በአሜሪካ ልደት ላይ ለተፈጸመው የጅምላ ግድያ ታዳጊ ወንድማማቾችን ጨምሮ ሶስት ሰዎች ተከሰሱ

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የ20 ዓመቱ ዊልሰን ላማር ሂል

የፎቶው ባለመብት, POLICE HANDOUT

የምስሉ መግለጫ, ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የ20 ዓመቱ ዊልሰን ላማር ሂል

ከቀናት በፊት በአሜሪካ አልባማ ግዛት በ16ኛ የልደት ድግስ ላይ አራት ሰዎች ለተገደሉበትና 32 የቆሰሉበትን የጅምላ ግድያ ተከትሎ ሁለት በአስራዎቹ እድሜ ያሉ ወንድማማቾችና አንድ ሌላ ሰው በግድያ ወንጀል ተከሰዋል።

የ17ና የ16 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ወንድማማቾቹ ታይ ሬክ ማካላና ትሬቭስ ማካላ ባለፈው ማክሰኞ ታስረዋል። ሌላኛው ተጠርጣሪ የ20 ዓመቱ ዊልሰን ላማር ሂል ደግሞ ትላንት ከሰዓት ላይ ወደ እስር ቤት ተወስዷል።

እያንዳንዱ ተጠርጣሪ አራት ሰውን በግዴለሽነት በመግደል መክሰሳቸውን ፖሊስ ገልጿል።

ባለፈው ቅዳሜ ከተፈጸመው ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎቹ ሌሎች ክሶችም እንደሚመሰረትባቸው ይጠበቃል።

ሶስቱ ተጠርጣሪዎች ጥቃቱ ከተፈጸመበት ዴድቪል ከተማ በመኪና የ40 ደቂቃ ርቀት ላይ በሚገኘው ተስጊጌ በተሰኘ ስፍራ የሚኖሩ እንደሆነ ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በግዛቱ ህግ መሰረት በግድያ ወንጀል የተጠረጠረ 16 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆነው ሰው እንደ አዋቂ ሰው ይጠየቃል። ሁለቱ ታዳጊ ወንድማማቾችም በዚህ ህግ መሰረት ይዳኛሉ።

ምርመራው አሁን ገና ያልዳበረ እንደሆነ ባለስልጣናት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ባለስልጣናቱ ቀደም ብለው የጥይት ቀለሃ እንዳገኙ ተናግረው በጥቃቱ ከባድ መሳሪያ ጥቅም ላይ ስለመዋሉ ማስረጃ አልተገኘም ብለዋል።

ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አራቱ ለህይወት የሚያሰጋ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙም ፖሊስ ገልጾል።

የአልባማ ግዛት ህግ ማስከበር ኤጀንሲ በርካታ የህግ አስከባሪ ተቋማት እርዳታ ሰጥተው የተወሳሰበ ምርመራ ከተደረገ በኃላ ተጠርጣሪዎቹ እንደተያዙ ገልጿል።

እስከባለፈው ረቡዕ ድረስ ጥቃቱን እና የተጠረጠሩ ሰዎችን በተመለከተ የተሰጠው መረጃ ጥቂት ነበር።

ይህ ሁኔታ በዜጎችና መገናኛ ብዙሃን በኩል ስጋት እንደፈጠረ እረዳለሁ ሲሉ የግዛቲቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ማይክ ሴገረስት ተናግረዋል።

በቅዳሜ የልደት ድግስ ጥቃት ከሟቹ መከካል አንደኛው ታዋቂ ስፖርተኛ ሲሆን ታናሽ እህቱን አድኖ እሱ ሞቷል።

ጥቃቱ የተፈጸመበት ዴድቪል ከተማ በግርድፉ 3 ሺህ ሰው የሚኖርበት ሲሆን ከግዛቲቱ መዲና ሞንጋሞሪ ከተማ 100 ኪሎ ሜትር ርቅት ላይ የሚገኝ ነው።

የቅዳሜ ምሽቱን ጨምሮ የፈረንጆቹ አዲስ አመት ከገባ ወዲህ ብቻ በአሜሪካ አራትና ከአራት በላይ ሰዎች የተገደሉባቸው 160 የጅምላ ግድያ መፈጸሙን ገን ቫዮለንስ አርካይቭ የተባለ ተቋም ገልጿል።