በሱዳኑ ግጭት የግብጽ አቋም ምንድን ነው?

አል-ቡርሐን እና አል-ሲሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሱዳን የበስተሰሜን ጎረቤት አገር ግብጽ በካርቱም ያለውን ወታደራዊ ግጭትን በአንክሮ እየተከታተለች ነው። እስካሁን ግን ግልጽ አቋም የያዘች አይመስልም።

የተራዘመ ውጊያ በግብጽ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አያጠያይቅም። ነገር ግን ግብጽ ወደየቱ ላዘንብል በሚለው ውዝግብ ውስጥ የገባች ይመስላል።

ግብጽ ከሁለቱ ተዋጊ ቡድኖች መካከል የሚቀርባት የሱዳን ጦር ነው። በመሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔምቲ) የሚመራው ሌላኛው የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይል በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ይደገፋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ደግሞ የግብጽ ዋነኛ የፋይናንስ ደጋፊ ነው።

በግብጽ ጦርነትን ወይም ድህነት የሸሹ አምስት ሚሊዮን ገደማ ሱዳናውያን ይኖራሉ።

ሁለቱ አገራት ለንግድም ይሁን ለኑሮ ነጻ የሰዎች ዝውውር ስምምነት አላቸው።

በቅርብ ዓመታት ወደ ግብጽ የሚጓዙ ሱዳናውያን ስደተኞች ቁጥር ጨምሯል።

በካይሮ መደብሮች፣ በምግብ ቤቶች፣ በሰዎች ቤት ውስጥም ሱዳናውያን ሠራተኞች ማየት የተለመደ ነው።

አምና የሱዳናውያን ስደተኞች ቁጥር ከመጨመሩ የተነሳ ሁለት የአውቶብስ መቆሚያዎች ካይሮ ተዘጋጅተዋል። ግብጻውያን አውቶብስ ማቆሚያዎቹን “የሱዳን አየር ማረፊያ” ሲሉ በስላቅ ይጠሯቸዋል።

አንድ ሱዳናዊ ለቢቢሲ እንደተናገረው፣ 800 የግብጽ ፓውንድ (26 የአሜሪካ ዶላር) ከፍሎ በሦስት ቀን ካርቱም መግባት ይቻላል።

በካርቱምና ካይሮ መካከል ቢያንስ 25 አውቶብሶች በየዕለቱ ይጓጓዛሉ።

ግጭቱ ካልተገታ ቁጥሩ ከዚህም ሊጨምር ይችላል።

ግብጽ የሱዳን ነገር የሚያሳስባት ለዚህ ብቻ አይደለም።

የካርቱም መንግሥት ከተዳከመ ወይም ተገዳዳሪ የፖለቲካ ኃይል ከመጣ ተጽዕኖው ከካርቱም ካይሮ ይደርሳል።

ግብጽ ሱዳንን እንደ አጋር ከምታይባቸው ምክንያቶች አንዱ ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገብበት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ይጠቀሳል።

ግብጽ የግድቡ ግንባታ የዐባይን የውሃ መጠን በመገደብ ለሕልውናዬ ያሰጋል ትላለች።

የፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ መንግሥት ስለ ሱዳኑ ቀውስ መፍትሄ ለመስጠት እያታገለ ነው።

የተወሰኑ የግብጽ ወታደሮች በሱዳን ፈጥሮ ደራሽ ልዩ ኃይል እንደተያዙ መገለጹ ይታወሳል።

ግብጽ ከዚህ ክስተት ሁለት ቀናት በኋላ በግጭቱ የየትኛውም ወገን ደጋፊ እንዳልሆነች ገልጻ፣ የማሸማገል ጥያቄ አቅርባለች።

ግብጽ ገለልተኛ ናት የሚለው ያልተዋጠላቸው አሉ።

ግብጽ ከሱዳን ጦር ጋር ቅርበት እንዳላት ይታወቃል። በሱዳን የተያዙት ወታደሮቿም ከጦሩ ጋር የጋራ ልምምድ ሲያደርጉ ነበር።

ግብጽ ግን ቅርበቷ ለማን እንደሆነ በይፋ አትናገርም።

ይህም የሱዳን የፖለቲካ ዐውድ ከመለወጡ ጋር ይያያዛል። በተጨማሪም በሁለቱም አገራት አብዮት ተካሂዷል።

ሆስኒ ሙባረክ እአአ በ2011 ከሥልጣናቸው ሲወገዱ ኦማር አል-በሽር ደግሞ በ2019 ተገልብጠዋል።

በሁለቱም መፈንቅለ መንግሥቶች ወታደራዊ ኃይል ሚና ተጫውቷል።

የሱዳን ውጊያ

የፎቶው ባለመብት, AFP

በግብጽ ጦሩ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ማምራቱን ያዩ የሱዳን የፖለቲካ ልሂቃል ይሄው የግብጽ ጦር የሱዳን ጦር ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርግ ያበረታታል የሚል ስጋት አላቸው።

የሱዳን ጦር የሲቪል ሽግግሩን እንደማያስቆም በአደባባይ ቢናገርም እአአ በ2019 የተጀመረው አብዮት አቀጣጣይ የሆነው ‘ፍሪደም ፎር ቼንጅ’ ይሄንን አያምንም። የግብጽን ጣልቃ ገብነትም ይፈራል።

ግብጽ የምጣኔ ሀብት ቀውስ ገጥሞታል። መገበያያ ገንዘቧ ከዶላር አንጻር ከግማሽ በላይ ዋጋውን አጥቷል።

የኑሮ ውድነት እና ድህነት ተባብሷል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በዋነኛነት ግብጽን በገንዘብ ሲደግፍ በሱዳን ግጭት ደግሞ የፈጥኖ ደራሽ ልዩ ኃይሉን ይደግፋል።

ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በተቃራኒው መቆም ለግብጽ አስጊ ነው።

በየትኛውም ወገን ቢሆን ግጭቱን በኃይል ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ከግብጽ ብሔራዊ ፍላጎት ይጻረራል።

በሊቢያ የእርስ በእርስ ጦርነት ስኬታማ ያልሆኑት ጀነራል ከሊፋ ሐፍጣርን የደገፈችው ግብጽ ከቀደመ ስህተቷ የተማረች ይመስላል።

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነቢል ፋሕሚ ለቢቢሲ እንደገለጹት “የግብጽን ብሔራዊ ፍላጎት ከግምት በማስገባት በሱዳን ደኅንነት እና መረጋጋት እንዲኖር” ይሻሉ።

“መረጋጋት” የሚለው አገላለጽ ግብጽን ጨምሮ በብዙ አምባገነን መንግሥታት ተቃዋሚዎችን ለማፈን ይውላል።

ሱዳናውያን ፖለቲከኞች የበስተሰሜን ጎረቤታቸው ግብጽ “ብሔራዊ ጥቅሜ” ስትል የሚሰጉትም ለዚሁ ነው።