መንግሥት በአማራ ክልል የሚወስዳቸው እርምጃዎች በግጭቱ ተሳትፎ የሌላቸውን ሰዎች እንዲለይ ተጠየቀ

የጎንደር ከተማ ከሁለት ዓመታት በፊት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መንግሥት በአማራ ክልል ያለውን ግጭት ለመቆጣጠር የሚወስዳቸው እርምጃዎች በግጭቱ ተሳትፎ የሌላቸውን ሰዎች በመለየት እንዲፈጸሙ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ጠየቀ።

በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተደረገ ያለው ውጊያ የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት መቅጠፉን ተከትሎም ነው ኢሰመጉ መንግሥት “የሚወስዳቸው ሰላም የማስከበር እርምጃዎች ተመጣጣኝ እና በግጭቱ ተሳታፊዎች ላይ” ተፈጻሚ እንዲሆኑ ነሐሴ 8/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የጠየቀው።

በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተ ሰላም ከተማ ነሐሴ 7/2015 ዓ.ም የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተመጣጣኝ ያልሆነ እና በግጭቱ ተሳታፊ ያልሆኑ ሰዎችን ሳይለዩ ጥቃት መፈጸማቸውን ኢሰመጉ በመግለጫው አትቷል።

ከፍኖተ ሰላም በተጨማሪ በቡሬ ከተማም ነሐሴ 6/2015 ዓ.ም ተመሳሳይ ጥቃት መድረሱን ገልጾ በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች እንደሞቱና የአካል ጉዳት እና ንብረት መውደሙንም ኢሰመጉ በመግለጫው አስፍሯል።

በነዚህ ጥቃቶች የሞቱ ሰዎችን ቁጥር መግለጫው ባያትትም በፍኖተ ሰላም ከተማ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 25 ሰዎች መገደላቸውንና ከ50 በላይ ሰዎችም እንደቆሰሉ የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሱ ተናግረዋል።

ጥቃቶቹን በተመለከተ አንዳንዶች የደረሰው በከባድ መሳሪያ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) የተፈጸመ መሆኑንም ነው ለቢበሲ የገለጹት።

በአማራ ክልል እንደ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ሸዋ ሮቢት፣ ደብረ ብርሃን፣ ላሊበላ እና ሌሎችም ከተሞች በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ከሰሞኑ የተኩስ ልውውጦች የነበሩ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎችም ላይ ከባድ መሳሪያዎች ጭምር ጥቅም ላይ መዋላቸውንም ኢሰመጉ አስታውቋል።

ኢሰመጉ በዚህም በግጭቱ ተሳታፊ ያልሆኑ በርካታ ሰዎች መሞታቸውን፣ የአካል ጉዳት መድረሱንም በትናንትናው መግለጫው አስፍሯል። በተጨማሪም የማረሚያ ቤቶችና የፖሊስ ጣቢያዎች ሰበራ ተፈጽሞባቸው የመሳሪያዎች ዝርፊያ እና ከፍተኛ የንብረት መውደም ደርሷል ብሏል።

በአማራ ክልል በተከሰተው ግጭት የንጹሃን ሕይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙን እና ዘረፋ መፈጸሙን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ ከሰሞኑ አስታውቋል።

በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ለቀናት በዘለቀው ግጭት በአማራ ክልል ከተሞች እና የተለያዩ አካባቢዎች እስካሁን በውል ያልታወቁ ሰዎች መሞታቸውን ቢቢሲ የሆስፒታል ምንጮችን በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል።

በአማራ ክልል ያሉ ከተሞችን ከፋኖ ታጣቂዎች ነጻ ማድረጉን መንግሥት ከሰሞኑ ማስታወቁንም ተከተሎ በአንዳንድ አካባቢዎች አንጻራዊ መረጋጋት መታየቱን የጠቆመው የኢሰመጉ መግለጫ አሁንም ውጥረት እና ስጋት ያለባቸው አካባቢዎችም አሉ ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመከላከያ ሰራዊት ግጭት ወዳለባቸው አካባቢዎች በስፋት ተሰማርቶም ያለውን የጸጥታ ችግር መቆጣጠሩንና በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም እንደሰፈነም ጠቅሶ ሆኖም የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችና እና አንዳንድ አገልግሎቶች ወደቀደመው አልተመለሱም ብሏል።

