“የጥይት እሩምታ በላያችን ላይ አርከፈከፉብን” ወደ ሳዑዲ ለመግባት የሞከሩ ኢትዮጵያውያን

በጥቃቱ እግሩን አጥቶ የተረፈው ሙስጠፋ
የምስሉ መግለጫ, በጥቃቱ እግሩን አጥቶ የተረፈው ሙስጠፋ

“በተደጋጋሚ ተኮሱብን። መቼም ቢሆን በማላስበው መንገድ የተገደሉ ሰዎች አይቻለሁ። በስፍራው 30 ሰዎች ሲገደሉ ተመለከትኩ። አንዲት ቋጥኝ ድንጋይ ስር ተኝቼ ተደበቅኩኝ። ሰዎች በዙሪያዬ የተኙ መስሎም ተሰማኝ። የተኙ የመሰሉኝ ሰዎች አስከሬኖች እንደሆኑ ያወቅኩት ቆይቼ ነው። ስነቃም ብቻዬን ነበርኩ” በማለት ከሳዑዲ የድንበር ጠባቂዎች ግድያ ያመለጠች የ14 ዓመቷ ታዳጊ ሃምዲያ ተናግራለች።

የሃምዲያ ታሪክ ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ከየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለማቋረጥ ሲሞክሩ በሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች በጅምላ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አሰቃቂ ሁኔታ በያዘው ሪፖርት ውስጥ ተካቷል።

ተቋሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የተፈጸመውን የጅምላ ግድያ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደሆነም ባወጣው ዘርዘር ያለ ሪፖርት ጠቅሷል።

ስደተኞቹ በጦርነት እየታመሰች ካለችው የመን ወደ ሳዑዲያ አረቢያ ሊያቋርጡ ሲሞክሩ ነው በጠባቂዎቹ በአስከፊ ሁኔታ እንደተገደሉ የሰፈረው።

ስደተኞቹ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በተተኮሰባቸው ጥይት ቆስለው እግራቸው የተቆረጡ እንዲሁም አስከሬኖች በመንገድ ላይ ተረፍርፍርፈው ማየታቸውን ነው።

ሳዑዲ አረቢያ እነዚህን ስልታዊ ግድያዎች መፈጸማቸውን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም በሰጠችው ምላሽ ውድቅ አድርጋ ነበር።

ሂውማን ራይትስ ዋች የጅምላ ግድያውን የያዘውን ሪፖርት ‘ዘይ ፋየርድ ኦን አስ ላይክ ሬይን’ “ጥይት እንደ ዝናብ በላያችን ላይ አዘነቡብን’ የሚል ርዕስ ሰጥቶታል።

ሪፖርቱ የመን ከሳዑዲ አረቢያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር ላይ የሳዑዲ ፖሊስ እና ወታደሮች ጥይት እና ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ጭምር በመጠቀም በጅምላ በአሰቃቂ ሁኔታ እንደገደሏቸው የስደተኞችን ምስክርነት ይዟል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ያናገራቸው ስደተኞችም ወደ ሳዑዲ ለመሻገር የሞከሩ በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የነበሩበትን አሸባሪ ሁኔታ ተናግረዋል። ሴቶች እና ህጻናትም በቅርብ ርቀት በጥይት ተተኩሶባቸው ተገድለዋል።

“ተኩስ አያባራም፣ ዝም ብሎ ይተኮስ ነበር” ሲል የ21 ዓመቱ ሙስጠፋ ሶፊያ መሐመድ ለቢቢሲ ተናግሯል።

እሱን ጨምሮ 45 ስደተኞች ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ድንበሩን ተሻግረው ወደ ሳዑዲ ለመግባት የሞከሩ ሲሆን የተወሰኑትም መገደላቸውን ያስረዳል።

“እንደተተኮሰብኝ እንኳን አላስተዋልኩም። ነገር ግን ለመራመድ ስሞክር እግሬ የለም” ሲልም ተናግሯል።

ለሦስት ወራት ያህል ጥምን፣ ረሃብን፣ መታረዝን፣ ድካምን ተቋቁመው ነበር እዚህ የደረሱት።

ይባስ ብሎም በየመን እና ኢትዮጵያውያን ሕገወጥ አዘዋዋወሪዎች እጅ ስቃይ እና መከራም አይተዋል። ከተኩስ እሩምታው ከሰዓታት በኋላ የተቀረጸ ቪዲዮ እንደሚያሳየው የሙስጠፋ ግራ እግሩ ከሞላ ጎደል መቆረጡን ነው።

