የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት የጸረ አፓርታይድ ታጋዩን የገደለው ቀኝ አክራሪ እንዲፈታ ወሰነ

የጸረ አፓርታይድ ነጻነት ታጋይ የሆነውን ክሪስ ሃኒን የገደለው የቀኝ አክራሪ ታጣቂ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የጸረ አፓርታይድ ነጻነት ታጋይ የሆነውን ክሪስ ሃኒን የገደለው የቀኝ አክራሪ ታጣቂ ከእስር እንዲፈታ ወሰነ።

በበርካታ ደቡብ አፍሪካውያን በተለይም ወጣቶች ዘንድ እንደ ጀግና የሚታየው ክሪስ ሃኒ የተገደለው በአውሮፓውያኑ 1993 ነበር።

ጃንሰስ ዋሉስ “ከበድ ያለ ወንጀል” ቢፈጽምም” ነገር ግን እንደ ሌሎች እስረኞች በአመክሮ የመውጣት መብት እንዳለው ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ይህንን ውሳኔም የክሪስ ሃኒ ባለቤት ሊምፖ “በእውነት ዲያብሎሳዊ” ነው ስትል አውግዛዋለች።

ለሶስት አስርት ዓመታት በእስር የቆየው የ69 ዓመቱ ዋሉስ ነጻነቱን ለማግኘት ያደረጋቸውን ሙከራዎች እሷም ትሁን የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በብርቱ ሲቃወማቸው ነበር።

ዋሉስ ክሪስ ሃኒን የገደለው የደቡብ አፍሪካ አናሳና ጨቋኝ አገዛዝ ተገርስሶ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር የሚደረገው ሙከራ እንዳይሳካ በሚል ነበር ።

ዋናው ዳኛ ሬይ ዞንዶ የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቱን ወክለው በሰጡት ብይን ዋሉስ ክሪስ ሃኒን በጭካኔ ከገደለ በኋላ አገሪቷ ወደ ርስ በርስ ጦርነት ለመግባት ተቃርባ ነበር ብለዋል።

 ክሪስ ሃኒ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ነገር ግን የፍትህ ሚኒስትሩ ሮናልድ ላሞላ በአመክሮ እንዳይወጣ መወሰናቸው “ምክንያታዊነት የጎደለው ነው" እና በ10 ቀናት ውስጥ ሊፈታ ይገባል ብለዋል ዋና ዳኛው።

አክለውም “ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል ነው የሚለው መርሆ አፓርታይድን ለተዋጉት ብቻ ሳይሆን በንቃት ለሚደግፉት ጭምር ነው" ሲሉ መናገራቸውን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የፍትህ አገልግሎት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ክሪስፒን ፒሪ “ፍርድ ቤቱ ወስኗል እናም ተግባራዊ ማድረግ አለብን" ማለታቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል.

ክሪስ ሃኒ የደቡብ አፍሪካ ኮሚዩኒስት ፓርቲ (ኤስኤሲፒ) መሪ እና በደቡብ አፍሪካ ለነጻነት የታገለው እና ስልጣን የተቆጣጠረው የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ወታደራዊ ክንፍ ከፍተኛ አመራር ነበር።

ክሪስ ሃኒን በመግደል ተባባሪ የነበረው ክሊቭ ደርቢ ሌዊስ በአውሮፓውያኑ 2015 መፈታቱ ይታወሳል።

ክሊቭ ክሪስ ሃኒን የሚገደልበትን ሽጉጥ ለዋሉስ በመስጠትም ወንጀል ነበር የተፈረደበት። ግለሰቡ በተፈታ በአመቱ በ80 አመቱ ህይወቱ አልፏል።

ዋሉስ የፖሊሽ ስደተኛ ሲሆን በአውሮፓውያኑ 2017 ደቡብ አፍሪካ የሰጠችውን ዜግነት ነጥቃዋለች። አንዳንዶቹም ከሃገር እንዲባረር ጠይቀዋል።

የደቡብ አፍሪካ ኮሚዩኒስት ፓርቲ የክሪስ ሃኒ ግድያ “በቤተሰቡ፣ በፓርቲው እና በሰራተኛው መደብ ላይ ከፍተኛ ክፍተትን የፈጠረ ነው” ብሏል።

“ብያኔው የነበረው ቁስል ላይ እንዲያመረቅዝ የሚያደርግ ነው ብሏል።

ዋሉስ በእስር ቤትም ቆይታው ለወጣት ፖላንድ አክራሪና ጭፍን ብሄርተኞች እና ፋሺስቶች ምልክት መሆን ችሏል።