በበርካታ የአማራ ክልል ውስጥ በፋኖ ታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ከዋና ዋና ከተሞች በመውጣት በሌሎች አካባቢዎች እየተካሄደ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በአማራ ክልል የልዩ ኃይልን መልሶ ለማደራጀት ጋር ተያይዞ በተነሳው ውጥረት አገርሽቶ ወደ ግጭት ያመራ ሲሆን እነዚህም ግጭቶች ተባብሰው መቀጠላቸውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል።

“የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ የወጣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” አርብ ሐምሌ 28/ 2015 ዓ.ም. ተደንግጎ ትናንት የጸደቀ ሲሆን የሕዝብን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲሁም ሕግ እና ሥርዓት ለማስከበር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያዋ በሚገኙ አካባቢዎች የጅምላ እስሮች እየተፈጸሙ እንደሆነና እነዚህም እስሮች አብዛኛዎቹ የህግ ስርዓትን ያልተከተሉ ተጠርጣሪዎችም ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡም አስፍሯል።

የጅምላ እስሩ ከወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በሚል እንደሚፈጸም እና ቤተሰቦች ታሳሪዎች ያሉበትን ማወቅ እንዳልቻሉና አንዳንድ ትምህርት ቤቶችም እንደ ማቆያነት ጥቅም ላይ እየዋሉ ስለመሆናቸውም ኢሰመጉ መረጃዎችን ማሰባሰቡን አስታውቋል።

“የፌደራል ፖሊስ አባላትና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት በከተማው የሚፈጽሙትን ህግን ያልተከተለ የጅምላ እስር እንዲያቆሙና ስልጣናችን አላግባብ ከመጠቀም እንዲቆጠቡ፣ ይህንንም የሚፈጽሙ አባላት በህግ እንዲጠየቁም” ኢሰመጉ በመግለጫው ጠይቋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኔር ዶ/ር ካሳ ተሻገር ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳም ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለው በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ይገኛል ይላሉ። በተጨማሪም ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው ሐምሌ 30/ 2015 ዓ.ም በጸጥታ ኃይሎች መወሰዱን አስፍሯል።

በተጨማሪም የሳተናው ሚዲያ መስራችና ባለቤት ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ከተወሰደበት ነሐሴ 7/ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ኢሰመጉ መግለጫውን እስካጠናቀረበት ድረስ ያለበትን ማወቅ እንዳልተቻለም ተገልጿል።

በአማራ ክልል የተፈጠረውን “ግጭት ለማባባስ የከተማ ውስጥ ግዳጅ በመውሰድ የሎጅስቲክስ እና የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ የተለያዩ ሕገወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ ነበር” ያላቸውን 23 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን መምሪያ ዕዙ ከሰሞኑ ማስታወቁ ይታወሳል።

ከአማራ ክልል በተጨማሪም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 12ኛ ሆኖ መመስረቱን ተከትሎ አዲስ የተመሰረተው ክልል ከተማ ውሳኔ ጋር ተያይዞ በአርባ ምንጭ ከተማ ውጥረት መንገሱም ሰፍሯል።

በዚህም ከነሐሴ 3/ 2015 ዓ.ም ጀምሮ መንገድ መዝጋት፣ ጎማ ማቃጠል እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውንና እንዲሁም በተከታዮቹ ቀናት የተቃውሞ ሰልፎችና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ተዘግተው እንደነበርና የንግድ ሱቆች ተዘግተው ነበር ብሏል።

በከተማው በርከት ያኩ ሰዎችም ከየመንገዱ እና ከየቤታቸው ጭምር በጅምላ እየታፈሱ በተለያዩ ጣቢያዎች እና ወደማይታወቅ ስፍራ ተወስደው መታሰራቸውን ገልጿል።

ከነዚህም መካከል የኢሰመጉ የአርባ ምንጭ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሰራተኛ የሆኑት አበበ ዶረና ነሐሴ 4/2015 ዓ.ም ከባጃጅ ውስጥ በፖሊሶች ተይዞ አርባ ምንጭ ከተማ የትነበርሽ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮብኛል ብሏል።

በኦሮሚያ ክልል በአዳማ እና በወንጂ ከተማዎች ውስጥ ሰፋ ያለ የጅምላ እስሮች መኖራቸውንና የሚደረጉ እስሮችም ተገቢውን የህግ ስነ ስርዓት ያልተከተሉ ናቸው ብሏል።

ኢሰመጉ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉ የጅምላ እስሮች በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ በእስር ላይ ያሉ ሰዎች ፍርድ ቤት አንዲቀርቡ እና የሚደረጉ እስሮች ተገቢውን የህግ ሰነስርዓት እንዲከተሉም ጠይቋል።