ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ከነጮች ባነሰ ሁኔታ የሚኖሩባት ደቡብ አፍሪካ

በደቡብ አፍሪካ ደርባን የሚገኝ የጎልፍ መጫወቻ አጠገብ የሚገኝ የጎስቋሎች መንደር ከአየር ሲታይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እኤአ በ2018 ከአየር ላይ የተነሳው ምስል በደቡብ አፍሪካ ሀብታምና ደሃ እንዴት ተለያይተው እንደሚኖሩ ያሳየ ነበር

ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ከነጭ አቻዎቻቸው በሦስት እጥፍ ያነሰ ገቢ እንደሚያገኙ አንድ ጥናት ይፋ አደረገ።

ጥናቱ በደቡብ አፍሪካውያን መካከል ያለውን ያልተመጣጠነ ገቢን የተመለከተ ሲሆን፤ ከአገሪቱ 80 በመቶ የሚሆኑት ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የወር ገቢያቸው በአማካኝ 13000 ብር ገደማ ሲሆን፤ የነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ግን 38 ሺህ ብር አካባቢ እንደሆነ ተቀምጧል።

ጥናቱ አክሎም እንዴት የተለያዩ ብሔሮች በማኅበራዊ መደብ ውስጥ እንደተቀመጡ አሳይቷል።

ጥናቱ በአገሪቱ የስታስቲክስ መሥሪያ ቤት እኤአ ከ2002 እስከ 2017 ድረስ የተሰበሰበን መረጃ የተጠቀመ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፤ ይህም ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን በሥራ ማጣት ክፉኛ እንደሚቸገሩ ያሳያል።

እነዚህ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን የግል የሕክምና ተቋማትን መጎብኘት፣ መጠለያና መብራት የማግኘት ጉዳይም ቅንጦት እንደሆነባቸው ጥናቱ ያመለክታል።

ጥናቱ፤ የደቡብ አፍሪካ ከተሞችን ከዓለማችን አገራት መካከል ከፍተኛ ያልተመጣጠነ ገቢ ያላቸው ዜጎች የሚኖሩባት አገር አድርጓታል።

ጥናቱ ለበርካታ ዓመታት በአገሪቱ አከራካሪ ለነበረው ጉዳይ ጠቅለል ያለ ምልከታን በማስቀመጥ መረጃን የሰጠ መሆኑ ተነግሮለታል።

በብሔሮች መካከል ከፍተኛ የሆነ የሀብት ልዩነት እንዲኖር ካደረኩጉ ምክንያቶች አንዱ የአፓርታይድ ውጤት ነው የተባለ ሲሆን፣ አፓርታይድ በቁጥር አነስተኛ የሆኑት ነጮች አገሪቱ ያላትን ውስን ሀብት ያለስስት እንዲጠቀሙና ሀብት እንዲያካብቱ አድርጓል ተብሏል።