ሲፈን ሐሰን በመጀመሪያ የማራቶን ተሳትፎዋ የለንደን ማራቶንን አሸነፈች

ሲፈን ሐሰን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሲፈን ሐሰን በመጀመሪያ የማራቶን ተሳትፎዋ የለንደን ማራቶንን ማሸነፍ ቻለች።

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ እና ለኔዘርላንድስ የምትሮጠው ሲፈን ሐሰን በአትሌቲክስ መድረክ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠውን የለንደን ማራቶንን በ 2፡18፡33 ሰዓት ማሸነፍ ችላለች።

በወንዶች ማራቶን ደግሞ ኬንያዊው ኬልቪን ኪፕተም አሸናፊ ሆኗል። ከጥቂት ወራት በፊት የቫሌንሺያ ማራቶንን ያሸነፈው ኬንያዊው 2፡01፡25 በሆነ ሰዓት ውድድሩን በበላይነት ጨርሷል።

በሴቶቹ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ መገርቱ አለሙ ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀች ሲሆን ውድድሩን ልታሸንፍ ትችላለች ተብላ ትልቅ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው የቶኪዮ ኦሊምፒክ የማራቶን አሸናፊ ፒርስ ጄፕቺርቺር በሦስተኛ ደረጃ አጠናቃለች።

በወንዶች ኢትዮጵያውያኑ የኬንያ አትሌቶችን ተከትለው ከ3-5ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ጨርሰዋል። ታምራት ቶላ፣ ልዑል ገ/ስላሴ እና ሴይፉ ቱራ እንደ ቅድመ ተከተላቸው ከ3ኛ እስከ 5ኛ ወጥተዋል።

“ትልቁ የሕይወቷ ስኬት”

የቢቢሲው አትሌቲክስ ተንታኝ አንድሩ ኮተር፤ “እስካሁን ካየኋቸው አስደናቂው የማራቶን ድል” ሲል የሲፈንን ድል ገልጾታል።

በውድድሩ መጀመሪያ አካባቢ ሲፈን የሕመም ምልክት እያሳያች ሩጫዋን እያቆመች ሰውነቷን ለማፍታት ስትሞክር ታይታ ነበር።

በረመዳን ወቅት ጾም ላይ ሆና ልምምድ ስታደርግ የነበረችው ሲፈን፤ በመጀመሪያ የማራቶን ውድድሯ ታሸንፋለች ተብሎ አልተጠብቅም ነበር።

አንድሩ ኮተር አትሌቷ ከዚህ ቀደም የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያሸነፈች ቢሆንም፤ “ይህ ትልቁ የሕይወቷ ስኬት መሆን አለበት” ብሏል።

ሌላኛው የቢቢሲ የማራቶን ተንታኝ ስቲቨን ክራም ደግሞ የኦሊምፒክ የ5ሺህ እና 10ሺህ ሜትር ሻምፒዮኗ ሲፈን ሐሰን የለንደን ማራቶንን በማሸነፍ “ማንም ያልጠበቀውን አድርጋለች” ብሏል።

ሲፈን ከውድድሩ በፊት በሰጠችው አስተያየት፤ “በአሁኑ ሰዓት ሌላ የማስበው ምንም ነገር የለም። ዓላማዬ ከማራቶን ጋር መተዋወቅ ነው። መማር እፈልጋለሁ” የሚል ነበር ነበር።

የባለፈው ዓመት የለንድን ማራቶን ውድድር አሸናፊዋ ያለምዘርፍ የኋላው ክብሯን ለማስጠበቅ ጥሩ ተፎካካሪ ሆና ስትሮጥ ብትቆይም ውድድሯን በአምስተኛ ደረጃ አጠናቃለች። አልማዝ አያና 7ኛ ሆና ስትጨርስ ታዱ ተሾመ ደግሞ 8ኛ ደረጃን ይዛ ጨርሳለች።

በወንዶቹ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኬንያዊው የኒው ዮርክ ሲቲ ማራቶን አሸናፊ ኬንያዊ ጂዮፌሪ ካምዎሮሮ ነው።

የወንዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሲፈን ከውድድሩ በኋላ ለቢቢሲ በሰጠችው አስተያየት፤ "በጣም አስደናቂ ነበር። ማራቶንን ጨርሳለሁ ብዬ አስብዬ አላውቅም፤ ይህው ግን ማራቶን አሸነፍኩ!"

"ግራ ዳልዬ አካባቢ ችግር ገጥሞኝ መቆም ግድ ሆኖብኝ ነበር። ግን እየተሻለኝ መጣ። 20ኛ ኪሎ ሜትር ላይ ውድድሩን መጨረስ እንደምችል ገባኝ ምክንያቱም ያን ያክል አልደከመኝም ነበር። አሸንፋለሁ ብዬ አላሰብኩም። ማሸነፍን አለማሰቤ ጥሩ ሆኖልኛል ብዬ አስባለሁ" ብላለች።