“የእኔ ትግል የመጨረሻ ግብ ከእስር ለሚፈታኝ ሰው ባለውለታ ሆኜ መቅረት አይደለም” አንዳርጋቸው ጽጌ

የፎቶው ባለመብት, ethiotube
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አምስት አስርት ዓመታት ለሚሆን ጊዜ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሲሳተፉ የቆዩ ተጠቃሽ ፖለቲከኛ ናቸው። የፖለቲካ ተሳትፏቸው በኢሕአፓ፣ በኢሕአዴግ እና በግንቦት ሰባት ውስጥ አስከ ትጥቅ ትግል የሚደርስ ነው።
ከወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የቀረበ ግንኙነት የነበራቸው አቶ አንዳርጋቸው፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አመራር ተስፋ ቆርጠው ከአገር ወጥተዋል። ቢቢሲ ምክንያታቸውን እና የወደፊት አላማቸውን ጠይቋቸዋል።

ቢቢሲ፡ ከአገር ኮብልለዋል እየተባለ ነው። ብዙም የተጠበቀ አይደለም። ይህንን ሊያረጋግጡልኝ ይችላሉ?
አቶ አንዳርጋቸው፡ መኮብለል አይደለም። ከአገር ወጥቻለሁ ነው የምለው። የመንግሥት ሥራ ውስጥ የነበርኩ ወይም የጦር ኃላፊ ወይም ደግሞ የመንግሥት ሚኒስትር አይደለሁም። እኖር የነበረው በግል ነበር፤ እናም አገር ጥዬ ወጥቻለሁ። ይህ ትክክል ነው።
ቢቢሲ፡ መቼ ነው የወጡት?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ከአገር የወጣሁት ባለፈው ዐርብ [ነሐሴ 05/2015 ዓ.ም.] ነው።
ቢቢሲ፡ በመውጣት ሒደት ውስጥ የገጠመዎት እክል ነበር?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ምንም እክል የለም። ፓስፖርት ኤግዚት ቪዛ የሚሞላው ሰው ‘ሳያስታርቁን ወዴት ይሄዳሉ’ ብሎ ትንሽ ተመለከተኝ ። ግን ማህተም መትቶ አሳልፎኛል።
ቢቢሲ፡ እዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሰዎት ምክንያት ምንድን ነው? በእርስዎ ላይ ክትትል ነበር? ያዩት? የጠረጠሩት ነገር አለ?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ወንድሜ፣ ጋዜጠኛ ነህ አይደል እንዴ? አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሰዎች በጅምላ እንደሚታፈሱ ታውቃለህ ወይስ እንደ መንግሥት ባለሥልጣናት 23 ሰዎች ብቻ ናቸው የተያዙት የሚለውን ነው የምታምነው?
ቢቢሲ፡ ዛሬ ከእርስዎ በፊት ከኢሰመኮ ሰዎች ጋር አውርቼ በርካታ የጅምላ እስሮች እንዳሉ ተረድቻለሁ እርስዎን የተመለከተውን ለመጠየቅ ነው።
አቶ አንዳርጋቸው፡ ስለዚህ በአማራ ክልል ላይ ፍኖተ ሠላም ከተማ ላይ የኢዜማ ቢሮ፣ የከተማው ትልቅ ሆቴል ያለበት ላይ በድሮን ንጹሃን ዜጎችን መትተው በ20ዎቹ፣ በ30ዎቹ የሚቆጠሩ ሰዎች እንደገደሉ፣ እንዳቆሰሉ አልሰማህም? እያወራሁልህ ያለሁት ስለዚህ ነው።
እንዲህ ዓይነት ግፍ እና በደል የሚፈፅም መንግሥት፣ ምንም ያላደረጉት ላይ ይህንን እርምጃ የሚወስድ መንግሥት፣ ይህንን ግፍ እና በደል በጣም አምርሮ የሚቃወምን ሰው ዝም ብሎ ይመለከታል ብለህ ታስባለህ?
