ከመጋረጃ ጀርባ የሚካሄደው የሩሲያና የምዕራባውያን ሰላዮች ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምዕራቡና ሩሲያ የሚዋጉት በአፈሙዝ ብቻ አይደለም። በሳይበር ብቻም አይደለም።
የሰላዮች ጦርነት የሚባል አለ።
ብዙ የማይታይ፣ ብዙ የማይዳሰስ፣ ይልቅ ለጀምስ ቦንድ ፊልምነት የቀረበ ነው።
አንዱ አገር ሌላውን ይሰልላል፤ ያለመታከት።
ሩሲያ ወደ አውሮፓ ሰላዮቿን አስርጋ ታስገባለች። አንዳንዴ በቱሪስት ስም፤ ሌላ ጊዜ በዲፕሎማሲ ስም።
ምዕራብ አገራትም ይህንኑ ነው የሚያደርጉት።
ይህ የሰላዮች ጦርነት ያለና የነበረ ነው።
አሁን በዩክሬን እና በሩሲያ ውጊያ ምክንያት እየፈጠጠ መጣ እንጂ ከቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ጀምሮ የሶቪየቱ ኬጂቢም ሆነ የአሜሪካው ሲአይኤ መች ተኝተው ያውቃሉ።
የምዕራቡ ዓለም የስለላ ሰንሰለት አያንቀላፋም።
ሸለብ አድርጎት ግን ያውቃል። ሩሲያ በዚህ ደረጃ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደምትከፍት ለመተንበይ ተስኖት ነው የቆየው።
ሸለብ ባያደርገው ገና ድሮ ከሩሲያ የጋዝ እና ነዳጅ ኃይል ጥገኝነት ለመላቀቅ ብዙ በሠራ ነበር እየተባለ ይታማል።
በአንጻሩ ራሳቸው የኬጂቢ ሰላይ በነበሩት ፑቲን፣ ምሥራቅ ጀርመን በስለላ ጥርሳቸውን በነቀሉት ፑቲን የምትመራዋ ሩሲያ በስለላ ብዙ ርቀት ተጉዛለች።
ሩሲያ ዩክሬንን በ2014 ዓ.ም ስትዳፈራት፣ መጀመርያ ሰላዮቿን ነበር ወደ ምዕራብ የላከችው። ሁሉን ነገር ገምግመው መረጃ አቀብለዋታል።
ክሪሚያን ስትጠቀልል በሰላዮች የደለበ መረጃን ይዛ ነው።
ቀደም ብላ የሳይበር ቦርቧሪዎቿን በአሜሪካ ምርጫ እንዲዶልቱም አሰማራች።
መርዝ ቀማሚ ሰላዮቿን ደግሞ ወደ ምዕራብ አገራት ላከች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ድርብ ሰላዮችን፣ አገር ከድተዋል ያለቻቸውን ሰላዮችን፣ ለምዕራብ አድልተዋል ያለቻቸውን የቀድሞ ሰላዮችን አንድ በአንድ መርዝ አበላች። በጨረር ገደለች።
በሳይበርም በመርዝም ያሰማራቻቸው ሰላዮቿ ከሞላ ጎደል ተግባራቸውን ተወጥተው ተሰውረዋል።
ምዕራባዊያን ግን ይህ ሁሉ ሲሆን ሸለብ አድርጓቸው ነበር። ዘግይተው ይሆናል የነቁት።
በቅርቡ ግን ያጠፉትን ጊዜ ለማካካስ ምዕራባዊያን ጨክነዋል።
ምሥጢራዊ የስለላ ተግባር የሚያስፈጽሙ "ዲፕሎማት" የሚል መለያ ያጠለቁ ሩሲያዊያንን አንድ በአንድ ከአገራቸው እያባረሩ ነው።
እነዚህ በውድ ሱፍ የተንቆጠቆጡ፣ በባለ 5 ኮከብ ሆቴል ኮክቴል የሚያነሱ ዲፕሎማቶች ሁሉ ዲፕሎማቶች አልነበሩም።
መረጃን ሲቃርሙና ወደ እናት አገር ሩሲያ ሲልኩ ነው የከረሙት።
ይህን የተገነዘቡ አገራትም እርምጃ ወስደዋል።
ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከምዕራብ አገራት በድምሩ 500 ሩሲያዊያን "ዲፕሎማቶች" ተሸኝተዋል።
እነዚህ በተለምዶ ዲፕሎማቶች ይባሉ እንጂ የሙሉ ጊዜ ሰላዮች እንደሆኑ ሩሲያም ምዕራቡም ዓለም አሳምሮ ያውቀዋል።
የምዕራብ አገራትም ቢሆኑ ወደ ሞስኮ የሚያሰርጓቸው "ዲፕሎማቶች" ሁሉም የምር ዲፕሎማት ናቸው ማለት ይከብዳል።
