ታዋቂው ብሪታኒያዊ የሩሲያ ሰላይ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የቀድሞው የብሪታኒያ የስለላ ተቋም ኤምአይ6 መኮንንና የቀዝቃዛው ጦርነት ድርብ ሰላይ ጆርጅ ብሌክ በ98 ዓመት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ለዘጠኝ ዓመታት ያክል የሶቪዬት ሕብረት ሰላዩ ጆርጅ ጠቃሚ መረጃዎችን ከብሪታኒያ የስለላ መሥሪያ ቤት [ኤምአይ6] እያወጣ አሳልፎ ሰጥቷል ይባልለታል።
በዚህ በምሥራቅ አውሮፓ የነበሩ ቢያንስ 40 ለሚሆኑ የኤምአይ6 ሰላዮች መጋለጥ ምክንያት ሆኗል።
በፈረንጆቹ 1960 ለንደን ውስጥ ለእሥር የተዳረገው ጆርጅ በ1966 አምልጦ ወደ ሩሲያ ገብቶ ነበር። የሩሲያ የውጭ ስለላ አገልግሎት ጆርጅ "ለሩሲያ ጥልቅ ፍቅር ያለው ሰው ነበር" ሲል ገልፆታል።
የሩሲያ መንግሥት ዜና ወኪል የአገሪቱን የውጭ ስለላ አገልግሎት ቃል አቀባይ ሰርጌ ኢቫኖቭን ጠቅሶ ነው ጆርጅ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን የዘገበው።
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን "እጅግ ላቅ ያለና ልዩ ድፍረት ያለው፤ ጠንካራ ሕይወትን የመራ" ሲሉ ጆርጅ ብሌክን ገልፀውታል።
"ለዓመታት በጠንካራ ሥራው ለምድራችን ሰላምና ፍትሃዊ እኩልነት ለማምጣት በዋጋ የማይተመን አስተዋፅዖ ያበረከተ" ሲሉ ፕሬዝደንቱ በሐዘን መግለጫ መልዕክታቸው ሰውዬውን አሞካሽተውታል።
"ይህን ዘመን አይሽሬ ሰው በልባችን ሁሌም እንዘክረዋለን" ይላል የፕሬዝደንቱ መልዕክት።
ብሌክ በ1922 በኔዘርላንዷ ሮተርዳም ከተማ ወርሃ ጥቅምት የተወለደ ሲሆን በወቅቱ መጠሪያ ስሙ ጆርጅ ቤሃር ነበር።
አባቱ ስፔናዊ አይሁድ ነበሩ። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ከእንግሊዝ ጦር ጋር አብረው ተዋግተው የብሪታኒያን ዜግነት አግኝተዋል።
ብሌክ ደግሞ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለደች ጦር ተሰልፎ ተዋግቷል። ብሪታኒያ ስር ወደምትገዛው ጂብራልታር ሸሽቶ በመሄድ የስለላ ተቋሙን እንደተቀላቀለ የሕይወት ታሪኩ ያሳያል።
በ1990 ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገው ብሌክ፤ ቢያንስ 500 ያህል ምዕራባዊያን ሰላዮችን እንደከዳ ቢናገርም 42 ሰላዮች በእኔ ምክንያት ነው የሞቱት ብዬ አላስብም ብሏል።
ብሌክ ድርብ ሰላይነቱ የተጋለጠው የፖላንድ ደኅንነት መሥሪያ ቤት መኮንን የነበረው ማይክል ጎሌኔዎስኪ ወደ ምዕራቡ ዓለም በመሸሽ የብሌክን ውሽማ ይዞ በመምጣት ምስጢሩን በማጋለጡ ነበር።
ይህን ጊዜ ነበር ብሌክ ወደ ለንደን እንዲመለስ ከተጠራ በኋላ የታሠረው። በወቅቱ በነበረው የፍረድ ሂደት አምስት ጊዜ ለሶቪዬት ሕብረት መረጃ አሳልፎ መስጠቱን አምኖ ነበር።
ሰውዬው በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የብሪታኒያ ሰላይ ሆኖ እየሠራ በርካታ መረጃዎችን አሳልፎ ሰጥቷል።
አልፎም በወቅቱ ከእሥር ቤት ማምለጥ መቻሉ ለእንግሊዝ እንደ ውርደት ነበር የተቆጠረው፤ ይላል የቢቢሲ የደኅንነት ጉዳዮች ተንታኙ ጎርደን ኮሬራ።
ብሌክ ለምን ወደ ምሥራቁ ዓለም እንዳደላና እንዴት የብሪታኒያ ሰላይ ሆኖ እንደተመረጠ የሚታወቅ ብዙ መረጃ የለም።
በአንድ ወቅት ለምን የብሪታኒያን ስለላ ድርጅት እንደከዳ ተጠይቆ "ይህንን ጉዳይ አሁን ሰው ተረዳኝ አልተረዳኝም ብዬ የምጨነቅበት ጊዜ አልፏል" ሲል መልሶ ነበር።
ሰውዬው በሩሲያ የስለላ መሥሪያ ቤት [ኬጂቢ] ውስጥ እንደ ጀግና ነው የሚቆጠረው።