ቢቢሲ፡ እርስዎ በተለይ መጀመሪያ አካባቢ ላይ ከዚህ መንግሥት ጋር የነበረዎትን ቅርበት መሠረት አድርገን በእርስዎ ላይ ሲደርስ ነገሩ ለየት ያለ መልክ ሊኖረው ይችላል በሚል ነው።
አቶ አንዳርጋቸው፡ ምንም የለም። እኔ የረዥም ዘመን ልምድ ያለኝ ፖለቲከኛ ነኝ። አንድ መንግሥት ከየት ተነስቶ ወዴት እንደሚሄድ፣ በምን ዓይነት ወቅቶች ምን ዓይነት እርምጃ እንደሚወስድ፣ ምን ዓይነት አካላትን እንደሚፈራ በደንብ የማውቅ ነኝ።
እኔ ከዚህ መንግሥት ጋር ከተደራጀ ጀምሮ መልካም ግንኙነት ነው የነበረኝ፤ ነገረ ግን በሂደት እየሻከረ ሄዶ መልዕክት ማስተላለፍ የማይቻልበት፣ የምልክላቸው መልዕክት በጣም ጠንካራ ከመሆናቸውም የተነሳ አኩርፈው፣ ዘግተው የተቀመጡበት ሁኔታ ነው ያለው።
እናም ለረዥም ጊዜ ማለትም ካለፈው ዘጠኝ ወይም አስር ወር ወዲህ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለኝም። የምጽፋቸውም ጽሑፎች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያበሳጯቸው በደንብ ነው የማውቀው። እነሱ አካባቢ ያሉ ሰዎችም ይነግሩኛል። ከዚያ አልፎም እነሱ አካባቢ ያሉ ሰዎች ‘ለምን ዝም ብሎ ይታያል? ለምን እርምጃ አንወስድበትም?’ የሚል ሃሳብ እስከማቅረብ እንደሄዱ አውቃለሁ።
በዚህ ሁኔታ አገር ውስጥ ከተቀመጥኩ አገር ውስጥ የሚሰራውን ግፍ ማጋለጥም፣ መናገርም አይቻልም። እናም ሁኔታውን መዝኜ ነው ከአገር የወጣሁት። ሕዝብ ማወቅ አለበት ያልኩት፣ በተጨባጭ መረጃ የተደገፉ ብዙ መረጃዎች ስላሉኝ እነዚያን ለማውጣት አገር ውስጥ ተቀምጬ አልችልም። ለዚህ ነው የወጣሁት።
ቢቢሲ፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመጨረሻ ጊዜ በአካል ያገኟቸው መቼ ነበር? በግንኙነታችሁ ወቅትስ ያስደነገጠዎት ንግግር አለ?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ለመጨረሻ ጊዜ በአካል ያገኘኋቸው ምን አልባት አንድ ዓመት፣ አስር ወር ወደዚያ ገደማ ሊሆን ይችላል። ከዚያ በኋላ በአካል ተገናኝተን አናውቅም። ግን በአካል በምንገናኝበት ሰዓትም ሆነ፣ በአካል ሳንገናኝ እኔ አገር የሚያውቀው ጠባይ ነው ያለኝ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ሄጄ ለእርሱ ጆሮ የሚጥመውን ሙዚቃ ተናግሬ አይደለም የምመለሰው።
ድንገት መረጃው ያልደረሰው ከሆነ በሚል አገር ውስጥ ያለውን ጠቅላላ የባለሥልጣናቱን ሌብነት፣ በየቦታው የሚደረገውን ግድያ እና አፈና፣ በየመሥሪያ ቤቱ የሚፈፀመውን ጉቦ መብላት እና ሌላም ሌላም በመረጃ አስደግፌ ነው የምናገረው።
የሥርዓቱን አደገኛ አካሄድ ሁልጊዜ እንደተናገርኩ ነው። የእኔ ግንኙነት ዝም ብሎ ተገናኝቶ ተጨባብጦ፣ የቆጥ የባጡን ዘበራርቆ የሚመጣበት አይደለም። የሌሎቹን አላውቅም። የአንድ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር ካለው ጊዜ አንጻር ለእኔ በቂ ጊዜ እንደሰጠኝም ነው ያማምነው።
ግን በእነዚያ ጊዜያት ያደረግናቸውን ውይይቶች አንዳቸውንም ሲጠቀምባቸው አላየሁም። ከነበረን ግንኙነት ጀምሮ በየጊዜው ለሚፈፀሙ ጥፋቶች የተለያዩ ምክንያቶች ነው የሚሰጡት።
በመጀመሪያዎቹ ወራት እነዚያን ምክንያቶች እያመንክ ትሄዳለህ፤ ነገረ ግን በቀጣይ እነዚህ ምክንያቶች በሙሉ በቂ እንዳልሆኑ እና ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌለው ወይም ብቃት የሌለው ወይም እውቀት የሌለው እንደሆነ አሁን ራሽናላይዝ [ምክንያታዊ] ማድረግ አልፈልግም። እንዲህ ዓይነት ነገር ውስጥ ለምን እንደገቡ መግለጽ የእነሱ ሥራ ነው።
