አዲስ የተመሰረተው የተቃዋሚዎች ጥምረት እና የመንግሥት አስተያየት

የፎቶው ባለመብት, Oda Tarbi/FB
የኢትዮጵያ ፌደራሊስት እና ኮንፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት በሚል በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ለመተካት በሚል ዘጠኝ የፖለቲካ ቡድኖች ዋሽንግተን አንድ ጥምረት መመስረታቸውን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ፣ ጥምረቱ ይህ ነው የሚባል የፖለቲካ መሰረት የሌለው ደካማ ስብስብ ነው ሲል አጣጥለውታል።
በጥምረቱ ውስጥ ትብብር ለመፈጠር ከፈረሙት መካከል ህወሓት፣ የኦሮሞ ነጻነት ጦር፣ የሲዳማ ብሔራዊ ነጻነት ግንባር፣ የአገው ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ይገኙበታል።
ይህም ጥምረት በኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት የመመሥረት ዓላማ እንዳለው የኦሮሞ ነጻነት ጦር ቃል አቀባይ ኦዳ ታርቢ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ይህ አዲስ የተመሰረተው ጥምረት በትናንትናው ዕለት በዋሺንግተን የፊርማ ስነስርዓት ሲያካሂድ፣ የሕወሓት አማፂያንን በመወከል የተገኙት አምባሳደር ብርሃነ ገ/ክርስቶስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን በኃይል አልያም በድርድር በማስወገድ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
የአዲሱን ስብስብ መመስረት ያጣጣለው የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ፣ ከበደ ዴሲሳ፣ ከቢቢሲ ኒውስ አወር ጋር በነበራቸው ቆይታ "ደካማ የፖለቲካ ኃይል ነው" በማለት ገልጸውታል።
በተጨማሪም ሚኒስትር ዲኤታው በዚህ ጥምረት መመስረት "አለመደነቃቸውን" አመልከተዋል፤ ጥምረቱ በአገሪቱ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ድጋፍ የሌለው ነው ብለዋል።
"እነዚህ አማጺያን ቡድኖች መሠረት የላቸውም። ምንም አይነት ማኅበራዊ መሠረት የላቸውም፤ ምንም ለውጥ ሳያመጡ ላለፉት 40 ዓመታት እዚያው የቆዩ ናቸው።"
አቶ ከበደ ዴሲሳ ጨምረውም "በአገሪቱ ውስጥ የፖለቲካ መረጋጋት በሚያስፈልግበት ጊዜ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች መንግሥት ተዳክሟል፣ ሥልጣን ላይ መቆየት አይችልም ብለው ሲያስቡ ተሰባስበው ትብብር ይፈጥራሉ" በማለት ሁኔታው የተለመደ መሆኑንም ተናግረዋል።
የጥምረቱ አባላት ይህንን ስብስብ የፈጠሩት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እየተባባሰ ባለበት ወቅት ሲሆን፤ ወደፊት በአገሪቱ ይመጣል ብለው ለሚያስቡት የሽግግር መንግሥት እና ጊዜያዊ መንግሥት የመጀመሪያ ሂደት ነው ብለዋል።
ይህ ጥምረት በውስጡ ዘጠኝ ቡድኖችን ያካተተ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ጋምቤላ፣ ጉሙዝ፣ አፋር፣ ሶማሊ፣ ትግራይ፣ ኦሮሞ፣ ቅማንት፣ አገውን የፖለቲካ ቡድኖች ይወክላል ተብሏል።
ስብስቡ እነዚህን ቡድኖች ብቻ በመያዝ የሚቀጥል አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን ሌሎችም ቡድኖች እንደሚቀላቀሏቸውና ውይይትም እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ጥምረቱ ፌደራሊስት እና ኮንፌደራሊስ የሆኑ ኃይሎች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን አሁን ያለውን የአገሪቱ ሕገ መንግሥት መሰረት ባደረገው የፌደራሊዝም ሥርዓት ለመቀጠል መስማማታቸው ተነግሯል።
"በረዥም ጊዜ ሂደትም ሁላችንም የምናስበው ኮንፌደራሊስት ወደሆነ ሥርዓት መሻገር ነው። እዚያ ላይ ተስማምተናል" ብለዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር አንድ ዓመት በቆየ ጦርነት ውስጥ የሚገኘው ህወሓት፣ ከዚህ በፊት ከኦሮሞ ነጻነት ጦር ጋር በትብብር ለመንቀሳቀስ ከስምምነት መድረሳቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
ህወሓት እና ጦር መንግሥት ሸኔ የሚለው የኦሮሞ ነጻነት ጦር ባለፈው ዓመት ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ቡድኖች ተብለው መፈረጃቸው ይታወሳል።
አሁን ጥምረት እንደፈጠሩ ያስታወቁት ቡድኖቹ በቀጣይ ስለሚያከናውኑት እንቅስቃሴ በዝርዝር ያሉት ነገር የለም።












