሚናገሩ አገራት መካከል ሰሜን ኮሪያ አንዷ ናት።

እንዲሁም ሩሲያ የመጀመሪያውን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ጥቅም ላይ ካዋለች በኋላ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያ ሚሳኤሉን በተመለከተ የበለጠ ለመረዳት እንዲሁም እራሳቸውን ለመከላከል ትብብር ጀምረዋል።

ይህ ፕሮግራምም ሦስቱ አገራት በቅርቡ ይፋ ያደረጉት ‘አውኩስ’ የተባለው የጋራ ደኅንነት ትብብር ስምምነት አንድ አካል ነው።

ከምዕራባውያን በተለይም ከአሜሪካ ጋር ዐይን እና ናጫ የሆነችው ኢራን ባለፈው ኅዳር ወር ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል እንዳላት ማሳወቋ ይታወሳል።

ሰሜን ኮሪያም ይህን አይነቱን የጦር መሳሪያ ሙከራ “በተሳካ ሁኔታ” ስለማከናወኗ አሳውቃለች።

ሱፐርሶኒክ ሚሳኤልን ሩሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ካዋለች በኋላ ኢያን ቦይድ እንዳሉት፣ የመሳሪያው ግንባታ ወጪ “ውድ ስለሚሆን በብዛት የማምረቱ ሁኔታ የሚሆን አይደለም።”

ነገር ግን ወደፊት በሚከሰቱ ጦርነቶች ላይ ከድምጽ የሚፈጥነው ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል ተጽእኖውን በማሳደር በኩል የሚያጠራጥር እንዳልሆነ ባለሙያዎች ያምናሉ።