እኔ ግን ያየሁት ራሱን ማረም የማይችል፣ በሕዝብ ላይ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ እና የሰብዓዊ መብት ሰቆቃ እያደረሰ ያለ፣ ዘረኝነትን በከፍተኛ ደረጃ የሚያጠናክር፣ በጣም መሰሪ የሆነ፣ አላማው ምን እንደሆነ የማይታወቅ ሥራ የሚሠራ መንግሥት ሆኖ ነው ያገኘሁት። ይህንንም በግልጽ በመግለጫ ደረጃ፣ በጽሑፍም ደጋግሜ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ልኬለታለሁ። እናም ምን አቋም እንዳለኝ ያውቃል።
ቢቢሲ፡ እነዚህን በማኅበራዊ ሚዲያም ሲያጋሩ ይታያሉ፤ ብዙ ሰውም ሃሳቡን ይገልጻል። የእርስዎን ልዩ የሚያደርገው አራት ኪሎ በስሱ አንኳኩተው መግባት ከሚችሉ ጥቂት ፖለቲከኞች አንዱ ነዎት። በንግግራችሁ ውስጥ ‘ነገሩ እንደዚህ ነው እንዴ?’ ብለው ድንጋጤ ውስጥ ሊከት የሚችል ምልክት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አይተዋል ወይ?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ማየት የለብኝም። አገሪቷ ውስጥ በዚህ ደረጃ ሰው ከመንገድ ላይ ታፍኖ ተወስዶ ሲደበደብ፣ የእነርሱን ጥቅም እና ሥልጣን ከነካህ ለምንም ነገር እንደማይመለሱ ለማወቅ ጠንቋይ መሆን አሊያም የሮኬት ሳይንቲስት መሆን የለብህም።
አንድ ነገር ንገረኝ ካልከኝ፣ በመጨረሻው መልዕክቴ በአማራ ክልል ላይ የሚሠሩትን ነገር በተመለከተ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክት ልኬያለሁ።
ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ከትግራይ አካባቢ የሰላም ስምምነቱን የማይቀበሉ ኤርትራውያንን እና የአማራ ክልልን ከማዕከላዊ መንግሥቱ ጋር ሆነን እንወጋለን የሚል ተደጋጋሚ የሆነ ውይይት ከማዕከላዊ ኮሚቴያቸው ጋር አድርገው ይህ መረጃ እኔ ጋ ደረሰ። እኔ እንደተለመደው ይህን መረጃ ለእሱ አስተላላፊ ነኝ። ምክንያቱም እዚያ ያሉ ሰዎች ለእሱ እንዳስተላልፍ ከእርሱ ጋር ስምምነት ገብተው፣ እርሱም የገባበት የመረጃ መቀባበል መንገድ ነው።
ታዲያ የአማራ ክልል ቀውስ ሲነሳ፣ ‘እነዚህ ሰዎች ሲሉት የነበረው አማራን የማጥፋት እርምጃ ተጀመረ ወይ?’ ብዬ ነው መልዕክት የላኩለት። ይህንን እየተናገርክ እዚያ አትቀመጥም። እስካሁን የሚችለውን ያህል ችሏል። ከዚህ በኋላ ወደ ምን ሊሄዱ እንደሚችሉ ገምቶ በጊዜ መውጣቱ አይከፋም።
ቢቢሲ፡ ይህንን መልዕክት ሲልኩላቸው ምን ምላሽ አገኙ?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ምንም መልስ የለም። እንዲያውም የመጨረሻው ኩርፊያው የመጣው ከዚያ በኋላ ነው። እንደዚህ ዓይነት መልዕክት መቀባበልም የቆመው ከዚያ በኋላ ነው።
ቢቢሲ፡ እርስዎ ሲነሱ በተለይ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በማቀራረብ፣ በማገናኘት ሁነኛውን ሚና ተጫውተዋል ከሚባሉ ሰዎች አንዱ ነዎት። የእርስዎ ከአገር መልቀቅ በሁለቱ መሪዎች መካከል ያለ ግንኙነት የተወሰነ ነፋስ እንደገባው የሚገምቱ ሰዎች አሉ። እርስዎ ምን ይላሉ?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ነፋስ መግባቱንም አለመግባቱንም አላውቅም። አንተ እንዳልከው ግን አንደኛው ሰው አይደለሁም። ያ ሠላምና እርቅ የተፈጠረበትን ግንኙነት ለመመሥረት ሚና የተጫወትኩ ብቸኛው ሰው ነኝ። አሁን ስላላቸው ግንኙነት የውስጥ መረጃ የለኝም። ነገር ግን ጠቅላላ እየሆነ ባለው ነገር ሰው ሁሉ መገመት የሚችል ይመስለኛል።
