ፖለቲካ፡ የሩሲያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አሌክሲ ናቫልኒ "ተመርዘዋል" - ቃለ አቀባያቸው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሩሲያ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጣቸውና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የሆኑት አሌክሲ ናቫልኒ ራሳቸውን ስተው ሆሰፒታል መግባታቸውን ቃለ አቀባያቸው ተናግረዋል። ፖለቲከኛው ሳይመረዙም አልቀረም ተብሏል።
በፀረ-ሙስና ዘመቻቸው የሚታወቁት አሌክሲ በበረራ ላይ እያሉም ነው በአውሮፕላን ውስጥ ተዝለፍልፈው የወደቁት።
አውሮፕላኑን በድንገተኛ ሁኔታም ኦምስክ የሚባል ቦታ ለማረፍ መገደዱንም ቃለ አቀባይዋ ኪራ ያርሚሽ በትዊተር ገፃቸው አስታውቀዋል።
ዛሬ ጥዋትም ከመዲናዋ ሞስኮ ወደ ቶምስክ እየተመለሱ እንደነበርም መረዳት ተችሏል።
ኪራ እንደሚሉት ሻያቸው ላይ መርዝ ተጨምሮ እንደተሰጣቸው እንደሚጠረጥሩ ነው።
"በበረራው ወቅት በጠና ታመሙ። አውሮፕላኑም በድንገተኛ ሁኔታ አረፋ። አሌክሲ እንደተመረዘም ተረድተናል ወደ ሆስፒታል እየሄድን ነው" ብለዋል በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት
ቃለ አቀባይዋ ፖለቲከኛው ያሉበትን ሁኔታ እየተከታተሉ ከስር ከስሩ በትዊተር ገፃቸው እያሳወቁ ይገኛሉ።
"ፖለቲከኛው ሻያቸው ላይ መርዝ ተጨምሮ እንደተሰጣቸው እንጠረጥራለን፤ ምክንያቱም ከጥዋት ጀምሮ የቀመሰው ነገር ቢኖር ሻይ ብቻ ነው። ዶክተሮች መርዛማ ንጥረ ነገሮች ሞቅ ባለ ፈሳሽ ላይ በፍጥነት መዋሃድ ይችላሉ ብለዋል። በአሁኑ ሰዓትም ራሱን እንደሳተ ነው" ብለዋል።
ቆየት ብለውም ፖለቲከኛው በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙም በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
ምንም እንኳን ቃለ አቀባይዋ ይህንን ይበሉ እንጂ መመረዛቸው በገለልተኛ አካል ጉዳዩ አልተጣራም፤ አልተነገረም።
አሌክሲ ናቫልኒ በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ የሰላ ትችትን በማቅረብ ይታወቃሉ።
ከጥቂት ወራትም በፊት የህገ መንግሥት ማሻሻያ ላይ ድምፅ ይሰጥ መባሉን ተከትሎ ህገ መንግሥቱን የጣሰ ነው በማለት ከመፈንቅለ መንግሥት ጋር አመሳስለውታል።
ፖለቲከኛው ይህንን ያሉት ማሻሻያው የአገሪቱን የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ከሁለት ጊዜ በላይ መመረጥ እንዲያስችላቸው የሚያደርግ በመሆኑ ነው።
በተለይም በአገሪቱ ውስጥ ያለ ቅጥ የተንሰራፋውን ሙስና በማጋለጥ የህዝብ ቀልብ የሳቡት ፖለቲከኛው የፕሬዚዳንት ፑቲን ዩናይትድ ራሺያ (የተባበረች ሩሲያ) ፓርቲን "ሌቦችና ቀማኞች" ሲሉም ይጠሯቸዋል።
በጎርጎሳውያኑ 2011 የፑቲን ፓርቲ ምርጫን አጭበርብሯል በማለት ከፍተኛ ተቃውሞ ማስተባበራቸውን ተከትሎም ለአስራ አምስት ቀናት ታስረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በ2013ም ገንዘብ አጭበርብረዋል በሚል ክስ ለአጭር ጊዜ ታስረው የነበረ ቢሆንም እስሩ ፖለቲካዊ ነው በሚል በከፍተኛ ሁኔታ ተወግዟል።












