በምዕራብ ኦሮሚያ ሰላማዊ ሰዎች በመንግሥት ኃይሎች መገዳላቸው ተነገረ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ሰላማዊ ሰዎች በመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች መገደላቸው ተነገረ።
በዞኑ ባሉ ወረዳዎች ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ፣ ድብዳባ እና እስር እየተፈጸመ ስለመሆኑ ከጥቃት የተረፉ እና ቤተሰቦቻቸውን ያጡ እንዲሁም የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በክልሉ የሚንቀሳቀሱት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረሰ (ኦፌኮ) ፓርቲዎች ባወጡት መግለጫ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
ነዋሪዎች እና ፓርቲዎቹ ስለሚያቀርቡት ክስ ከክልሉ መንግሥት ምላሽ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
ነዋሪዎች እንደሚሉት በዞኑ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተፈጽሟል ከተባሉ ግድያዎች መካከል አንዱ ጮቢ በተባለው ወረዳ የተፈጸመው የበርካታ ሰዎች ግድያ ይገኝበታል።
ይህ በጮቢ ወረዳ ነሐሴ 04/2015 ዓ.ም. በመከላከያ ሠራዊት አባላት በተፈጸም ጥቃት ስድስት ሰዎች መገደላቸውን በቦታው የነበሩት እና በጥይት ተመትተው በሕይወት የተረፉት አቶ አራርሳ ያደሳ ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግረዋል።
አቶ አራርሳ እንደሚሉት በዕለቱ ከቤተሰብ አባላት እና ከጎረቤት ጋር በቤት ውስጥ ቡና እየጠጡ ሳለ ድንገት አንድ ወታደር ወደ ቤት ገብቶ ተኩስ በመክፈት 6 ሰዎችን መግደሉን እና እርሳቸውን ጨምሮ ሁለት ሰው ማቁሰሉን ገልጸዋል።
“ቡና እየጠጣን ሳለ ድንገት ወደ ቤት ዘሎ በመግባት ‘ምን እየሰራችሁ ነው?’ ሲል ጠየቀን። ...‘ቡና እየጠጣን ነው’ አልን። ከዚያ ምንም አይነት መልስ ሳይሰጠን ወንድ ሴት ሳይል ተኩስ ከፈተ” በማለት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የሆነውን ተናግረዋል።
ሕይወታቸው ያለፈው ስድስት ሰዎች እህታቸውን ጨምሮ ሁለቱ ሴቶች እንዲሁም ልጃቸውን ጨምሮ አራቱ ወንዶች መሆናቸውን ይገልጻሉ።
“ወንድ ልጄ ከረዩ አራርሳ፣ የልጄ ሚስት ደስታ ለሜሳ፣ እህቴ ጥሩ ያደሳ፣ አማቼ ዱጋሳ መርጋሳ ሲሆን፣ ጉርሜ ጂፋራ እና አበራ ጂፋራ ደግሞ እኔ በምኖርበት ቦታ የእርሻ ሥራ የሚሰሩ ናቸው” በማለት በወታደሩ የተገደሉ ሰዎችን ማንነት ዘርዝረዋል።
አቶ አራርሳ በዕድሜ ትንሽ የሆነ ኃይሉ ፉፋ የሚባል ታዳጊ እና እርሳቸው ብቻ ከዚህ ጥቃት በሕይወት መትረፋቸውን ገልጸዋል።
እግራቸው በጥይት መመታቱን የሚናገሩት አቶ አራርሳ ጥቃት አድራሹ “በደም ተነክሬ ሲመለከተኝ የሞትኩ መስሎት ትቶኝ ሄዷል” በማለት በሕይወት የተረፉበትን አጋጣሚ አስረድተዋል።
ለቅሶ ለመሄድ ተጠራርተው በአንድ ቦታ ተሰባስበው ቡና ሲጠጡ ሕይወታቸው ያለፉት ሰዎች አርብ ነሐሴ 05/2015 ዓ.ም. ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል ብለዋል።
እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን በስፋት ከሚንቀሳቀስባቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች መካከል አንዱ ምዕራብ ሸዋ ዞን እንደሆነ ይነገራል።
በዞኑ ባሉ የተለያዩ ወረዳዎች በታጣቂ ቡድኑ እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶች ሲደረጉ ቆይተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት አባሉ በነዋሪዎቹ ላይ ጥቃቱን ለመፈጸም ምክንያቱ ምን እንደሆነ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ የሚናገሩት አቶ አራርሳ፣ በዕለቱ በአካባቢው የታጣቂዎች እንቅስቃሴም ሆነ ተኩስ እንዳልነበረ ገልጸዋል።
“በቦታው ምንም የሆነ ነገር የለም። የተኮሰም ሰው የለም። እንዲሁ ከሜዳ ተነስቶ ነው ቤት ውስጥ ገብቶ የጨረሰን” ብለዋል።
በተመሳሳይ ጀልዱ ተብሎ በሚጠራው ሌላኛው የምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ደግሞ ከብት በማገድ ላይ የነበረ ሰው በመንግሥት ኃይሎች መገደሉን ለቢቢሲ የተናገረው የሟች ወንድም ነው።