ብዙ ግንኙነቶች አትመለከትም። ባለፈው ግብፅ ላይ ከተገናኙ በኋላ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ይመጣል ተብሎ ነበር አልመጣም። ለምን ይመጣል ብለው እንደዚያ ዓይነት ነገር እንዳወጡም አላውቅም። ከዚያ የባሰ ነገር ውስጥ ገብተው ከሆነም ወደፊት የምናየው ይሆናል።
ቢቢሲ፡ የባሰ ነገርስ ይመጣል ብለው ይገምታሉ?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ይህ መንግሥት ጠቅላላ የሚሠራውን ነገር ከተመለከትክ፣ በዲፕሎማሲውም እየሠራቸው ያሉትን አጠቃላይ የተዝረከረኩ እና በደንብ ያልታሰበባቸው ነገሮች ከተመለከትክ፣ ምንም ዓይነት ነገር ለመሥራት፣ ምንም ዓይነት ጥፋት ለማጥፋት የሚቸግረው፣ የሚሳነው ነው የሚል እምነት የለኝም። ስለዚህ ምን ይታወቃል።
ቢቢሲ፡ ለሁለት ዓመት የተካሄደውን ጦርነት ባስቆው የፕሪቶሪያው ስምምነት ደስተኛ ነዎት?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ከዚያ በፊት እንዲያውም ከአንድ ሚዲያ ጋር ባደረኩት ውይይት፣ ይህንን ጦርነት ማስቆም የሚቻል ከሆነ በተለይ መሪዎቹ ለንብረታቸው እና ለሕይወታቸው የሚጨነቁ ከሆነ መንግሥት ከአገር የሚወጡበትን መንገድ ያመቻችላቸው ብዬ ነበር፤ ሲጨንቀኝ ማለት ነው።
ከዚያ በኋላ ወደ ሰላም ስምምነቱ ሲመጡ በጣም ደስተኛ ነው የሆንኩት። በተለይ ደግሞ የሰላም ስምምነቱ የተቋጨበት መንገድ በጣም ጥሩ ነበር። በእብሪት ተነሳስተው ለፈፀሙት ነገር የሚመጥን ስምምነት ነው። ከባድም ቀላልም መሣሪያቸውን እንዲያወርዱ ነው የሚለው ስምምነቱ። ያ ስምምነት የምርኮኝነት ስምምነት ነው ማለት ይቻላል።
እነርሱም እጅ ሰጣችሁ ተብለው ተከሰዋል። ነገር ግን ያ ስምምነት ካለቀ በኋላ ኬንያ ላይ ዐቢይ ሬድዋንን እና ብርሃኑ ጁላን ልኮ፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩትን ሌሎች ሰዎችን አግልለው ከእነርሱ ጋራ ምን እንደተነጋገሩ እስከዛሬ ድረስ መረጃ የለም። እዚያ ስብሰባ ላይ የተነጋገሩት ነው መሣሪያ እንዳያወርዱ ያደረጋቸው? በዚህ ላይ በጣም ዝርዝር ነገር አለኝ። አሁን ወደዚያ ዝርዝር አልገባም።

ቢቢሲ፡ የቀድሞ ጓድዎ የነበሩት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አሁን በቅርብ ከመንግሥት ጋር እየሠሩ ነው። የካቢኔ አባልም ናቸው። ሁለታችሁ ከዚያ በኋላ ትገናኙ ነበር ወይ? አሁን እርሳቸው ለመንግሥት ካላቸው ቅርበት እና በቅርብ ከመሥራታቸው አንጻር የተፈጠረበዎት ቅሬታ አለ ወይ?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ለምን ቅሬታ ይኖረኛል። ግልጽ የሆነ አቋሜን ነግሬሃለሁ። ያ ጦርነት በነበረበት ወቅት በፊት ለፊት በአካል አግኝቼ የአንተ ድርጅት ኢዜማ፣ ሌሎችም ድርጅቶች እንደ አብን ዓይነቶቹ ያ ጦርነት በነበረበት ወቅት አገር መታደግ እንዲቻል ከመንግሥት ጎን ቆማችሁ መሥራታችሁ፣ መታገላችሁ እና ሌላው ሌላው ነገር ትክክል እና ተገቢ ነበር።
ያ ካበቃ በኋላ በጠቅላላ በአገሪቷ ውስጥ ከኢኮኖሚ አንስተህ እስከ ማኅበራዊው እና ከፀጥታ ጋር የተገናኙ ሁኔታዎች ችግር ውስጥ በወደቁበት ሰዓት ከዚህ መንግሥት ጋራ ተጣብቃችሁ የተፎካካሪን ሥራ አለመሥራት ራሱን የቻለ ወንጀል ነው። የፓርቲ ሰዎቻችሁ በሙሉ ይህንን ጉዳይ አምርረው እየተቃወሙት ነው። ምንድን ነው ተለጥፋችሁ እዚያ የምትሠሩት? ከዚህ በኋላ መሥራት የሚገባው የትክክለኛ ተፎካካሪ ሥራ ነው፤ ብዬ በሥነ ሥርዓቱ አነጋግሬያለሁ።
ቢቢሲ፡ ራሳቸው ፕሮፌሰር ብርሃኑን አነጋግረው ያውቃሉ?
