ከሦስት አስርታት በላይ የዘገየው ፍትሕ

ክራዶክ አራት በሚባል የሚታወቁት በአፓርታይድ የተገደሉት የነጻነት ታጋዮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ክራዶክ አራት በሚባል የሚታወቁት በአፓርታይድ የተገደሉት የነጻነት ታጋዮች

ሉክሃንዮ ካላታ የአባቱ የመጀመሪያ ትዝታ የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ነው።

ወቅቱ በአውሮፓውያኑ 1985 የክረምት ወቅት፣ አጥንት የሚሰብር ቅዝቃዜ የነበረበት፣ እናቱ በሐዘን የተሰበሩበት ያ ዕለት።

በደቡብ አፍሪካ ምሥራቅ ኬፕ በአነስተኛዋ ክራዶክ ከተማ ነዋሪ ነበሩ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ለቀስተኞች በባህሉ መሠረት መሬቱን እየረገጡ እና ሙሾ ያወርዱ ነበር።

መሬቱ የራደ መስሎ ተሰማው።

ለቀስተኛው የተሰበሰው ከመላው አገሪቱ ነበር።

የሉክሃንዮ አባት ፎርት ካላታን ጨምሮ ክራዶክ አራት የሚል ስያሜ ለተሰጣቸው ወጣት ነጻነት ታጋዮች ክብራቸውን ለመግለጽም ነበር የተመሙት።

ከሉክሃንዮ አባት በተጨማሪ የሌሎቹ ሦስት ፀረ አፓርታይድ ታጋዮች ቀብር በዚችው ዕለት ነበር።

አራቱ ግለሰቦች ዘረኝነትን እና ጭቆናን በመጠየፋቸው በጭካኔ የተገደሉ ሲሆን፣ በአፓርታይድ ዘመን ከተፈጸሙት እጅግ ዘግናኝ ወንጀሎች አንዱ ነውም ተብሏል።

ግድያውን ፈጽመዋል የተባሉት የፀጥታ ኃይሎች ለፍርድ አልቀረቡም። ከአፓርታይድ መወገድ በኋላ የተቋቋመው የአገሪቱ የእውነት እና ዕርቀ ሰላም ኮሚሽንም ምህረት አላደረገላቸውም።

በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን ግድያ ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች የዘረኛው የአፓርታይድ ሥርዓት ወንጀሎች እንደገና እንዲከፈቱ እንቅስቃሴዎች ተጀምሯል።

በአውሮፓውያኑ 1985 የተፈጸመው የክራዶክ አራት ግድያ በወቅቱም በመላ አገሪቱ ከፍተኛ ቁጣ የቀሰቀሰ ነበር።

በወቅቱ በዘረኛው ሥርዓት ታግዶ የነበረው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ፕሬዝዳንት ኦሊቨር ታምቦም፣ ከነበሩበት የግዞት ስፍራ መልዕክታቸውን በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለታደመው ሕዝብ ልከው ነበር።

መልዕክታቸውም በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተነቧል።

የሉክሃንዮ አባት ፎርት ካላታ ከባለቤቱ ጋር

የፎቶው ባለመብት, FORT CALATA FOUNDATION

የምስሉ መግለጫ, የሉክሃንዮ አባት ፎርት ካላታ ከባለቤቱ ጋር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የነጻነት ታጋዮቹ በተገደሉበት በዚያች ቀንም የጨቋኙ አፓርታይድ መንግሥት ፕሬዝዳንት ፒደብሊው ቦታ በምሥራቅ ኬፕ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጁ። በሚቀጥለው ዓመትም በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲሰፋ ተደረገ።

እርምጃው ዘረኛው የጥቂት ነጮች አገዛዝ እንዲያከትም የሚጠይቁ እንቅስቃሴዎችን ለማሽመድመድ ለፖሊስ እና ለፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ ሥልጣን የሰጠ ነው።

ዘረኝነትን እና ጭቆናን የሚታገሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቡድኖችን ያቀፈው የተባበሩት ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ዩዲኤፍ) የገጠር አደራጅ የነበረው እና ከክራዶክ አራት መካከል አንዱ ማቲው ጎኒዌ አንዳንድ ጊዜ በፖርት ኤልዛቤት ከተማ ስብሰባዎችን ለመካፈል ይጓዝ ነበር።

በአውሮፓውያኑ ሰኔ 27/1985 ከሌሎች ሦስት ወጣቶች ማለትም ከፎርት ክላታ፣ ስፓሮው ማክሆንቶ እና ሲሴሎ ምህላውሊ ጋር አብረው ነበሩ።

