የሩሲያው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን (ቫግነር) በሱዳን ምን እየሠራ ነው?

ቫግነር ማን ነው ከሚለው እንጀምር?
ቫግነር እራሱን ‘የግል የጦር ኩባንያ’ ብሎ ይገልጻል። እውነቱ ግን ለሩሲያ መንግሥት ቅርበት ያለው ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን ነው። መሥራቹ የቀድሞው ወንጀለኛ የአሁኑ የቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ወዳጅ የሆነው ይቭጌኒ ፕሪጎዚን ነው።
ቡድኑ የግል ኩባንያ ነው። ዋና ተግባሩ ደግሞ ተቀጥሮ መዋጋት ነው። በአፍሪካ ከ10 ባላነሱ አገራት ውስጥ ተሰማርቷል። በዩክሬን ጦርነት ከሩሲያ ጎን በመሰለፍ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው።
ከሰሞኑ ደግሞ የሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ ስሙ እየተነሳ ነው።
ለመሆኑ ቫግነር በሱዳን አለ? ካለስ ምን እየሠራ ነው?
የወርቅ ማዕድን እና ቫግነር
ቢቢሲ የቫግነር ቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን በዚህ ወቅት በሱዳን እንዳለ በተጨባጭ ማረጋገጥ አልቻለም።
ይሁንና ቫግነር ከሱዳን የእርስ በርስ ግጭቱ ቀደም ብሎ በሱዳን ውስጥ እንደነበረ እና ተሳትፎውም በአውሮፓ ኅብረት እንዲሁም በአሜሪካን መንግሥት ማዕቀቦች ዒላማ እንደነበር ተጠቅሷል።
በፈረንጆች 2017 የሱዳን ፕሬዝዳንት የዛሬው እስረኛ ኦማር ሐሰን አልበሽር ሞስኮን ጉብኝተው ነበር።
በዚያ ቆይታቸው ብዙ ስምምነት ተፈራርመዋል። ለሩሲያ ባሕር ኃይል የጦር ሰፍር በቀይ ባሕር አቅራቢያ በፖርት ሱዳን ለመስጠት መፈረማቸው አንዱና ዋንኛው ነው።
ኤም ለሚባል የሩሲያ ኩባንያ የወርቅ ማዕድን ልማት ፍቃድም ለመስጠትም ፈርመዋል አል በሽር።
ሱዳን በአፍሪካ ሦስተኛዋ ትልቅ የወርቅ አምራች አገር ናት። አሜሪካ እንደምትለው ኤም ኢንቨስትመንት እና እህት ኩባንያው ሜሮዌ ጎልድ ከቫግነር ቡድን ጋር እጅና ጓንት ሆነው ነው የሚሠሩት።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት የቀድሞ ዋና ፀሐፊ ስቴቨን ሙንቺን ከዚህ ቀደም “የቫግነሩ አለቃ ፕሪጎዚን እና አጋሮቹ የሱዳንን የተፈጥሮ ሃብት እየዛቁት ነው” ሲሉ ተናግረው ነበር።
ኤም እና ሜሮዌ ጎልድ አሜሪካ ማዕቀብ ጥላባቸው ነው ያሉት።
የቫግነሩ አለቃ ፕሪጎዚን “ሱዳን ውስጥ ምንም እጃችን የለበትም" ሲል ያስተባብላል።
በአንድ ወቅት ሲኤንኤን ቴሌቪዥን በሠራው ዘገባ ቫግነር ወርቅ ከሱዳን ወደ ሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ እንደሚያስተላልፍ አጋልጦ ነበር። ይህም ከሱዳን ባለሥልጣናት ዕውቅና ውጪ የሆነ ነው።
ዴይሊ ቴሌግራፍ እንደጻፈው ደግሞ የወርቅ ክምችቱ ከአገር የሚወጣው ወታደራዊ አየር ማረፊዎችን በመጠቀም ነው።

ቫግነር በሱዳን ሌላ ምን ይሠራል?