አቶ አንዳርጋቸው፡ አነጋግሬው አውቃለሁ። የፓርቲው አባላት በሆኑ በሦስት የተለያዩ ቡድኖች ተልኬ አነጋግሬዋለሁ። የሰጠኝ መልስ በጣም ግልጽ ነው፤ ቀላል ነው። ‘ወደዚያ የገባንበት የፓርቲ አካሄድ አለ። አባላቱ ይህንን ነገር ከፈለጉ የዚያ ዓይነት ስብሰባ እና አካሄድ አምጥተው እዚያ የገባንበትን ውሳኔ ማስወሰን ይችላሉ’ የሚል እንጂ፣ አዎ! ይሄ ነገር እውነት አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል፤ እኔ ተነሳሽነቱን ወስጄ ከዚህ ዓይነት ነገር እንወጣለን የሚል አቋም የሌለው መሆኑን ነው ያየሁት።
በዚያው የመቀጠል ፍላጎት ነው ያለው። ለምን በዚያው ይቀጥላል የሚለውን ለእርሱ ራሽናላይዝ [ምክንያታዊ] አላደርግለትም። ነገር ግን ትክክል እና ተገቢ ያልሆነ በወያኔ ዘመን ካየነው ግፍ፣ በደል፣ ሌብነት እና ዘረፋ በላይ በአሁኑ ዘመን እየተፈፀመ፤ ወያኔን ተቃውመን ይህንን የብልጽግና መንግሥት የማንቃወምበት ምንም ምክንያት ሊኖረው እንደማይችል አውቃለሁ። ሌላውን ምክንያት እርሱም ሆነ ሕዝቡ ሊመልሰው ይችላል። የእርሱን ግላዊ ፍላጎት እንዲህ ነው እንዲያ ነው ማለት አልችልም።
ቢቢሲ፡ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ከአገር እንደሚወጡ ያውቁ ነበር?
አቶ አንዳርጋቸው፡ አያውቅም።
ቢቢሲ፡ በጣም የቅርብ ወዳጅ እና የትግል አጋር ናችሁ ብዬ ነው።
አቶ አንዳርጋቸው፡ ጌታዬ፣ እኔ አልተነጋገርኩም። አልነግረውምም። ምክንያቱም ከመንግሥት ጋር ባለው ግንኙነት እኔ ምንም የምናገርበት ምክንያት የለም። በጣም ‘ሴንሲቲቭ’ የሆነ ሁኔታ እየተፈጠረ እንደመጣ በራሴ የገመትኩት ነገር አለ። ድንገት መጥፎ ነገር ሳያስብ እንኳን ለሰዎች ‘አይ እርሱ እኮ እንደዚህ ሆነ፣ ሊወጣ ነው’ ቢል ሊመጣ የሚችለውን ነገር ስለማውቅ መውጣቴን ለሰዎች ሳልነግር ነው የወጣሁት።
ቢቢሲ፡ ቀጣይ ምንድን ነው ሊያደርጉ ያሰቡት? ወደ ኤርትራ በረሃ ይመለሳሉ?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ትግል ብዙ መልክ አለው። የሚታገሉ ሰዎች አገር ውስጥ አሉ። አላግባብ ግፍ እየተፈፀመባቸው እያለቁ ያሉ፣ እየተገፉ ያሉ፣ ምድር ላይ የሚታገሉ ሰዎች አሉ። የእነዚህን ሰዎች ትግል በብዙ መንገድ መደገፍ ይቻላል። የማደራጀት ልምድ አለን፣ የሕዝብ ግንኙነት ልምድ አለን፣ የዲፕሎማሲ ልምድ አለን። በወታደራዊው መንገድም ቢሆን አንድ ሠራዊት ማሟላት የሚገባቸውን ጽንሰ ሃሳቦች፣ ከሥነ ምግባር አንስቶ ሊኖረው ስለሚገባ ሥነ ልቦና የመሳሰሉ ነገሮች ምን መሆን እንዳለበት እናውቃለን።
እና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሰፊ የሆነ አሁንም በውጭ የሚገኝ እነሱን ሊደግፍ የሚችል እስካሁን ከእኛ ጋር የተቆራኘ የሰው ኃይል አለ። እነዚህንም እንዲደግፏቸው ማድረግ እንችላለን። ማድረግ የማንችለው ነገር ይህንን ግፍ በዝምታ ማለፍ ብቻ ነው።
ቢቢሲ፡ ከምላሽዎ የምረዳው የትጥቅ ትግል ሊኖር እንደሚችል ነው።
አቶ አንዳርጋቸው፡ እኔ አላልኩም። የትጥቅ ትግል የሚታገሉ አሉ እኮ። የትጥቅ ትግል ምሥጢር አይደለም እኮ፤ እዚያው መሬቱ ላይ እየታገሉ ነው። እየሰማህ ነው። መሣሪያ ያልያዙ ሰዎች ናቸው በሁለት ሳምንት ውስጥ እነዚህን ሁሉ በአማራ ክልል ያሉ ከተሞችን የተቆጣጠሩት።