አራቱ የማኅበረሰብ መሪዎች እና ታጋዮች የሚያደርጉት የፀረ አፓርታይድ እንቅስቃሴ በፖሊስ ይታወቅ ነበር።

በፖርት ኤልዛቤት የነበራቸውንም ስብሰባ ጨርሰው ምሽት ላይ ወደ ክራዶክ ሲመለሱ ፖሊስ መንገድ ዘጋባቸው።

በኋላም የተቃጠለው አስከሬናቸው በተለያዩ ቦታዎች ተገኘ። መንግሥት በመጀመሪያ በግድያቸው ውስጥ እጄ የለም ብሎ በመካድ በአውሮፓውያኑ 1987 ባደረገው ምርመራ የተገደሉት “በማይታወቁ ሰዎች” ነው አለ።

ነገር ግን አፓርታይድ በሚገረሰስበት ዋዜማ፣ በአውሮፓውያኑ 1993 ሌላ ምርመራ ተከፈተ።

ለዚህም መነሻ የሆነው አራቱ ግለሰቦች ለዘለቄታው እንዲወገዱ ምስጢራዊ ወታደራዊ መልዕክት መላኩን አንድ ጋዜጣ መዘገቡን ተከትሎ ነው።

ይህም ምርመራ አራቱን የነጻነት ታጋዮች የገደሏቸው የፀጥታ ኃይሎች ናቸው የሚል ድምዳሜ ላይ ቢደርስም የእነዚህ የፀጥታ ኃይሉ አባላት ስም ግን አልተጠቀሰም።

የአገሪቱ የዕውነትና የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን

የፎቶው ባለመብት, AFP

ፍትሕን በመጠባበቅ ላይ

ሉክሃንዮ ካላታ አባቱ ሲገደል የሦስት ዓመቱ ህጻን ነበር።

የክራዶክ አራት ቤተሰቦች ከሰላሳ ስምንት ዓመታት በኋላ ገዳዮቹን ለፍርድ ለማቅረብ እና ፍትሕን ለማግኘት እየተጠባበቁ ነው።

የክራዶክ አራት ግድያ በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ሥርዓት ማብቃቱን ተከትሎ ሽግግሩን ሰላማዊ ለማድረግ በኮሚሽኑ ከተሰሙ በሺዎች ከሚቆጠሩ ወንጀሎች አንዱ ነው።

አስርት ዓመታት በዘለቀው የአፓርታይድ ሥርዓት የተፈጸሙ የጭካኔ ድርጊቶችና መጠነ ሰፊ ጥሰቶች ሊያስከትል የሚችለውን የበቀል ጥቃትን ለማስቀረት ነበር ኮሚሽኑ የተቋቋመው።

በይቅርታ እና በእርቅ አገሪቷ እንድትሻገር እንዲሁም መጪው ዘመንም ከቂም እና ከጥላቻ እንዲጸዳ ይሰበክ የነበረ ሲሆን፣ ይህንንም ኮሚሽን እንዲመሩ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ሊቀ ጳጳስ ዴዝሞን ቱቱን ጠየቋቸው።

ኮሚሽኑ በአፓርታይድ ዘመን የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአደባባይ በማውጣት ወንጀለኞችን፣ ምስክሮችን እና ሰለባዎችን በአንድ ላይ ሰብስቦ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ አድርጓል።

ኮሚሽኑ ሙሉ በሙሉ ወንጀላቸውን ለተናዘዙ ግለሰቦች የምህረት ዕድልን የሰጠ ሲሆን፣ ቢያንስ ለዘመዶቻቸው እና ለቤተሰቦቻቸው በሚወዷቸው ሰዎች ላይ የተፈጸመውን እንዲያውቁ በማድረግም እርማቸውን እንዲያወጡ አድርጓል።

በክራዶክ አራት ግድያ ላይ እጃቸው እንዳለበት ለኮሚሽኑ ካመኑ ሰባት የቀድሞ የፖሊስ አባላት መካከል ስድስቱ ምህረት ተነፍገዋል። የፖሊስ አባላቱ ሙሉ በሙሉ ወንጀላቸውን አልተናገሩም በሚል ነው ምህረት ያልተደረገላቸው።

ኮሚሽኑ ይህ ግድያ ለበለጠ ምርመራ እና ወደ ክስ እንዲያመራ ካደረጋቸው 300 ከሚሆኑን ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።