ከነዚህ ውስጥ ሩሲያ 45 የሚሆኑትን አገሬን ሊያበጣብጡ መሰሪ ሥራ ሲሠሩ ደረስኩባቸው በሚል ሸኝታቸዋለች።

የፎቶው ባለመብት, Metropolitan Police
መርዝ የሚያበሉት የሩሲያ ሰላዮች
ከ2014 (እአአ) ጀምሮ ምዕራብ አገራት በትክክል የሩሲያ ሰላዮች ምንድነው የሚያደርጉት፤ እነማንስ ናቸው በሚለው ላይ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል።
ጂአርዩ (GRU Unit 29155) በሚል ምህፃር የሚታወቀው የሩሲያ ወታደራዊ የስለላ ክንፍ ብዙዎቹን የማፈን፣ የመግደል፣ መርዝ የማብላት፣ በነርቭ ንጥረ ነገር አመንምኖ የመግደል፣ እንዲሁም የፖለቲካ አሻጥር ሥራዎችን ሲፈጽምና ሲያስፈጽም እንደነበረ ደርሰውበታል።
ነገር ግን ምዕራቡ የዚህን ምሥጢራዊ የወታደራዊ ስለላ ክንፍ ዱካ ለማግኘት ድፍን ሰባት ዓመት ወስዶበታል።
ይህ ክንፍ በቼክ ሪፐብሊክ ጫካ ውስጥ ድብቅ የጦር መሣሪያ ማከማቻ መጋዘንን ዶግ አመድ ያደረገ ነው።
ይህ የሆነው በ2014 (እአአ) ነበር።
ከአራት ዓመት በኋላ የተፈጸመው በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ)፣ የሳሊስበሪ የነርቭ ጥቃትም በዚህ ቡድን የተቀነባበረ ነበር።
ለሁለት ወገን ማለትም ለዩኬው ኤምአይ5 እና ለቀድሞ የጂአርዩ ሰላይ የነበሩትን ሰው ከሴት ልጃቸው ጋር የመረዙት የዚህ ምሥጢራዊ ድርጅት ሁለት መኮንኖች እንደነበሩ ተደርሶበታል።
እኚህ ሰው ስለላ በቃኝ ብለው፣ ድምጽ አጥፍተው በሰላም ከሚኖሩበት ሳሊስቤሪ ነበር በኋላ ማንነታቸው በተለዩ ሁለት ሩሲያዊያን ሰላዮች በነርቭ ኤጀንት የተመረዙት።
ይህም የሆነው በውቧ የሳልስቤሪ ከተማ በቅጽበት በአንድ መናፈሻ ውስጥ ነበር።
ፈጣን ሕክምና አግኝተው አባትና ልጅ ከሞት ቢተርፉም ለዩኬና ለመላው አውሮፓ አስደንጋጭ ክስተት ነበር።
አሁን አባትና ልጅ ከመርዝ አገግመው ባልታወቀ ቦታ ሕይወታቸውን እየመሩ ነው።
ዩኬ ጉዳዩን ወደ አውሮፓ ኅብረት በመውሰድ ከአጋሮቿ ጋር በመሆን 124 የሩሲያ ዲፕሎማቶች እንዲባረሩ አድርጋለች።
ይህ የሰላዮች ቡድን ከዚህ ጥቃት ባሻገር በቡልጋሪያ የጦር መሣሪያ አሻሻጮችን አፍኖ መርዟል።
ይህ ቡድን በዩክሬን ፖለቲካዊ አመጽ ሲከሰት የሩሲያ አጋር የሆኑ ባለሥልጣናትን ከዩክሬን ያሾለከ ነው።
አሁን ከዩክሬን ጦርነት መፈንዳት በኋላ ምዕራብ አገራት ዝንጉነታቸውን እርግፍ አድርገው ትተዋል።
እያንዳንዱን ሩሲያዊ "ዲፕሎማት" 24 ሰዓት በንቃት ይከታተሉ ይዘዋል።
አንድ ነባር የአሜሪካ ባለሥልጣን በጉዳዩ ላይ ለቢቢሲ ሲናገሩ፣ "ቀደም ሲል ሩሲያ በርካታ ዲፕሎማቶችን ትልክብን ስለነበረ ክትትሉን ከባድ አድርጎት ቆይቷል" ብለዋል።
አሁን ግን በገፍ ዲፕሎማቶች ተባረው ጥቂት አስፈጻሚዎች ብቻ በየኤምባሲው እንዲቆዩ ነው የተደረገው።
እነዚህን በዲፕሎማትነት መለያ የተሰማሩ ሰላዮችን ማባረሩ ዘግይቷል የሚሉ በምዕራብ አገር የሚገኙ የጉዳዩ አዋቂዎች፣ "ሩሲያ ከልቧ ስትስቅብን ነው የኖረችው" ሲሉ ለቢቢሲ ጉዳዩን አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዲፕሎማቶች ወይስ ሰላዮች?
