አዘውትረው ከፑቲን ጋር ፎቶ የሚነሱት ‘ቅጥረኛ ተዋንያን’ እነማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለፈረንጆች አዲስ ዓመት የተነሱት ፎቶግራፍ አነጋጋሪ ሆኗል።
ፑቲን ፎቶውን ከወታደሮቻቸው ጋር ነው የተነሱት ተብሎ ነው የተነገረው። ነገር ግን ከፑቲን ጀርባ ያሉት ወታደሮች ሳይሆኑ ‘ቅጥረኛ ተዋንያን’ ናቸው እየተባለ ነው።
ቭላድሚር ፑቲን ‘ከቅጥረኛ ተዋንያን’ ጋር ፎቶ ሲነሱ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም እየተባለም ይገኛል።
ቢቢሲ የሰዎችን ገጽታ ከፎቶ አይቶ ማንነታቸውን በሚገልጸው የኮምፒውተር ፕሮግራም (facial recognition software) የሰዎቹን ፎቶ አመሳክሯል።
ፑቲን የተለያዩ መሰናዶዎች ላይ ፎቶ ይነሳሉ። የዝግጅቶቹ ላይ ተሳታፊ ናቸው ተብለው ፎቶ ውስጥ የሚካተቱት ሰዎች ግን እውነተኛ ስለመሆናቸው ጥያቄ ይነሳል።
‘ከተርታው ሕዝብ ጋር’ ፑቲን ሲነጋገሩ ያሳያሉ የተባሉ ምሥሎች ውስጥ ያሉ ሰዎች እንደተባለው ‘ተርታ ሕዝብ’ ሳይሆኑ የፑቲን የቅርብ ወዳጆች እና ባለሥልጣናት እንደሆኑ የቢቢሲ የሩሲያ ቋንቋ አገልግሎት እአአ በ2020 የሠራው ዳሰሳ ደርሶበታል።
‘ዘ ሰን እና ዴይሊ ሜል’ ድረ ገጾች ዘገባ እንደሚያሳየው፣ በተለይ አንዲት ሴት የተለያየ ቦታ ላይ የተለያዩ ሰዎችን ወክላ ፎቶ ስትነሳ ተስተውሏል።
በ2016 ፑቲን ዓሣ ሲያጠምዱ አብራ ፎቶ ተነስታለች። በ2017 (እአአ) ከፑቲን ጋር ቤተክርስቲያን ውስጥ አብራ ፎቶ ተነስታለች። ከሰሞኑ በተከበረው የፈንጆች አዲስ ዓመት ፑቲን ከወታደሮች ጋር ፎቶ ሲነሱም አብራ ተነስታለች።
ይህች ሴት የሩሲያ ፌደራል ጥበቃ ኃይል አባል እንደሆነች የዩክሬን ዘገባዎች ይጠቁማሉ።
ቢቢሲ የኮምፒውተር ፕሮግራምን በመጠቀም በአዲስ ዓመት የተነሳችውን ሴት በ2016 እና በ2017 ከተነሳችው ሴት ጋር ሲያነጻጽር 29 በመቶ እና 28 በመቶ ተመሳሳይነት አግኝቷል። ቢቢሲ በ2016 እና በ2017 የተነሳችውን ሴት ሲያነጻጽር 99.1 በመቶ ተመሳሳይነት አግኝቷል።
በብራድፎርድ ዩኒቨርስቲ የቪዥዋል ኮምፒውቲንግ ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ሐሰን ዩጊል እንደሚሉት፣ ከ75 በመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ሲገኝ በተለያየ ፎቶ የሚታየው ግለሰብ አንድ ሰው እንደሆነ ይታመናል።

በሩሲያ ሚዲያ ይህች ሴት ላሪሳ ሰርጉኪና እንደሆነች ተገልጿል።
በኖቭጎሮድ ግዛት የምክር ቤት አባል ናት። ሁለቱም ከፑቲን ጋር የተነሳቻቸው ፎቶዎች የተወሰዱት በዚህ ግዛት ነው።
በበይነ መረብ ካለው ይፋዊ ፎቶዋ ጋር ከፑቲን ጋር በዓሣ ማጥመጃ ጀልባ የተነሳችው ፎቶ ሲነጻጸር 99.8 በመቶ ተመሳሳይነት ተስተውሏል።
ላሪሳ በዚያው ግዛት የዓሣ ምርት ተቋም ባለቤትም ናት።
ከፑቲን ጋር በአዲስ ዓመት ፎቶ የታየችው ሴት አና ሰርጊቫና እንደምትባል የሩሲያ ሚዲያ ዘገባ ይጠቁማል።
ካፒቴን እና የወታደሮች ሐኪም ስትሆን ከሩሲያ ከኢስቬስቲያ ጋዜጣ ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስ ከተለጠፈው ፎቶዋ ጋር የአዲስ ዓመቱ ፎቶ ሲነጻጸር በ99.5 በመቶ ተመሳሳይ ሆኖ ተገኝቷል።

