ሩስያ፡ ኔቶ የፑቲን መንግሥት ስለ ኖቪቾክ መርዛማ ኬሚካል መረጃ መስጠት አለበት አለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ሩስያ ስለ ኖቪቾክ ፕሮግራሟ ለዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች መረጃ መስጠት አለባት አለ።
የመብት ተሟጋቹ አሌክሴ ናቫልኒ መመረዙን ተከትሎ ነው ስለ ኖቪቾክ ነርቭ ኤጀንት (መርዛማ ኬሚካል) መረጃ እንድትሰጥ የተጠየቀው።
የኔቶ ጸሐፊ ጄንስ ስቶልበርግ አባላቱ ጥቃቱን አውግዘዋል ብለዋል። የመብት ተሟጋቹ በኖቪቾክ እንደተመረዘ “ማስረጃ አለ” ሲሉም አክለዋል።
ሩስያ ግን ለአሌክሴ ሕክምና እያደረገ ያለው ሆስፒታል የሰጠውን ማብራሪያ አጣጥላለች።
ድርጅቱ አስቸኳይ ስብሰባ ካደረገ በኋላ “ሩስያ በዓለም አቀፍ ምርመራ የኬሚካል መሣሪያ ላይ እገዳ እንዲጣል መተባበር አለባት። ስለ ኖቪቾክ ፕሮግራም ሙሉ መረጃ መስጠት አለባት” መባሉን ጸሐፊው አስታውቀዋል።
ይህ ኬሚካል የቀድሞው ሰላይ ሰርጌ ሰኬሪፓልን እና ልጁን ለመመረዝም ውሎ ነበር። አባትና ልጅ እአአ በ2018 ዩኬ ውስጥ ሲመረዙ የሩስያ ወታደራዊ ስለላ መወቀሱ ይታወሳል።
20 አገራት ከመቶ በላይ የሩስያ ዲፕሎማቶችና ሰላዮችን ከአገራቸው አባረውም ነበር። ሩስያ ግን በጉዳዩ እጄ የለበትም ብላ ነበር።
ጸሐፊው በተጨማሪም “ይሕ ዓለም አቀፍ መርህ መጣስ ነው። ስለዚህ ዓለም አቀፍ እርምጃ ያስፈልጋል” ብለዋል።
በርካታ የሩስያ ከፍተኛ የሕዝብ እንደራሴዎች የኔቶን ጥያቄ ችላ ብለዋል።
የሩስያ ፌደሬሽን ካውንስል ኮንስታንቲን ኮሳቼቭ፤ “አሌክሲ የኬሚካል መሣሪያ ስምምነትን በጣሰ ኬሚካል መመረዙ ሳይረጋገጥ ኔቶን በጉዳዩ ማስገባት ነገሩን ፖሊቲካዊ ማድረግ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ፑቲንን የሚቃወመው አሌክሲ የጸረ ሙስና አቀንቃኝ ነው። ከሳይቤሪያ ወደ ሞስኮ ሲሄድ አውሮፕላን ውስጥ ታሞ ጀርመን ለሕክምና ተወስዶ ነበር።
ሩስያ የጀርመኑን የሕክምና ውጤት እንዳላየችና ተመርዟል የሚለውን ድምዳሜ እንደማትቀበል ተናግራለች።
የአውሮፓ ሕብረት፤ የሩስያ መንግሥት ጉዳዩን በግልጽ እንዲመረምር ጠይቋል። የአሜሪካ ብሔራዊ የጸጥታ ካውንስልም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሩስያን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት ገልጿል።