ዝም ብለህ ስትመኝ ብትውል እነዚህ ኃይሎች ብን ብለው አይጠፉም። ሰላማዊ ሰዎችን በድሮን ደበደብክ እና ጠመንጃ የያዘው ሰው መሣሪያ ይዞ እየሮጠ ወዳንተ ይመጣል ማለት አይደለም። ይህ ደግሞ ባለኝ መረጃ የጥቂት ፋኖዎች ትግል አይደለም። የጥቂት ሚሊሻዎች ትግል አይደለም። ይሄ የሕዝቡ ትግል ነው።
የፈለገውን ፕሮፖጋንዳ በሞኖፖል በያዘው ሚዲያ እንዲህ እያለ ቢያሰራጭም፣ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሐቅ የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች አሉ። ስለዚህ ይሄ ኃይል ለነጻነቱ፣ ለመብቱ፣ ለህልውናው በተለይም የአማራ ክልል ለሕልውናው የሚያደርገውን ትግል እንደግፈዋለን።
ቢቢሲ ፡ የተለያዩ ነገሮች እየተባሉ ነው። በአንድ በኩል አንድን በታሪክ ተገፍቻለሁ ብሎ የሚያምንን ብሔር ታላቅ ኃይል አድርጎ የማውጣት ተልዕኮ አለ ብለው የሚያስቡ አሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን ታላቅ የማድረግ ህልም ነው ያላቸው፤ ነገር ግን አልሳካ ብሏቸው ነው የሚሉም አሉ። እርስዎ ከዚህ አስተዳዳር ጋር ቅርብ ሰው ስለነበሩ ብዙ ምልክቶችን አይተው ሊሆን ይችላል። ምንድን ነው እየሆነ ያለው?
አቶ አንዳርጋቸው፡ እየውልህ ከዚህ ቀደም ለተለያዩ ድርጊቶቻቸው፣ ለሚፈፀሙ ጥፋቶች ወይም አንዳንዴ ደግሞ ለሚሰሩት በጎ ነገሮች ምክንያቶችን በመስጠት ነው ስኖር የነበረው። አሁን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነው በአጠቃላይ ከዘረፋ አንስተህ እስከ ግድያ እስከ ማፈናቀል፣ ጦርነት በንጹሃን ላይ ማወጅን ተከትሎ በመጣው ጉዳይ ላይ እኔ፣ ለምንድን ነው ይህንን የሚሰሩት? እውነት መሠሪነት ነው? ስህተት ነው? በድክመት ነው? በአቅም ማነስ ነው? የሚሉ ምክንያቶችን ለእነሱ መደርደር ከሚያስፈልገኝ ወቅት በላይ ተሻግሬ ሄጃለሁ።
ለዚህ እነሱ ይህ ችግር ገጥሞናል ብለው ማብራሪያ ይስጡ። እኔ ግን ድርጊታቸው መቆም አለበት፣ ሕዝብ ሊያስቆማቸው ይገባል የሚል አቋም ወስጃለሁ። በዚያ ላይ ጊዜ ማጥፋት እንዲያውም እነዚህን ሰዎች ለሚቃወም ኃይል ትክክል ነው ብዬ አላምንም። ይህ ችግር ቢገጥማቸው ነው፣ ይህ ባይሟላላቸው ነው እያልን በተለያየ ጊዜ ለሚፈጠሩ ችግሮች በቂ የሆነ ጊዜ ሰጥተናቸዋል። ግን በአምስት ዓመት ውስጥ እነዚህ ነገሮች፣ መጀመሪያ አካባቢ እውነት ሊሆኑ ይችላሉ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን እነዚህ ነገሮች ማስመሰያ እና ማጭበርበሪያ ሆነው ነው ያገኘኋቸው።
ስለዚህ እኔ አያገባኝም። ሰውዬው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ ነው ወይስ የኦሮሞ ብሔርተኛ ነው? የሚለው ከዚህ በኋላ የእኔ ጉዳይ አይደለም። የማውቀው ሌቦች አገር የሚያዘርፉበት፣ ንጹሃን በድሮን የሚደበደቡበት፣ በየመሥሪያ ቤቱ በወያኔ ጊዜ ከነበረው በላይ ተራ ሠራተኛ ሳይቀር ያለ ጉቦ ምንም ሥራ የማይሠራበት ሁኔታ የተፈጠረበት እና በተለያዩ መስኮች አገሪቱ ችግር ውስጥ የገባችበት ሁኔታ ነው ያለው።