ቫግነር ከ2017 ጀምሮ በሱዳን በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው።
ከእነዚህ መካከል የቫግነር አባላት ወታደሮችን ሲያሰለጥኑ የሚያሳዩ ምሥሎች ይገኙበታል። ወታደሮች ተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ሲመሩ የታየበት ምሥልም ወጥቶ ያውቃል። ቢቢሲ ይህን ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።
በ2021 ደግሞ ከቫግነር ጋር ግንኙነት አለው የሚባል የቴሌግራም ቻናል አንድ የቫግነር ኮማንደር የሱዳን ወታደሮችን ሲሸልም የሚያሳይ ምሥል አጋርቷል።
ይኸው ቴሌግራም ባሠራጨው ሌላ ተንቀሳቃሽ ምሥል የቫግነር ቅጥረኛ ቡድን አባላት የሱዳን ወታደሮችን በፓራሹት ከሄሊኮፕተር ዘለው እንዲወርዱ ሲያሰለጥኗቸው ያሳያል።
በ2020 ቫግነር ባሰራጨው የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮ ላይ ቡድኑ ከሚሳተፍባቸው አገሮች አንዷ ሱዳን እንደሆነች ያሳያል።
አሜሪካ ይህን ቡድን የድሃ አገሮችን አንጡራ ሃብት በማግበስበስ እና ለአምባገነኖች ከለላ በመስጠት ትከሰዋለች።
ይህ ቡድን ቀደም ሲል 100 አባላትን ይዞ የሙሉ ጊዜ ሥልጠና ለሱዳን ታጣቂዎች ሲሰጥ ነበር ይላሉ አንዳንድ መረጃዎች።
ከሱዳን የወጡ ሌሎች መረጃዎች ደግሞ ቡድኑ 500 አባላት እንዳሉት እና በደቡብ ምዕራብ ኡም ዳፉቅ ከሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ድንበር አካባቢ በብዛት እንደሚንቀሳቀስ ይጠቅሳሉ።
ሱዳን ትሪቡን እንደዘገበው ደግሞ በ2019 በአልበሽር ላይ ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲቀሰቀስ ቫግነር ተቃውሞውን ለማቆም ተሰማርቶ እንደነበር ዘግቧል። ይሁንና ይህ ክስ በሱዳን ባለሥልጣናት ተስተባብሏል።
ሩሲያ በአፍሪካ ያላትን እንቅስቃሴ በተመለከተ መጽሐፍ የደረሱት ዶክተር ሳሙኤል ሮማኒ በበኩላቸው ቫግነሮች የሱዳናውያን አልበሽር ላይ ያነሱትን ተቃውሞ ጭጭ ለማድረግ የራሳቸውን ሚዲያ ዘመቻ መምራታቸውን ጠቅሰዋል።
የቫግነሩ አለቃ ፕሪጎዚን የአል በሽር ተቃዋሚዎች የእስራኤል ተላላኪዎች እና የኢስላም ጠላቶች ተብለው እንዲከሰሱ ሐሳብ ማቅረቡን ዶ/ር ሳሙኤል ጽፈዋል።
በኋላ ላይ ግን አል በሽር ከመንበራቸው ሲፈነቀሉ ቫግነር ቶሎ ብሎ ወደ አል ቡርሃን ደጋፊነት ፊቱን ማዞሩን ደራሲው ያወሳሉ። የሩሲያ መንግሥት ግን የአል በሽርን መንበር መነቃነቅ አልደገፈም።
ከዚያ በኋላም ቫግነር ከፈጥኖ ደራሽ ሠራዊት ጋር ግንኙነት መሠረተ። ይህም የሆነው ሚስተር ፕሪጎዚን በመሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) የተያዘው የወርቅ ክምችት ላይ ፍላጎት ስላደረበት ነው።
ባለፈው ዓመት ሔሜቲ ሞስኮን በጎበኙ ጊዜ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚሹ ለሩሲያ ገልጸው ነበር።
በሱዳን ጉዳይ ጥናት የሚያደርገው ኩሉድ ካይር የባለሙያዎች ቡድን ግን ቫግነር ከሔሜቲ ጋር ወግኗል በሚለው ላይ አይስማማም።
“ቫግነር ከአል ቡርሃንም ሆነ ከሔሚቴም ጋር ነው የሚሠራው፤ በተለያየ ሁኔታና መጠን፤ እንደየአግባቡ” ይላል።

የፎቶው ባለመብት, TELEGRAM
ቫግነር ከሱዳን ሌላ የት ይገኛል?