በ2016 ከፑቲን ጋር እንደ ‘ዓሣ አስጋሪ’ ፎቶ የተነሱት ወንዶች በ2017 ቤተክርስቲያን ውስጥ ከፑቲን ጋር ፎቶ ተነስተዋል የሚሉ አሉ።
ቢቢሲ በምሥሎቹ ያሉትን ወንዶች ሲያነጻጽር በአራቱ መካከል 99 በመቶ ተመሳሳይነት አግኝቷል።
ሁሉም በኖቭጎሮድ ግዛት እንደሚኖሩ እና ቢያንስ ሦስቱ ዓሣ አስጋሪ እንደሆኑ ቢቢሲ ማወቅ ችሏል።
አሌክሲ ሊያሽንኮ የተባለው በቁጥር 1 የሚታየው ግለሰብ የዓሣ አስጋሪው ቡድን መሪ ነው።

በቁጥር 5 የሚታየው ዬቫግኒ ደግሞ የአሌክሲ ልጅ እንደሆነ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እነዚሁ ሰዎች በአንድ የግብርና ቡድን ውስጥ እንዳሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ከለጠፏቸው ፎቶዎች መረዳት ይቻላል።
ምክትል ዳይሬክተሯ ደግሞ ላሪሳ ናት።
በቁጥር 2 የሚታየው ሰርጌ አሌክሳድሮቭ ዓሣ አስጋሪ ተብሎ በሩሲያ ሚዲያ ተጠቅሷል። የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ላይም የዓሣ አስጋሪ ልብስ ለብሶ ፎቶዎች አሉት።
በቁጥር 4 ያለው ግለሰብ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ፎቶው አልተገኘም።
ሌላ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተለጠፈ ፎቶ እነዚሁ ሰዎች በስቫርፖል ግዛት እንደ አርሶ አደር ሆነው ከፑቲን ጋር ፎቶ መነሳታቸውን ይጠቁማል።
ሆኖም ግን ምሥላቸው በመተግበሪያ ሲነጻጸር 8 በመቶ ብቻ ተመሳሳይነት ነው የተገኘው።

በ2017 እና በ2019 ለፑቲን አይስ ክሪም ስታቀርብ የምትታየው ሴት ሌላ ጥያቄ የሚነሳባት ናት።
የተነሳቻቸው ፎቶዎች ጥራት የጎደላቸው ስለሆኑ መተግበሪያ በመጠቀም ማጣራት ባይቻልም፣ በ2019 በተደረገ ቃለ ምልልስ ላይ ለፑቲን በሁለቱም ዓመታት አይስ ክሪም ያቀረበችው እሷ እንደሆነች የተናገረች ሴት አለች።
ፑቲን በሁለቱም ዓመታት በተመሳሳይ ቦታ የአውሮፕላን ትዕይንት ለመመልከት ሄደው ነው ፎቶዎቹ የተነሱት።
ስለዚህም በሁለቱም ጊዜ አይስ ክሪም የሸጠችላቸው አንድ ሴት ብትሆን እምብዛም አይገርምም።
ነገር ግን ይህች ሴት ኤሮፍሎት የተባለው የሩሲያ አየር መንገድ ሠራተኞች ጋር አብራ ፎቶ መነሳቷ ይነገራል። በምሥል ጥራት መጓደል ምክንያት ግን ፎቶዎችን በመተግበሪያ ማጣራት አልተቻለም።
ከወራት በፊት ፑቲን ከአንድ ቁስለኛ ወታደር ጋር ፎቶ እንደተነሱ እና ይሄው ወታደር ግን ቀደም ሲል ፋብሪካ ውስጥ ከፑቲን ጋር ፎቶ እንደተነሳ የሚናገሩም አልታጡም።
የምሥል ማነጻጸሪያ መተግበሪያው ግን በሁለቱ ወንዶች መካከል ያለው ተመሳሳይነት 25 በመቶ እንደሆነ ይጠቁማል። ያ ማለት ደግሞ ወንዶቹ አንድ ሰው አይደሉም ማለት ነው።