ሙስጠፋ በአሁኑ ወቅት ከጉልበቱ በታች ያለው የግራ እግሩ ተቆርጧል። ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶም ከወላጆቹ ጋር እየኖረ ሲሆን፣ ሲራመድም በክራንች ድጋፍ እና ያልተስተካከለ የሰው ሰራሽ እግርም አጥልቋል።

“ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሄድኩት የቤተሰቦቼን ሕይወት ለማሻሻል ፈልጌ ነበር። ነገር ግን ተስፋዬ ጨለመ። አሁን በወላጆቼ እርዳታ ነው የምኖረው” ሲል የሁለት ልጆች አባት የሆነው ሙስጠፋ ተናግሯል።

ማንነቱን ለመጠበቅ ኢብሳ ብለን የምንጠራው ሌላው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በበኩሉ በድንበር ላይ የተተኮሰበት የሳዑዲ ወታደራዊ መለዮ በለበሱ ሰዎች መሆኑን ይናገራል።

“ደበደቡን። የተወሰኑትን ገደሉ። በሕይወት የተረፉትንም ወደ ሆስፒታል ወሰዱ። የተገደሉት ሰዎች አስከሬን መሬት ላይ በየቦታው ተረፍርፎ ነበር” ሲልም ለቢቢሲ ተናግሯል።

“ጭኔ መሃል ብልቴ አካባቢ በጥይት ተመትቻለሁ። እግሮቼም ሽባ ሆነዋል። መራመድ እንኳን አልችልም። እሞታለሁ ብዬ አስቤ ነበር” ብሏል።

በሳዑዲ የድንበር ጠባቂዎች የተገደሉ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, social Media

የምስሉ መግለጫ, በሳዑዲ የድንበር ጠባቂዎች የተገደሉ ስደተኞች

የግድያ ሜዳዎች

ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎች ዕድለኛ ቢሆኑም በከፍተኛ መቃወስ እና መረበሽ ውስጥ ናቸው።

በየመን መዲና ቢቢሲ ያገኛት ዛህራ ስለተፈጠረው ሁኔታ ስትናገር ህመሟ፣ መረበሿ፣ ስቃይዋ ይነበባል።

እድሜዬ 18 ነው ብትልም ትንሽ ትመስላለች። ዛህራንም ማንነቷን ለመጠበቅ ስንል ትክክለኛ ስሟን አንጠቅስም።

ሳዑዲ አረቢያ ለመድረስ ከፍተኛ ገንዘብ ፈጅታለች።

ለሕገወጥ አዘዋዋሪዎች የሚከፈለው ዋጋ፣ ለአጋቾች የሚከፈል ካሳ ተደማምሮ 2 ሺህ 500 ዶላር ወጥቶባታል። ይህ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለበትም ጉዞ በጥይት እሩምታ ተጠናቋል።

ይህችም ታዳጊ በተተኮሰባት ጥይት የአንድ እጅ ጣቶቿን በሙሉ አጥታለች። ስለ ጉዳቷ ስትጠየቅ ዐይኗ ቦዘዝ ይልና በርቀት የምትመለከት ሲሆን መልስም ልትሰጥ አልቻለችም።

እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት ከሆነ በየዓመቱ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከአፍሪካ ቀንድ ተነስተው አደገኛ የሚባል ጉዞን በማድረግ በጦርነት ውስጥ ወደምትገኘ የመን ይደርሳሉ።

ከየመንም ለተሻለ ሕይወት በሚል በነዳጅ በበለጸገችው ሳዑዲ አረቢያም ያቀናሉ።

በርካቶችም በዚህ አስከፊ ጉዟቸው እስር፣ ድብደባ እና ሌሎችም ጥሰቶች እንደሚደርስባቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።

