የአሜሪካን የአቪዬሽን ንግድ ሚስጥርን ሰርቋል የተባለው ቻይናዊ ተቀጣ

የጂኢ አቪየስን ፋብሪካ ውስጥ የሚገጣጠም አውሮፕላን ሞተር- ኩባንያው በሰላዩ ዒላማ ውስጥ ከነበሩ ኩባንያዎች መካከል አንዱ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቻይናዊው የስለላ ሠራተኛ የአቪዬሽን ኩባንያዎችን ምስጢር ለመስረቅ አሲሯል በሚል በአሜሪካ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ መባሉን የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

ዡ ያንጁን የተባለው ይህ ግለሰብ ከኢኮኖሚ ስለላ እና ከንግድ ምስጢር ስርቆቶች ጋር በያያዘ በቀረቡበት አምስት ክሶች ጥፋተኛ የተባለ ሲሆን የ60 ዓመት እስራት እና ከ5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅጣት ይጠብቀዋል።

ዡ ለመጀመሪያ ጊዜ በቁጥጥር ስር የዋለው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 ቤልጂየም ውስጥ ሲሆን ምናልባትም ለአሜሪካ ተላልፎ የተሰጠ የመጀመሪያው ቻይናዊ ነው ተብሏል።

የቻይና ባለስልጣናት ትናንት [አርብ] ስለተላለፈው ውሳኔ የሰጡት አስተያየት ባይኖርም ቻይና ቀደም ብላ ክሱን መሰረተ ቢስ ስትል ውድቅ አድርጋው ነበር።

የአሜሪካ የፍትህ መሥሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ መሰረት ዡ በቻይና ደኅንነት ሚኒስቴር ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚሰራ የስለላ ባለሙያ ነው።

ቻይናዊው ሰላይ ከአውሮፓውያኑ 2013 ጀምሮ በአሜሪካ እንዲሁም በሌላ አገራት ውስጥ የሚገኙ በርካታ ኩባንያዎች ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞችን ኢላማ አድርጎ ሲንቀሳቀስ ነበር ተብሏል።

ቻይናዊው እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 የአንድ አቪዬሽን ሠራተኛን የጉዞ ወጪ በመሸፈን እና አበል በመክፈል፣ ወደ ቻይና ተጉዞ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ገለጻ እንዲደረግ እስከመጋበዝ ደርሶ ነበር።

ይህ በሆነ በዓመቱ ባለሙያውን የአንድ ንድፍ ሂደትን የተመለከተ መረጃን እንዲሰጠው ዡ ጠይቋል ተብሏል።

ታዲያ ከኤፍ ቢ አይ ጋር ሲሰራ የነበረው ባለሙያው ምስጢራዊ የሆነ መረጃ የሚል ባለ ሁለት ገጽ ሰነድ ለዡ በኢሜይል ልኳል።

በመቀጠል ዡ ለባለሙያው ሥራ በሚጠቀምበት ኮምፒውተሩ ላይ የፋይል ቅጂ እንዲልክለት ጥያቄ ያቀርባል። በተጨማሪም በቤልጂየም ውስጥ ባለሙያውን ለማግኘት ሞክሯል። ሆኖም በዚህ ሙከራው ቻይናዊው በቁጥጥር ስር ውሏል።

የኤፍ ቢ አይ ረዳት ዳይሬክተር አለን ኮህለር "የቻይናን እውነተኛ ፍላጎት ለሚጠራጠሩ ይህ የማንቂያ ደወል ሊሆን ይገባል" ብለዋል። "የአሜሪካን ቴክኖሎጂ እየዘረፉ ኢኮኖሚያቸውን እና ወታደራዊ ኃይላቸውን ለማጠናከር እየተጠቀሙበት ነው" ሲሉም አክለዋል።

ይህ ክስ የተሰማው በሁለቱ አገራት መካከል ውጥረት በነገሰበት ወቅት ነው። ቻይና በቅርቡ አዲስ የሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልን ስትሞክር የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ታይዋንን ከማንኛውም የቻይና ወታደራዊ ወረራ ለመጠበቅ ቃል ገብተዋል።

እንደ ሲኤንኤን ዘገባ ከሆነ የሲአይኤ ዳይሬክተር ቢል በርንስ ቻይናን ለአሜሪካ ትልቁ የቴክኖሎጂ ስጋት መሆኗን ገልጿል። ባለፈው ወር የስለላ ድርጅቱ ቻይና ላይ የሚያደርገውን የስለላ ጥረት እንደሚያሳድግ ገልጿል።