ነገር ግን በርካቶች የተገደሉ ቤተሰቦቻቸውን እና ወዳጆቻቸውን ፍትሕ ለማግኘት አስርት ዓመታትን ቢጠብቁም ጠብ ያለ ነገር የለም።

ሁሉም በሚባል ሁኔታ ክሶቹ አልተከፈቱም። ባለሥልጣናቱ እነዚህን ክሶች ለምን እንዳዘገይዋቸውም ሙሉ በሙሉ ግልጽ አይደለም።

በአውሮፓውያኑ 1983 ደብዛዋ የጠፋቸው የነጻነት ታጋይ የኖኩቱላ ሲሚላኔ እህት ይህንንም አስመልክተው በአውሮፓውያኑ 2015 መደበኛ ምርምራ እንዲደረግ እና ፍርድ ቤቱ ማብራሪያ እንዲሰጣቸውም ጠየቁ።

በዚህም ወቅት ነበር ቀደም ሲል ኮሚሽኑ እንዲመረመሩ የላካቸው ጉዳዮች ለምን ዘገዩ የሚለው ጥያቄ በተወሰነ መልኩ ምላሽ ለማግኘት ቻሉ።

ኮሚሽኑ እንዲመረመሩ እና ክስ እንዲመሰረትባቸው የወሰነባቸው ጉዳዮችን የኤኤንሲ መንግሥት ለማደናቀፍ ሞክሯል በማለት የዐቃቤ ሕግ የቀድሞ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል የሲሚላኔ ጉዳይ አንዱ ነው።

ለዚህም ምክንያቱ በአንዳንዶቹ ምርመራ ላይ የአፓርታይድን ሥርዓት በሚታገሉበት ወቅት በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ ተሳትፈው ሊሆን ይችላል በሚል የገዢው ኤኤንሲ አባላት ክስ እንዲመሰረትባቸው ሊያነሳሳ ይችላል የሚል ስጋት ስላደረባቸው ነው ተብሏል።

ቢቢሲ በዚህ ጉዳይ ላይ የደቡብ አፍሪካን መንግሥት ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

ፖለቲካዊ ጣልቃገብነት እንዲሁም ከእነዚህ ክሶች መዘግየት ጋር ተያይዞ ከጀርባ እየተሰጡ ስላሉ ምክንያቶች ምንም ዓይነት ይፋዊ ምርመራ የለም።

ሆኖም በርካታ ዓመታትን ሲጠብቁ ለነበሩ ፍትህ ፈላጊ ቤተሰቦች እየተሰጠ ያለውን ምክንያት “ስንጠረጥረው የነበረ ነው” ይላሉ።

ሲሚላኔ የኤኤንሲ ወታደራዊ ክንፍ የነበረው ኡምኮንቶ ዌ ሲዝዌ አባል የነበረች ስትሆን፣ ገና የ21 ዓመት ወጣት ነበረች።

በአውሮፓውያኑ 1983 በጆሃንስበርግ ከሚገኝ ከመሬት በታች የመኪና ማቆሚያ ላይ ታፍና ተወሰደች።

ለሳምንታት ያህልም እንዳሰቃይዋት የአፓርታይድ ወቅት የፖሊስ መኮንኖች ለኮሚሽኑ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ሆኖም አስከሬኗ እስካሁን አልተገኘም።

የትብብር አስተዳደር እናባህላዊ ጉዳዮች ሚኒስትር፣ የሲሚላኔ እህት ቴምቢ ንካዲሜንግ ታላቅ እህታቸውን በህልማቸው እንደሚያዩዋት ተስፋ ያደርጋሉ።

ሲሚላኔን በደንብ አያስታውሷትም። ትዝታዋ ቢደበዝዝም ምግብ ማብሰል እንዴት ትወድ እንደነበር ያስታውሳሉ። ቤተሰቦቿን ሁሉ በጠረጴዛ ላይ አስቀምጣ የተለያየ ዓይነት ምግብ ነበር የምታዘጋጅላቸው።

“እናቴ እንዲህ ስትል አስታውሳለሁ ‘አንቺ ታበስያለሽ ነገር ግን አትበይም’ ትላታላች። ነገር ግን ጣፋጭ ትወድ ነበር። በጣም ጣፋጭ ትወድ ነበር” ይላሉ።

ቴምቢ እህታቸው ለዘጠነኛ ዓመታቸው በስጦታ የገዛችላቸው ነጭ ፓላዞ የተሰኘው ሱሪ በአሁኑ ወቅት አለመኖሩ ይጸጽታቸዋል። ያ የመጨረሻው ስጦታዋ ነበር፤ ከወራት በኋላ የእህታቸው ደብዛዋ ጠፋ።

