ጦርነቱ በቀጠለባት ሱዳን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ካርቱምን ለቀው እየወጡ ነው

በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከዋና መዲናዋ ካርቱም እየሸሹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ጦርነቱ ለስድስተኛ ቀን ተፋፍሞ በቀጠለባት ሱዳን በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከዋና መዲናዋ ካርቱም እየሸሹ ሲሆን የውጭ አገራትም ዜጎቻቸውን ለማስወጣት እየሞከሩ ነው።

ረቡዕ ማለዳ ከፍተኛ ፍንዳታዎች እና የተኩስ ድምጽ ካርቱምን እያናወጣትም በነበረበት ወቅት በርካቶች በመኪና እንዲሁም በእግራቸው ከተማዋን ለቀው እየወጡ ታይተዋል።

የጃፓን እና የታንዛንያ ባለስልጣናት ዜጎቻቸውን ለማስወጣት ዝግጅት መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በርካቶች ከመዲናዋ መውጣትም የጀመሩት ማክሰኞ ዕለት በተፋላሚ ወገኖች ተደርሶ የነበረውን የተኩስ አቁም ስምምነት መፋረሱን ተከትሎ ነው።

የሱዳን መደበኛ ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሎች ማክሰኞ እለት ለ24 ሰዓታት የሚቆይ ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀው ነበር።

ነገር ግን በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር 12 ሰዓት ከምሽቱ ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል የተባለው የተኩስ አቁም ስምምነት የፈረሰው በደቂቃዎች ውስጥ ነው።

ተመሳሳይ አዲስ የተኩስ አቁም ስምምነት ተቀባይነት እንዳገኘ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ ረቡዕ ዕለት አስታውቆ ነበር። የሱዳን ጦርም የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደሚያከብር ቢያሳውቅም በመዲናይቱ ካርቱም ውጊያው እንደቀጠለ ነው።

በተፋላሚ ወገኖች መካከል የሚካሄደው ውጊያ በከተማዋ ማዕከል በሚገኘው የጦሩ ማዘዣ ጣቢያ ላይ ያተኮረ ሲሆን በመስሪያ ቤቱም አካባቢ ከፍተኛ ጭስ ይታያል።

በካርቱም ተቀማጭነቱን ያደረገው ጋዜጠኛ መሀመድ አላሚን ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ሬድዮ እንደተናገረው የተኩስ አቁም ስምምነት ተብሎ ቢታወጅም የተኩስ እሩምታው እንዳልቆመ ነው።

“በእርግጥ እየተካሄደ ያለው ውጊያ አሰቃቂ ነው። ተፋላሚ ወገኖች በየቦታው በዘፈቀደ እየተኮሱ ነው” የሚለው ጋዜጠኛው “እኔ ራሴ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከካርቱም እየወጡ ወደ አጎራባች ግዛቶች ለመጓዝ ሲጣደፉ አይቻለሁ” ብሏል።

አንደዳንድ ነዋሪዎች ምን እየተፈጠረ እንደሆነ ባያውቁም ሌሎች ደግሞ ቁጣቸውን ወደ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች እየወረወሩ ነው።

“ጦርነቱ በህዝብ ላይ ያነጣጠረ ነው ብለው ያስባሉ። በየጎዳናው የማገኘው ሱዳናውያንም የሚነግረኝ ይህንኑ ነው” በማለት መሃመድ ተናግሯል።

የጦርነቱ ማዕከል የሆነችው ካርቱም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ አንዱ ተግዳሮት በከተማው ውስጥ ያሉት የተበታተኑ ኃይሎች ሊሆን እንደሚችልም ጠቁሟል።

“በእነዚህ ወታደሮች መካከል የተቀናጀ ግንኙነት የለም። ውጊያው እየተካሄደ ያለው በተለያዩ አካባቢዎች ሲሆን በተበታተነና ግንኙነትም በሌለው መልኩ ነው” ሲልም ያስረዳል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው ውጊያ በአብዛኛው በከባድ መሳሪያ ድብደባ ሲሆን የአየር ጥቃቶች እምብዛም አይደሉም ተብሏል።

የዓይን እማኞች በክፍት ፒክ አፕ መኪናዎች የተጫኑ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች ከተማን እየተዘዋወሩ እንደነበር ተናግረዋል። የጦሩ ጄቶች ደግሞ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ይዞታዎች ናቸው ተብለው በሚታሰቡ ኢላማዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈጸማቸውን እኚሁ እማኞች አስረድተዋል።

ጦርነቱን ተከትሎ ባጋጠመው የነዳጅ እጥረት እና የህዝብ ማመላለሻ እጦት ምክንያት በርካቶች በእግራቸው እንዲሸሹ ተገደዋል። እነዚህ ነዋሪዎች መዳረሻቸውንም ያደረጉት ወደ መካከለኛው እና ምዕራብ ሱዳንም መሆኑም ተነግሯል።