በርካቶችም ባሕሩን የሚያቋርጡት ሕይወታቸውን አስይዘው ነው።

ባለፈው ሳምንት ብቻ በጂቡቲ የባሕር ዳርቻ ላይ ጀልባዋ በገጠማት አደጋ ከ24 በላይ ስደተኞች መጥፋታቸው ተዘግቧል።

ካርታ

ከየመን የሚነሱት ዋና ዋና የስደተኛ መተላለፊያ መንገዶች ሕይወታቸው በተቀጠፈ ስደተኞች መቃብር ተሞልቷል።

ከሁለት ዓመት በፊት በመዲናዋ ሰንዓ የሚገኘውና በአገሪቱ የሁቲ አማጺያን የሚተዳደረው እስር ቤት ቃጠሎን ተከትሎ በርካታ ስደተኞች ሕይወታቸውም አልፏል።

ነገር ግን በሂውማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ላይ የተጠቀሱት ጥሰቶች በመጠን እንዲሁም በሁኔታቸው ከዚህ ቀደሙ የተለዩ ናቸው።

“የመዘግባናቸው ጅምላ ግድያዎችን ነው” ሲሉም ሪፖርቱን በመሪነት ያጠናቀሩት ናዲያ ሃርድማን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በርካቶች ግድያ ስለሚከናወንባቸው ሜዳዎች ነግረውናል። አስከሬኖች በኮረብታዎችም ላይ እንዲረፈረፉ ተደርገዋል” ሲሉም ናዲያ ገልጸዋል።

ከመጋቢት 2014 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 2015 ዓ.ም. ድረስ የደረሱ ግድያዎችን ያጠናቀረው ሪፖርት 28 ተቀጣጣይ ፈንጂዎች የተፈጸሙበትን እንዲሁም 14 በቅርብ ርቀት ተኩስ የተገደሉበትን ዝርዝር አካቷል።

“ከእነዚህ ጥቃቶች የተረፉ ሰዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ አሰቃቂ የግድያ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ልከውልኛል። በጣም የሚያስፈሩ እና የሚያሳቅቁ ጉዳቶችን ያሳያሉ” ብለዋል።

ድንበሩን ለማቋረጥ ያለው ርቀት እንዲሁም የተረፉ ሰዎች ተከታትሎ ለማግኘት አስቸጋሪ ከመሆኑም ጋር ተያይዞ ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ በትክክል ማወቅ እንደማይቻል የሪፖርቱ ፀሐፊዎች ተናግረዋል።

“ቢያንስ 655 ሰዎች ተገድለዋል እንላለን ነገር ግን በሺዎች ሊሆን ይችላል። የደረሱት ጥቃቶች መጠነ ሰፊ የሆኑ እንዲሁም ስልታዊ ሲሆኑ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊቆጠሩ እንደሚችሉም አሳይተናል” ብለዋል።

በሳዑዲ ሰሜናዊ ድንበር አካባቢ መጠነ ሰፊ ግድያዎች በሳዑዲ የፀጥታ ኃይሎች እየተፈጸሙ እንደሆነ ይፋ የሆነው ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች ለሳዑዲ መንግሥት በጻፉት ደብዳቤ ላይ ነው።

“የሳዑዲ የፀጥታ ኃይሎች በስደተኞቹ ላይ እያደረሱት ጥቃቶች ስልታዊ፣ መጠነ ሰፊ፣ ድንበር ዘለል መሆናቸው እንዲሁም ከባድ የጦር መሳሪያዎች እንዲሁም ትንንሽ መሳሪያዎችን ተጠቅመዋል” በሚል ነው ባለሙያዎቹ የጻፉት።

ምንም እንኳን ክሱ በጣም አስፈሪ ቢሆንም ደብዳቤው ሪፖርት አልተደረገም።

በየመን የስደተኞች መስመር ያሉ መቃብሮች

የሳዑዲ እና የኢትዮጵያ ምላሽ

የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት የቀረበበትን ክስ እንደሚመለከተው ገልጾ፣ ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ግድያው ስልታዊ እንዲሁም መጠነ ሰፊ ነው ማለቱን ሐሰት ነው ሲል አጣጥሏል።