መሠረታዊ ነገሮች ከመሥራት ይልቅ የተብለጨለጨ ነገሮች ላይ በመንጠልጠል ይህንንም በሕዝብ ግንኙነት ሚዲያዎች እያሰራጩ ትልቅ ነገር እንደሰሩ አድርጎ የሚያወራ ዓይነት ሰው ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ምን ነክቶት ነው? ምን ችግር ገጥሞት ነው? ማለት የእኔ ሥራ አይደለም።
ቢቢሲ፡ ንጹሃንን በድሮን የሚጨፈጭፍ ብለዋል። በትግራይ ጦርነት ጊዜ ንጹሃን በድሮን ተመትተዋል። ወለጋ በተደጋጋሚ ተመትተዋል። ግን እርስዎ ያለ ዛሬ ይህንን ሲሉ አልሰማሁም። ልክ ነኝ?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ትግራይ ውስጥ በነበረው ጦርነት በድሮን ንጹሃን መመታታቸውን በተጨባጭ በጆሮዬ ቦታው ላይ ስልክ ደውዬ ያላረጋገጥኩት ነገር ነው። በሌላ መንገድ ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ተብሎ ‘ኮላተራል’ በምትለው መልኩ የሚመታ ነገር በተወሰነ ደረጃ ትቀበላለህ።
አካባቢው ምንም ነገር የሌለበት ፍኖተ ሰላም ከተማ መሃል ላይ ድሮን የመታው መሣሪያ የታጠቀ ሰው በሌለበት ቦታ ላይ ነው። የዚያ ዓይነት ነገር ትግራይ ላይ የተፈፀመበት ሁኔታ ቢኖር ይህንንም እቃወም ነበር። ንጹሃን በድሮን ኦሮሚያ ውስጥ የተደበደቡበት ሁኔታ፣ እዚህ ከተማ ላይ በእንዲህ ዓይነት መንገድ ልክ አሁን ፍኖተ ሰላም እንዳለው እስኪ ኦሮሚያን አምጣልኝ። የት ከተማ ነው? የት ቦታ ነው ይህ የሆነው? ጂማ ነው? ናዝሬት ነው? ወለጋ ነው ይህ ሆነው? በዚህ ደረጃ ማስረጃ አምጣልኝ።
ቢቢሲ፡ ንጹሃን ሞቱ ተብሎ እኛ በተለያየ ጊዜያት ስንዘግብ ነበር። ነገር ግን አጭሩ መልስዎ ሊሆን የሚችለው እኔ መረጃ በሌለኝ ነገር ሐዘኔን ልገልጽ አልችልም ነው ያሉት?
አቶ አንዳርጋቸው፡ እንደዚያ ነው እንጂ፤ ማስረጃ ያለን ሰዎች እኮ ነን። እኔ በአማራ ጉዳይ ላይ ወይም በአማራ ሕዝብ ላይ በሚደርሱ ነገሮች ከጻፍኳቸው መግለጫዎች ወይም ሐተታዎች ወይም ከተናገርኳቸው በላይ ስለሌሎች ተናገሪያለሁ።
ለምሳሌም ወያኔ ጋምቤላዎች ላይ በፈፀመው እልቂት፣ ወያኔ ኦጋዴን ላይ መንደሮችን ወደ አመድነት የቀየረበትን ዓይነት የጥፋት እርምጃ፣ ኦሮሚያ ውስጥ ይፈፀሙ የነበሩትን ግፎች እና በደሎች ላይ ነው በአብዛኛው መግለጫ እና ጽሁፍ ያወጣሁት።
በአማራ ጉዳይ ላይ እንዲህ ዓይነት ነገር ስሠራ አላስታውስም። ስለዚህ የአንድ ወገን ወይም ብሔር ወገንተኝነት ኖሮኝ የአንዱን ጥፋት እና ሞት የማሳነስ የመሸፋፈን የሌላውን የማጋነን ባህሪ የለኝም።
በየትኛውም መጽሐፌ፣ ቃለ ምልልስ፣ በየትኛውም ጽሑፍ፣ በየትኛውም መግለጫ፣ በየትኛውም ሥራዬ እነዚህን ነገሮች ፊት ለፊት አስቀምጬ የምሄድ ሰው ነኝ። ነገር ግን በቂ መረጃ ማስተላለፍ ያለባቸው አካላት አላወጡትም፤ እኔም አላየሁም።