ከመዲናይቱ የሸሹ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በከተማው ዙሪያ ባሉ ጎዳናዎች ላይ የፍተሻ ኬላዎችን እንዳዘጋጁ እና አንዳንድ ተዋጊዎችም ስልካቸውን እና የተወሰነ ገንዘብም እንደዘረፏቸውም ተናግረዋል።

በመዲናዋ ካርቱምም በርካታ ዝርፊያዎች ነበሩ ተብሏል። የካርቱም 2 አካባቢ ነዋሪዎች ማክሰኞ እለት እንደተናገሩት የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉ ሚሊሻዎች በአካካባቢው ከቤት ወደ ቤት እየተዘዋወሩ ውሃ እና ምግብ እና ውሃ እየጠየቁ ነበር ብለዋል።

ጦርነቱ እየተፋፋመ ባለበት በአሁኑ ወቅት ዜጎቻቸውን ከአገሪቱ ለማስወጣት ዝግጅት መጀመራቸውን በርካታ አገራት አስታውቀዋል።

ጃፓን መከላከያ ሰራዊቷ 60 የሚጠጉ ዜጎቿን ከሱዳን እንዴት ማስወጣት እንደሚቻል እያጤነ መሆኑንና ወታደራዊ አውሮፕላንም በተጠባባቂነት ተይዟል ብላለች።

የታንዛንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስተርጎሜና ታክስ ለፓርላማቸው እንደተናገሩት መንግሥታቸው 210 ዜጎቿን የሚያስወጣበት ሁኔታን እየገመገመ ነው።

ነገር ግን በካርቱም የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በመዲናይቱ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እርግጠኛ አለመሆን “አሜሪካ በተቀናጀ ሁኔታ ዜጎቿን ለማስወጣት እቅድ እንዳይኖራት አድርጓታል” ብለዋል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ማህበራት ፌዴሬሽን የአካባቢው ነዋሪዎች ከውጊያ ቀጣና እንዲርቁ እና በአንድ ቦታም እንዲወሰኑ ምክር እየሰጠ እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግሯል።

“በአሁን ወቅት ነዋሪዎቹን ከካርቱም ማስወጣት ፈተና እንደሆነ እውነቱን እየነገርናቸው ነው። በያላችሁበት መቆየት ለደህንነታችሁ አስተማማኝ ነውም ብለናቸዋል” ሲሉ በሱዳን የሚገኘው የተቋሙ ዋና ኃላፊ ፋሪድ አብዱልቃድር ለፎከስ ኦን አፍሪካ ተናግረዋል።

ረቡዕ ዕለት የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ዩናይትድ ኪንግድም እና 12 ሌሎች አገራት የሟቾች ቁጥር 270 መደረሱን ተናግረዋል።

ነገር ግን በርካቶች በጥይት ተመትተውና ቆስለው ወደ ሆስፒታል መድረስ አለመቻላቸውንም በማየት ትክክለኛው አኃዝ ከዚህ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በካርቱም ውስጥ የሚሰራ ታንዚል ካን የተባለ ህንዳዊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በከተማዋ የሚፈጸመው የአየር ድብደባ የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ መጣሉን ነው።

“ከማለዳ ጀምሮ በዚህ አካባቢ የሚፈጸመው የአየር ድብደባ ተባብሷል። ያለንበት ህንጻ መቼ ጥቃት እንደሚፈጸምበት አናውቅም” ሲሉም ተናግረዋል።

በካርቱም የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተጠልላና መውጫ ያጣች አንዲት ሩሲያዊት ምግብ እና ውሃ እንዳለቀ እንዲሁም መብራትም በመቋረጡ ሁኔታው ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ መምጣቱን ተናግራለች። “በከተማዋ ያለው መብራት ጦርነቱ ሲቀሰቀስ ተቋርጧል። ነገር ግን በቤተክርስቲያኗ የነበረው ጄነሬተርም ነዳጅ አልቆበታል” ብላለች።

በግጭት የተፈናቀሉ ሰዎችን የሚረዳው ግብረ ሰናይ ተቋም የኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት በአገሪቷ ያሉ ውጊያዎች በከባድ ሁኔታ በመፋፋሙ የሰብዓዊ ስራዎች ሙሉ በሙሉ መቆማቸውን አስታውቋል።

“የእርዳታ ማከማቻ መጋዘኖች ተዘርፈዋል፣ ግቢዎቻቸው ተከበዋል፣ ሰራተኞቻቸው በጠመንጃ ታግተዋል፣ ባልደረቦቻቸው የጾታ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ያለው ሁኔታ አስከፊ ነው” ሲሉም የተቋሙ ኃላፊ ጃን ኤግላንድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።