“በተሰጠን ውስን መረጃ መሠረት፣ የሳዑዲ ባለሥልጣናት የቀረበውን ውንጀላ የሚያረጋግጥ ወይም የሚደግፍ ምንም አይነት መረጃም ሆነ ማስረጃ አላገኙም” የሚል ምላሽ የሳዑዲ መንግሥት ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ እና እያጣራ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባወጣው መግለጫ አመልክቶ፣ ከሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን ክትትል እንደሚደረግበት ገልጿል።

ባለፈው ወር ሚክስድ ማይግሬሽን ሴንተር የተሰኘ አለም አቀፍ የምርምር ማዕከል በሳዑዲ ድንበር አካባቢ እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎችን የያዘ ሪፖርት አውጥቷል። ማዕከሉ ይህንንም ሪፖርት ያጠናቀረው ከጥቃቱ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን አናግሮ ነው።

በድንበር አካባቢ የበሰበሱ አስከሬኖች፣ በሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች የተያዙ ስደተኞች የትኛው እግራቸው በጥይት እንዲመታ እንዲመርጡ፣ እንዲሁም መትረየስ እና ሌሎች መሳሪያዎች በርካቶችን በጅምላ ለመግደል ጥቅም ላይ መዋላቸውን የሚያሳይ ዘርዘር ያለ ሪፖርት ነው ማዕከሉ ይዞት የወጣው።

የሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት ጠለቅ ያለ ሲሆን፣ በርካታ የዐይን እማኞችን ጨምሮ፣ በርካታ ግድያዎች የተፈጸሙባቸውን ስፍራዎች የሚያሳዩ የሳተላይት ምስሎች እንዲሁም ጊዜያዊ የቀብር ስፍራዎችን ይዟል።

ሪፖርቱ በተጨማሪም ስደተኞች በታጠቁ ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ታጅበው ወደ ድንበር ከመወሰዳቸው በፊት ስለሚታሰሩበት የየመኑ ሞናቢህ የማቆያ ማዕከልም ይጠቅሳል።

ተቋሙ ያናገራቸው አንድ ስደተኛ እንዳሉት የሁቲ አማፂያን የሞናቢህ ማዕከል የፀጥታውን ጉዳይ የሚቆጣጠሩ ሲሆን፣ ከሕገወጥ አዘዋዋሪዎችም ጋር አብረው ይሰራሉ። የሳተላይት ምስሎች በአንድ በታጠረ ግቢ ውስጥ ተጠጋግተው የሚታዩ ብርቱካናማ ድንኳኖችን ነው።

አዳዲስ መቃብሮች

ሂውማን ራይትስ ዋች በሪፖርቱ ያካተተው እስከ ሰኔ ወር ድረስ ያለውን ቢሆንም ቢቢሲ ግን ግድያዎቹ ስለመቀጠላቸው የሚያረጋግጡ መረጃዎች አግኝቷል።

ቢቢሲ የተመለከታቸው ቪዲዮዎች በድንበር ላይ የተጎዱ ስደተኞች ወደ ሰሜናዊቷ ሰዓዳ ወደሚገኝ ሆስፒታል አርብ ዕእለት እንደገቡም ያሳያል። በአቅራቢያው በሚገኝ መካነ መቃብርም የቀብር ሥነ ሥርዓቶች እየተፈጸሙ ነበር።

ቢቢሲ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ሚክስድ ማይግሬሽን እና ሂውማን ራይትስ ዎች ያቀረቧቸውን ሪፖርቶች ጠቅሶ የሳዑዲ አረቢያን መንግሥት ስለ ጅምላ ግድያው ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።

ሆኖም የሳዑዲ መንግሥት ክሱ “መሰረተ ቢስ እና በታማኝ ምንጮች ላይ የተመሠረተ አይደለም” ሲል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ምላሽ ሰጥቷል።

በሰንዓ የሚገኘው በሁቲ የሚመራው መንግሥት በበኩሉ ለሂውማን ራይትስ ዎች በላከው ደብዳቤ የሳዑዲ የድንበር ጠባቂዎች “በስደተኞች እና የየመን ዜጎች ላይ ሆን ብለው ግድያ መፈጸማቸውን እንደሚያውቅ አስታውቋል። ሆኖም ከሕገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ጋር እንደማይተባበር አስታውቆ ወንጀለኞም ሲል ጠርቷቸዋል።