መንግሥት በአማራ ክልል በሚወስዳቸው እርምጃዎች ለነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲደረግ ኢሰመኮ ጠየቀ

የአማራ ሚሊሻ አባላት ጎንደር አካባቢ ባለፈው ዓመት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአማራ ክልል በመከላከያና በታጣቂ ሚሊሻዎች፣ ፋኖ የተነሳው ግጭት መባባሱን ተከትሎ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ።

መንግሥት በሚወስዳቸው እርምጃዎች ነዋሪዎች ለበለጠ ጉዳት እንዳይጋለጡ ጥንቃቄ እንዲደረግ ኢሰመኮ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።

“በአማራ ክልል ሰላም እና ደኅነነት ለማረጋገጥ መንግሥት በሚወስዳቸው እርምጃዎች ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ነዋሪዎች እንዳይዳረጉ ጥንቃቄ እንዲደረግም” ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ትናንት ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም በአማራ ክልል ያለው “በትጥቅ የተደገፈ ህገወጥ እንቅስቃሴ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር ወደማይቻልበት ደረጃ መሸጋገሩንም” በመግለጽ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስተላልፏል።

ኢሰመኮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅትም ሰብዓዊ መብቶች ሊከበሩ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም አስታውሷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማናቸውም ሁኔታ የማይገደቡ መብቶችን የመጠበቅ፣ የተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነጻ መርሆችን ባከበረ መልኩ እንዲተገበርም አሳስቧል።

የክልል ልዩ ኃይሎች መልሶ ማዋቀር ጋር በተያያዘ የተነሳው ግጭት በቅርቡ ተባብሶ በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ ነው።

በነዚህ ውጊያዎችም የተነሳ በቅርቡ የኢንተርኔት አገልግሎት በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች መቋረጡን ኢሰመኮ አስታውሷል።

በተጨማሪም ነዋሪዎች በነጻነት ለመንቀሳቀስና ስራቸውን ለመከወን መቸገራቸውን እንዲሁም የአንቅስቃሴ ገደቦች በአንዳንድ አካባቢዎች መጣላቸውንም ኢሰመኮ መረዳቱን ጠቅሷል።

ኢሰመኮ በክልሉ ከሚያዝያ ወር ጀምሮ በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር እየተባባሰ መምጣቱን እና ከሐምሌ ወር አጋማሽ ጀምሮም ሁኔታዎች እየተባባሱና በርካታ የክልሉ አካባቢዎች ውስጥ በግጭት ውስጥ መሆናቸውንም አስፍሯል።

በአንዳንድ አካባቢዎችም በሲቪል ነዋሪዎች ላይ ጥቃት መፈጸሙን እና የሰላማዊ ሰዎችና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም የትራንስፖርት እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶችም መቋረጣቸውን አስፍሯል።

ኢሰመኮ በአማራ ክልል ከጥቂት ወራት በፊት የክልል ልዩ ኃይሎችን እንደገና ለማዋቀር ከታያዘው የመንግሥት ዕቅድ ጋር በተገናኘ የተከሰተው የፀጥታ ችግር አሳሳቢ እንደሆነ ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርቱ ማመላከቱ የሚታወስ ነው።

በሪፖርቱ እንደ ዋቢ ሆኖ ከተገለጸውም ውስጥ ግንቦት 11/ 2015 ዓ.ም. በሰሜን ሸዋ ዞን የመከላከያ ሠራዊት በወሰደው የኃይል እርምጃ ቢያንስ 5 ሰዎች መሞታቸው ሐምሌ 5 በወጣው 106 ገጾች ባሉት ዓመታዊ ሪፖርት ተካቷል።

አሁን የተነሳው ግጭት ከሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ እንዲሁም ከጎረቤት አገራት ግጭት በመሸሽ የተሰደዱ ተፈናቃዮችንም ለከፍተኛ ችግር ይዳርጋል ብሏል።

ሁሉም ወገኖች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ለሰላም አማራጮች ቅድሚያ እንዲሰጡና ግጭቱን ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ መልዕክቱን አስተላልፏል።