ቫግነር አሁን አሁን በበርካታ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ እጁንም እግሩንም አስገብቷል።
በዋናነት በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና በሊቢያ ይንቀሳቀሳል። በተለይ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ከፍተኛ ወታደራዊ ተሳትፎ ያለው ሲሆን፣ የአልማዝ ልማት ላይ ተሰማርቶ ይገኛል።
ቡድኑ ከሊቢያ እና ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሌላ በማሊም እንዲሁ ተሳትፎ ያደርጋል።
በማሊ እስላማዊ አክራሪ ቡድኖችን ለመዋጋት ከመንግሥት ጋር እጅ እና ጓንቱ ሆኖ የሚሰራ ሲሆን፣ ቡድኑ ግን ይህንን ዜና አሁንም ድረስ ያስተባብላል።
ዋሽንግተን ፖስት ቅዳሜ ዕለት ባተመው ዘገባ ቫግነር በማዕድን ማውጣት እና በኮንትሮባንድ፣ የጦር መሣሪያ ማስተላለፍ እና በወታደራዊ ሥልጠና እንዲሁም በተዋጊነት ቢያንስ በ13 የአፍሪካ አገራት ውስጥ በአንድም በሌላም መልኩ ተሳትፎ እንዳለው አመልክቷል።
የአፍሪካ አገሮች እና መሪዎቻቸው ከአሜሪካ እና ከምዕራቡ ዓለም ጋር ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ግንኙነት ሊመሠርቱ አልቻሉም። ከምዕራቡ አገራት ጋር ያላቸው ግንኙነትም በቅድመ ሁኔታዎች የተሞላ ነው።
በዚህም የተነሳ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ አገሮች ሩሲያን እና ቻይናን እንደ ሁነኛ አጋር እያዩ መጥተዋል። ይህን ሁኔታ ለመለወጥ አሜሪካ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አዲስ ጥረት ብትጀምርም ብዙ የተሳካላት አይመስልም።
ሩሲያ በበኩሏ ለአፍሪካ አገሮች የውስጥ ጉዳያችሁ ጣልቃ ሳልገባ አብሪያችሁ ልሠራ እፈቅዳለሁ በማለት አዲስ የዲፕሎማሲ በር ከፍታለች።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሰርጌይ ላቭሮቭ በቅርብ ወራት ውስጥ ማሊ፣ ሱዳን፣ ደብብ አፍሪካ፣ ኢስዋቲኒ፣ አንጎላ እና ኤርትራን ጎብኝተዋል።
በሐምሌ ወር ላይ ደግሞ ፑቲን ለአፍሪካ መሪዎች በሴንት ፒተስበርግ ከተማ ውስጥ ጉባኤ አሰናድተዋል።
ከአፍሪካ አንጡራ ማዕድናት ትርፍ ለማጋበስ ኃያላን በሦስት ረድፍ ተሰልፈዋል። አሜሪካ፣ ሩሲያ እና ቻይና የቡድን መሪዎች ናቸው።
የቫግነር ቡድንን ልዩ የሚያደርገው መንግሥት አለመሆኑ እና እጁን የሚያስገባውም በቀጥታ መሆኑ ነው።