አንዳንድ የምዕራብ አገራት በርካታ የሩሲያ "ዲፕሎማቶችን" በጉያቸው ይዘው ሲሰለሉ ነው የኖሩት።
በርሊን 40 የሚሆኑትን በቅርቡ አባራለች። ከዚያ ቀደም ከመቶ በላይ ሰላዮችን ተሸክማ ነው የቆየችው፤ ጀርመን።
ይሁንና ምዕራብ አገራት በርካታ የሩሲያ ሰላዮችን ሲያባርሩ ዩኬ ግን እምብዛምም ከአገሯ ያላባረረችው ለምንድነው?
ዩኬ እንደምትለው ከሶሊስቤሪ የመርዝ ጥቃት ወዲህ በርካታ ዲፕሎማቶች ስለተባረሩ አሁን የቀሩት አስፈገላጊ ሥራዎችን ለመሥራት የሚያገለግሉት ብቻ ናቸው።
አሁን የቀሩት ግንኙነት ለመፍጠር የሚረዱ ናቸው። እነሱም ቢሆን የዩኬ የስለላ ተቋም፣ ኤምአይ5 በዓይነ ቁራኛ ይከታተላቸዋል።
አሜሪካ በበኩሏ የሩሲያ ዲፕሎማቶችን የምታባርረው ኤፍቢአይ በእያንዳንዱ ዲፕሎማት የስለላ ተግባር ተሳትፎ ላይ በሚያቀርበው መረጃ ነው።
ምዕራብ አገራት አንድ የተባረረ የሩሲያ ዲፕሎማት ወደ ሌላ ማንኛውም ወዳጅ አገር ለመሄድ ቪዛ እንዳያገኝ ይተባበራሉ።
ሩሲያም ለምዕራብ አገራት እርምጃ አጸፋውን ሳትውል ሳታድር መልሳለች።
ይሁንና ብዙዎቹ ከሰላይነት ይልቅ እውነተኛ ዲፕሎማቶች ናቸው የተባረሩት ይላሉ የምዕራብ አገር ተንታኞች።
ሩሲያ በቅርቡ 40 የጀመርን ዲፕሎማቶችን አባራለች።
አሁን ምዕራብ አገራት የደኅንነት ሰዎቻቸውን፣ የወታደራዊ ሊቆቻቸውን ከሞስኮ ይልቅ ወደ ዩክሬን እያሰረጉ እያስቡ ነው።
ዋንኛው ዓላማቸው ዩክሬናዊያንን ማሰልጠን፣ ማብቃት ነው። ምዕራብ አገራት ሳይሰስቱ መሣሪያም መረጃም እያቀበሉ ያሉት ለኬዬቭ ነው።
የምዕራብ አገር ሰላዮች ከፍተኛ ጥበባቸውን ለዩክሬናዊያን እየሰጡ ያሉት ሩሲያን ለመሰለል ከእንግዲህ ሩሲያን ከሚመስሉ ሰዎች የተሻለ እንደማይገኝ በመረዳታቸው ነው።
ሲአይኤ ዩክሬንን ዋንኛ ማዕከሉ ያደረጋት ዛሬ አይደለም። ቀደም ብሎም ሩሲያዊያንን በሰላይነት ለማሰልጠን ዩክሬን ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ ሆና አገልግላለች።
አሁን ግን ጊዜ የለም። ጥድፊያ ነው። ምዕራቡ ዩክሬንን የሚታደገው ራሱን ለመታደግ ጭምር ነው።
ሩሲያ እንዳሰበችው ዩክሬንን ከጠቀለለች የምዕራቡ ዓለም የበላይነት ያከትማል።
የዓለም ፖለቲካ አሰላለፍም ላይመለስ እስከወዲያኛው እንደሚቀየር ምዕራባዊያን ጠንቅቀው ያውቁታል።
አሁን የሩሲያ የስለላ መዋቅር የተጠመደው ምዕራቡ ወደ ዩክሬን ያለመሰሰት እያጋዘ የሚገኘውን መሣሪያ የሚገባበትን፣ የሚከማችበትን ቦታ ማሳበቅ ነው።
ይህ ከፖላንድ የሚነሳው የጦር መሣሪያ ድጋፍ በሩሲያ ሰላዮች እየተደረሰበት ለጥቃት እየተጋለጠ ነው።
የዓለም ፍርሃት ደግሞ ሌላ ነው። ሩሲያ በዚህ ጥቃት ፖላንድን ብትመታ ኔቶ ሊነሳ ይችላል።
ያን ጊዜ ሦስተኛው የዓለም ጦርነት ተቀሰቀሰ ማለት ነው።














