ሰሜን ኮሪያ አሜሪካዊው ወታደር ወደ ሃገሯ የገባው የሚደርስበትን ዘረኝነት ለመሸሽ ነው አለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ወር ላይ አሜሪካዊው ወታደር ድንበሯን አቅርጦ የገባው በጦሩ ውስጥ ያለውን ሰብዓዊ አያያዝ እና ዘረኝነት ለመሸሽ ነው አለች።
ሰሜን ኮሪያ፤ የዩናይትድ ስቴትሱ ወታደር ትራቪስ ኪንግ ባለፈው ወር ድንበሯን ተሻግሮ የገባው የሠራዊቱ አባል ሆኖ የሚደርስበትን “ኢ-ሰብዓዊ አያያዝና ዘረኝነት” በመሸሽ ነው ብላለች።
የ23 ዓመቱ ወታደር ባለፈው ወር ነው ጉብኝት ላይ ሳለ ከደቡብ ኮሪያ ተሻግሮ ወደ ሰሜን ኮሪያ የገባው።
ወታደሩ “በሰሜን ኮሪያ ጥገኝነት ለመጠየቅ ፍላጎት እንዳለው” የሃገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ዋሺንግተን፤ ፒዮንግያንግ ስለጉዳዩ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የሰጠችው አስተያየት እውነት ስለመሆኑ ማጣራት አልችልም ብላለች።
ለሰሜን ኮሪያ አስተያየት ምላሽ የሰጡ አንድ የፔንታገን ባለሥልጣን እንዳሉት ቅድሚያ የሚሰጡት ጉዳይ ወታደር ኪንግን “በተገኘው መንገድ” በሰላም ወደ ሃገሩ መመለስ ነው።
የዩኤስ ባለሥልጣናት ከዚህ በፊት እንዳሉት ወታደሩ ደንበር ተሻግሮ ወደ ሰሜን ኮሪያ የዘለቀው ሆነ ብሎ ነው። ወታደሩ ወደ ሰሜን ኮሪያ ከገባ በኋላ የት እንዳለ አይታወቅም።
የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ጣቢያ ኬሲኤንኤ እንደዘገበው ወታደሩ እያወቀ ድንበር ተሻግሮ እንደገባ ቢዘግብም ለዚህ ተግባሩ ቅጣት ይሰጠዋል ወይ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ጣቢያው በዘገባው ወታደሩ ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል አሊያም የት ነው ያለው የሚለውንም አልመለሰም።
ኪንግ የአሜሪካ ጦር ሠራዊትን የተቀላቀለው በፈረንጆቹ 2021 ሲሆን ደቡብ ኮሪያ ያለው ካምፕ ውስጥ ነበር።
ድንበር ተሻግሮ ወደ ሰሜን ኮሪያ ከመግባቱ በፊት ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ሰው በመማታቱ ለሁለት ወር ያክል የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎበት ቆይቶ ሐምሌ 10 ነው የተፈታው።
የሥነ-ምግባር ቅጣቱን ሊቀበል ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መብረር ሲገባው ነው ከአውሮፕላን ማረፊያ ወጥቶ በሰሜን እና ደቡብ ኮሪያ መካከል ወዳለው ከጦር ነፃ ወደሆነው ዞን ጉብኝት የሚያደርጉ ሰዎችን የተቀላቀለው።
“ምርመራ ሲደርግለት ወታደር ኪንግ ወደ ዴሞክራሲያዊት የሰሜን ኮሪያ ሪፐብሊክ የገባው በአሜሪካ ጦር ባለው ኢ-ሰብዓዊ አያያዝና ዘር ተኮር መድልዎ ምክንያት እንደሆነ ተናግሯል” ይላል የጣቢያዘው ዘገባ።
“ወታደሩ በሰሜን ኮሪያ አሊያም በሌላ ሶስተኛ ሃገር ጥገኝነት ጠይቆ መኖር እንደሚፈልግና በአሜሪካ እኩል የሆነ ማሕበረሰብ ይፈጠራል ብሎ ማሰብ ቅዠት እንደሆነ ገልጧል።”
በያዝነው ወር መባቻ ለኤቢሲ ኒውስ ድምፃቸውን የሰጡት የኪንግ ቤተሰቦች ዘረኝነት እየደረሰበት እንዳለ ነግሮናል ብለዋል። አክለውም የአእምሮ ጤናው እያሽቆለቆለ እንደነበር ጠቅሰዋል።
ሰሜን ኮሪያ በኮሚዩኒዝም ስም ከሚመሩ ጥቂት የዓለማችን ሃገራት አንዷ ስትሆን በጣም ምስጢራዊና ተገልሎ የሚኖር ሕዝብ ያላት ናት።
በኪም ጆንግ-ኡን የሚመራው መንግሥት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈፅማል የሚል ወቀሳ በተደጋጋሚ ይደርስበታል።
በእንግሊዝኛው ዲሚሊታራይዝድ ዞን የሚባለው ሥፍራ ከጦር እንቅስቃሴ ነፃ ይሁን እንጂ አሁንም በተቀበሩ ፈንጅዎች የተሞላ፣ በኤሌክትሪክ አጥሮች የተከበበና በካሜራ ዕይታ የሚጠበቅ ነው።
የታጠቁ ወታደሮች ሥፍራውን ቀን ተሌት ይጠብቃሉ።
ከወታደር ኪንግ ጋር ጉብኝት ሲያደርጉ የነበሩ ሰው ወታደሩ ድምፁን ከፍ አድርጎ ከሳቀ በኋላ በሕንፃዎች መካከል ተሽሎክሉኮ እንደጠፋ ይናገራሉ።
“መጀመሪያ ቀልድ መስሎን ነበር። ከዚያ ግን በዚያው ጠፍቶ ሲቀርና የምሩን መሆኑን ስናውቅ ሁሉም ተደናገጠ” ሲሉ ስማቸው ያልተጠቀሰው ግለሰብ ለቢቢሲው የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ተናግረዋል።
አክለው ወታደር ኪንግ ወደ ሰሜን ኮሪያ ዘልቆ ሲገባ የሃገሪቱ ወታደሮች በሥፍራው እንዳልነበሩ ያወሳሉ።
ወታደሩ ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለው አስጊ ሆኗል። በሰሜን ኮሪያ ባለሥልጣናትና በአሜሪካ አቻቸው መካከል ድርድር መደረግ ተጀምሯል።












