የውጭ አገራት ዜጎች ከካርቱም ሊወጡ ነው- የሱዳን ጦር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሳምንት የደፈነው የሱዳን ጦርነት ተፋፍሞ ከመቀጠሉ ጋር ተያይዞ የውጭ አገራት ዜጎቻቸውን ከመዲናዋ ካርቱም ሊያስወጡ ነው።
የአሜሪካ፣ የዩናይትድ ኪንግደም፣ የፈረንሳይ እና የቻይና ዲፕሎማቶች እና ዜጎች በወታደራዊ አውሮፕላኖች ከካርቱም እንዲወጡ ሊደረግ መሆኑንም የሱዳን ጦር ባወጣው መግለጫው አስታውቋል።
የሱዳን ጦር አዛዥ አብደል ፈታህ አል ቡርሃን የውጭ አገር ዜጎቹ “በሚቀጥሉት ሰአታት ውስጥ” የሚወጡበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እና ለማስተባበር መስማማታቸውን መግለጫው ጠቅሷል።
ሳዑዲ አረቢያም በሱዳን ያሉ ዜጎቿን “ከወንድም” ሱዳን አገር ልታስወጣ በዝግጅ ላይ መሆኗን አስታውቃለች።
የሳዑዲ አረቢያ ዲፕሎማቶች ሱዳንን ለቀው መውጣታቸውን የሱዳን ጦር አስታውቋል።
የጦሩ መግለጫ እንዳስታወቀው የዩናይትድ ኪንግደም፣ የአሜሪካ፣ የፈረንሳይ እና የቻይና ዲፕሎማቶች በወታደራዊ አውሮፕላኖች ከመዲናዋ ካርቱም እንዲወጡ ይደረጋል ብሏል።
ቀደም ብሎ የአውሮፓ ህብረት ዜጎቹን ከካርቱም ለማስወጣት እቅድ መንደፉን አስታውቆ ነበር።
አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን እንዳሉ የህብረቱን አባል አገራት ዜጎችም ለማስወጣት የተለያዩ አማራጮችን እያጤኑ እንደሚገኙም ነው።
በካርቱም ወደ 1 ሺህ 500 የሚጠጉ የህብረቱ አባል አገራት ዜጎች ይገኛሉ።
ሰባት የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት በሱዳን ተልዕኮ አላቸው።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አና ባየርቦኮክ ዜጎችን ለማስወጣት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መደረስ ቀዳሚ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
ግጭቱ ከተከሰተበት ሚያዝያ 7፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ የካርቱም አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንደተዘጋ ይገኛል።
አሜሪካ የዲፕሎማቲክ ሰራተኞች ካርቱምን ለቀው እንዲወጡ ለማድረግ ውሳኔ ላይ እንዳልደረሰች ገልጻ፤ ባለስልጣናቱ ከኤምባሲው ሰራተኞች ውጭ ያሉ ሌሎች የአሜሪካ ዜጎች ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ በራሳቸው እንዲዘጋጁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ነበር።
ባለስልጣናቱ ይህንን ይበሉ እንጂ አሜሪካ ዜጎቿን ለማስወጣት በዝግጅት ላይ መሆኑን ቀደም ብለው የወጡ ዘገባዎች አሳይተዋል።
የአሜሪካ ጦር የኤምባሲውን ሰራተኞች ከካርቱም ለማስወጣት እየተዘጋጀ መሆኑንም ተዘግቧል።
የአሜሪካ ወታደሮች በጂቡቲ ወደሚገኝ ወታደራዊ ካምፕ እየተወሰዱ እንደሆነም የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል።
አርብ እለት የአሜሪካ የጦር ሰራዊት ጀነራል ማርክ ሚሌይ ከጦር አዛዡ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን ጋር በሱዳን ስላሉት አሜሪካውያን ደህንነት ተወያይተዋል።
ፔንታጎን በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
ደቡብ ኮሪያ በበኩሏ ዜጎቿን ከሱዳን ለማስወጣት ወታደራዊ አውሮፕላን እንደምትልክ ማስታወቋን ዮንሃፕ የተሰኘው የዜና አገልግሎት ዘግቧል።
በርካታ ወታደሮች እና የህክምና ባለሙያዎችን የያዘው አውሮፕላን ወደ ሱዳን እንደሚያመራም ሚዲያው የጸጥታ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
25 የደቡብ ኮሪያ ዜጎች በሱዳን ውስጥ ያሉ ሲሆን እስካሁንም የደረሰባቸው ጉዳት እንደሌለም ይኸው ዘገባ አስነብቧል።
ጃፓን መከላከያ ሰራዊቷ 60 የሚጠጉ ዜጎቿን ከሱዳን እንዴት ማስወጣት እንደሚቻል እያጤነ መሆኑንና ወታደራዊ አውሮፕላንም በተጠባባቂነት ተይዟል ብላለች።
የታንዛንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስተርጎሜና ታክስ ለፓርላማቸው እንደተናገሩት መንግሥታቸው 210 ዜጎቿን የሚያስወጣበት ሁኔታን እየገመገመ ነው።
በመዲናዋ ካርቱም ውጊያው ተፋፍሞ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት የውጭ አገራት ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማስወጣት ፈታኝ ሆኖባቸዋል ተብሏል።
ከሳምንት በፊት በተቀሰቀሰው በዚህ ጦርነት ቢያንስ 400 ሰዎች ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩም ቆስለዋል።
በተቀናቃኝ ጎራ ተሰልፈው ያሉትና በስልጣን እየተሻኮቱ ያሉት የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል አዛዥ ጄነራል መሃመድ ሐምዳን ዳጋሎ በሱዳን እጣ ፈንታ ላይ እየተፋለሙ ይገኛሉ።