ነገር ግን ለቤተሰቡ አጠቃላይ ህመም የሆነባቸው ምርመራው እና የፍርድ ሂደቱ የፈጀው ጊዜ ነው። እህቷን በመግደል ከተከሰሱት አራት የቀድሞ የደኅንነት ፖሊስ አባላት መካከል ሁለቱ ሕይወታቸው አልፏል። የቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ የፍርድ ሂደታቸው መቼ እንደሚታይ ግልጽ አይደለም።

ከተከሰሱት አራት ፖሊሶች መካከል ሦስቱ ሲሚላኔን በማሰቃያቸው ምህረት እንዲደረግላቸው ለኮሚሽኑ ቢያመለክቱም ውድቅ ተደርጎባቸዋል። ለግድያዋ ግን ማንም ምህረት የጠየቀ የለም።

በ21 ዓመቷ ደብዛዋ የጠፋው የነጻነት ታጋይዋ ኖኩቱላ ሲሚላኔ

የፎቶው ባለመብት, FAMILY OF NOKUTHULA SIMELANE

የምስሉ መግለጫ, በ21 ዓመቷ ደብዛዋ የጠፋው የነጻነት ታጋይዋ ኖኩቱላ ሲሚላኔ

‘ትልቁ ኪሳራ’

በአውሮፓውያኑ 1971 በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለ ሕይወቱ ያለፈው የፀረ አፓርታይድ የመብት ታጋዩ የአህመድ ቲሞል ምርመራ በ2017 እንደገና ተከፍቷል። ይህም ሁኔታ ትልቅ ለውጥ ያመጣ እንደሆነ የኮሚሽኑ ሥራ አስኪያጅ ካታርዚና ዙዱንቺክ ያስረዳሉ።

አንድ የቀድሞ የደኅንነት ፖሊስ በቲሞል ግድያ ቢከሰስም ለፍረድ ከመቅረቡ በፊት በዓመቱ ህይወቱ አልፏል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ የብሔራዊ ዐቃቤ ሕግ ባለሥልጣን የቀድሞ የኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩትን አቶ ዱሚሳ ንፀቤዛን ለምርም እና ለክሰ የተመሩትን የአፓርታይድ ዘመን ጉዳዮች እንዲገመግሙ መሾማቸው የተጎጂ ቤተሰቦች በመልካም አይተውታል።

እርምጃው ያልተገባ የፖለቲካ ተፅእኖን ለመከላከል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተጀመረው ጥረት አካል ነው።

ነገር ግን ቲምቤ በበኩላቸው ኮሚሽኑ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነትን ሙሉ በሙሉ ማየት እንደማይችል በማመን እየቀረቡ ያሉ የጣልቃ ገብነት ቅሬታዎችን የሚመለከት ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

አብዛኞቹ ወንጀለኞች እና ቁልፍ ምስክሮች በመሞታቸው ጉዳዮቹን ለመርመር እና ክስ ለመመስረት ያለው ተስፋ የደበዘዘ ነው።

ነገር ግን ሉክሃንዮ የአባቱን ጉዳይ መከታተሉን እንደማያቆም ይናገራል።

“ከ38 ዓመታት በኋላም ቢሆን ወደ መቃብሩ ሄጄ አባቴ አሁን በመጨረሻ በሰላም ማረፍ እንደምትችል ተስፋ አደርጋለሁ። ለዚህ ያበቁህ ገዳዮችህ ተጠያቂ ሆነዋል እላለሁ።”

ቲምቤ እና ቤተቦቹ አሁን የሚፈልጉት እርማቸውን አውጥተው ወደፊት መቀጠል ነው። አባታቸው እና ወንድማቸው የሲሚላኔን መቀበር ሳያዩ አልፈዋል፣ ነገር ግን እናታቸው አስከሬኗ ተገኝቶ እንደሚቀብሯት ተስፋ ያደርጋሉ።

“በአንድ ወቅት እህት ነበረኝ። ለእናቴ ዛሬ ያለችበትን የማታውቀው ልጅ ነበረቻት። መቃብሯን መጎብኘት አትችልም። መቅበርም አልቻለችም።”

“ትልቁ ኪሳራ ነው ብዬ የማስበው፣ ሰዎች ከእንደዚህ አይነት ጥልቅ ህመም ጋር መሞታቸው ነው።”