ዓርብ ነሐሴ 05/2015 ዓ.ም. ጀልዱ ወረዳ ሃሮ ደጋ ተብላ በምትጠራ መንደር ውስጥ የቤተሰብ አስተዳዳሪ የነበረው አቶ ፉርጋሳ ከብት እያገደ ሳለ በመንግሥት ኃይሎች መደገሉን ስሜ አይጠቀስ ያለው ወንድም ለቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ተናግሯል።
“በአካባቢው የፀጥታ ችግር አልነበረም። ድንገት ወደ መንደራችን ገብተው ከብቶቹን እያገደ የነበረውን ወንድሜን ገደሉት” ብሏል።
ይህ ስሜ አይጠቀስ ያለው የሟች ወንድም ኢልፈታ ተብሎ ከሚጠራው ወረዳ የመጡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በሦስት አቅጣጫ ወደ መንደራቸው ከገቡ በኋላ ወንድሙን ከመግደላቸው በተጨማሪ በሌሎች ላይ ድብደባ መፈጸማቸውን ይገልጻል።

ይህን በምዕራብ ኦሮሚያ ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ የተፈጸመውን ግድያ ተቃዋሚዎቹ ፓርቲዎች፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አውግዘውታል።
ኦነግ ቅዳሜ ነሐሴ 12/2015 ዓ.ም. ባወጠው መግለጫ በምዕራብ ሸዋ በሚገኙት አምቦ፣ ጮቢ፣ ዳኖ፣ ግንደ በረት፣ ኢልፈታ፣ ኢሉ ገላን፣ ሊበን ጃዊ እና ሚዳ ቀኚ ወረዳዎች “የመንግሥት ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያ፣ ዘረፋ እና የጅምላ እስር እየፈጸሙ ነው” ብሏል።
ፓርቲው እንደሚለው መንግሥት ሸኔ ብሎ በሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላይ እያካሄደ ነው በሚሉት ዘመቻ በሕዝብ ላይ የተቀናጀ ጥቃት ከፍቷል ብሏል።
አክሎም በተጠቀሱት የምዕራብ ሸዋ ዞን ወረዳዎች ውስጥ መንግሥት ነሐሴ 01፣ 02፣ 04 እና 05/2015 ዓ.ም. በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ የሆነ ግድያ፣ ድብደባ፣ የጅምላ እስር፣ ዘረፋ እና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል ብሏል።
በተመሳሳይ ኦፌኮ እሁድ ነሐሴ 13/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “የበቀል በሚመስል ዘመቻ” መንግሥት በሰላማዊ ዜጎች ላይ በከፍተው ጥቃት በጮቢ ወረዳ በኬ ሆፉ ተብላ በምትጠራ መንደር ነሐሴ 04/2015 ዓ.ም. “አስራ አንድ ሰዎች በመንግሥት ኃይሎች ተገድለዋል” ብሏል።
በጮቢ ወረዳ በነበረ ጥቃት ከሞት ተርፊያለሁ የሚለው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ከእርሱ ጋር ተይዘው የነበሩት ሦስቱ መገደላቸውን ለቢቢሲ ተናግሯል።
ለደኅንነቱ ሲል ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገው ይህ ወጣት የመከላከያ ሠራዊት ከሚኖርበት ቀበሌ ሞጎራ ሚልኬሳ፣ ፊጣ ሚልኬሳ እና ቶለሳ ዲሪብሳ ከሚባሉ ሦስት ሰዎች ጋር ወደ ሌላ ቦታ ከወሰዷቸው በኋላ ተኩስ ተከፍቶባቸው ሦስቱ ሲገደሉ እርሱ ግን ማምለጡን ይገልጻል።
“ከአንድ ቦታ ላይ አራታችንንም ከያዙ በኋላ ሸክም አሸክመው ረዥም ርቀት ካስጓዙን በኋላ ድንገት ምንም ሳይሉ ተኩስ ከፈቱብን። ዐይኔ እያየማ አልሞትም ብዬ እየተኮሱብኝ ሮጥኩኝ። ብዙ ተኮሱብኝ። ግን አንድ ጥይት ብቻ ነው የመታኝ።”
ከዚያው ጮቢ ወረዳ በኬ ሆፉ ቀበሌ ቢቢሲ ያናገረው ሌላኛው ወጣት ሦስት ሰዎች በአንድ ቦታ ስለመገደላቸው አንድ ወጣት ግን ሮጦ ማምለጡን መስማቱን ገልጾ በቀበሌያቸው በዕለቱ መንግሥት ሸኔ ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን እና በመከላከያ መካከል የተኩስ ልውውጥ ተደርጎ እንደነበረ ይገልጻል።
በዞኑ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተፈጽሟል ስለተባለው ግድያ ለመጠየቅ የዞን እንዲሁም የወረዳ አስተዳዳሪዎችን ለማግኘት ቢቢሲ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን በምዕራብ እና በደቡብ ኦሮሚያ የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ ታጣቂ ቡድኑ በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች የደኅንነት እጦት ያለባቸው ሆነዋል።
ይህ ቡድን በበርካታ ሰላማዊ ሰዎች ሕይወት መጥፋት የሚከሰስ ሲሆን፣ መንግሥትም ከታጣቂ ቡድኑ ጋር ወግነዋል በሚላቸው ላይ ከሕግ ውጭ የሆነ ግድያን በመፈጸም በመብት እና በፖለቲካ ቡድኖች ይወነጀላል።
የክልሉ እና የፌደራል መንግሥት ይህን ቡድን ለማጥፋት ቁርጠኛ መሆናቸውን እና በተለያዩ ጊዜያት ዘመቻ እያካሄዱ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።