ቢቢሲ፡ በእስር ላይ እያሉ የለውጡ ጊዜ አቶ አንዳርጋቸው መፈታት የለባቸውም ተብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወሰዱት አቋም መፈታትዎ ሲነገር ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንደ ባለውለታ ይቆጥሯቸዋል?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ይህ ሰውን አለማወቅ ነው። ብዙ ጊዜ ከሰዎች ጋር ምነጋገረው ነገር ነው። የእኔ ትግል የመጨረሻ ግብ አንድ ሰው እስር ቤት ከጨመረኝ በኋላ ከእስር ይፈታ የሚል አንዲሆን አይደለም። ወይም ደግሞ ከእስር ቤት የሚፈታኝ ሰውዬ ባለውለታ ሆኜ እንድቀር አይደለም የታገልኩት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን በተፈታሁበት ጊዜ ቢሮው ያገኘሁት ዕለት አንድ ሰዓት ተኩል ነው የተነጋገርነው። ምንም የቀረኝ ነገር የለም፤ ሌብነት እና ዘረፋን ጨምሮ ፍራቻዬን በሙሉ ተናግሬያለሁ። ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያን ሕዝብ ችግር ለማቃለል ስለማይቻል እንደ እርሱ መራብህን እያሳየህ ካልመራኸው በስተቀር ችግር ውስጥ ነው የምትወድቀው፤ እና ሽሮ እንደምትበላ የምትበላውን እና ምትጠጣውን ሳይቀር እንዲያይ ቤትህ ውስጥ ካሜራ ገጥመህ በቀጥታ አሳየው ብዬው ነው የሄድኩት።
ቢቢሲ፡ ምን ነበር ያኔ ስሜታቸው?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ብዙ ነገር ነው። የዚያን ጊዜ የብሔር ፖለቲካውን አደገኛነትን በተመለከተ አንስቻለሁ። አገሪቷን ከፍተኛ ወደ ሆነ ችግር ውስጥ ሊጨምራት የሚችል ደረጃ ላይ ደርሷል። ሙስና ራሱን የቻለ አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፤ እና ፖለቲካው ውስጥ ያለው ቀውስ አገሪቷን የማያፈርሳት ከሆነ ሙስና ራሱ ያፈርሳታል። ሙስናን በተመለከተ በጣም ጠንካራ የሆነ አቋም መወሰድ እንዳለበት ነው የነገርኩት። ግን ዙሪያውን የሰበሰባቸው ሰዎች ምን ያህል በሌብነት የከበሩ ሰዎች አንደሆኑ አንዳንዶቹን እናውቃለን። ሌብነት የምትጠየፍ ከሆነ በሌባ አትከበብም። በቃ! የእኔ ችግር ይሄ ነው። የዚያን ጊዜ እነዚህን ነገሮች አድርጎ ቢሆን ኖሮ ለአገር የሚበጅ ነው ብዬ ስለማስብ፤ አንኳን ልቃወም ቀርቶ ለእርሱ የተተኮሰ ጥይት ፊት ለመቆምም ወደ ኋላ አልልም ነበር።
ቢቢሲ፡ አሁንም ያሉት ያኔ ያነጋገሯቸው ጠቅላይ ሚኒስትር እኮ ናቸው፤ በዚያ ጊዜ የተፈጠረበዎ ስሜት እና አሁን ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲያዩ ምንድ ነው የተቀየረው?
አቶ አንዳርጋቸው፡ ቅድም ተናገርኩህ እኮ። እኔ ራሽናላይዝ አላደርግም፤ የእኔ ሥራ አይደለም። የገጠመኝ ችግር ይህ ነው፤ የነበረን ዓላማ ይህ ነው። ግን አንዲህ ሆኖ ነው ለውጡ የተጨናገፈው ብሎ የሕዝብ ማሳመኛ ካለው ለሕዝቡ ይንገረው። ነገር ግን እኔ እስከማየው ድረስ ለውጥ የሚባለው ነገር ተቀልብሷል።
ቢቢሲ፡ ግን ያምኗቸዋል?
አቶ አንዳርጋቸው፡ የሠራው ሥራ የሚያሳምን ነው እንዴ? ለምንድን ነው የማምነው? የሚሠራቸው ሥራዎች፣ የሚያደርጋቸው ነገሮች እና በየጊዜው ሚዲያ ላይ እየተወጣ የሚነገረው ውሸት ሰዎቹ አይደሉም ፈጥረው እያቀረቡት ያለው። በሙሉ ማዕከላዊነት ያለው ሥራ የሚሠራ ፖለቲካዊ ድርጅት ነው ያለው። ይሄ በየጊዜው የተለያየ ክልል መግለጫ አወጣ የሚባለው ነገር ከማዕከል ነው የሚዘጋጀው።
የተደራጀ የፖለቲካ ድርጅት አንዴት አንደሚሠራ እኮ ከኢሕአፓ ዘመን ጀምሮ ነው የማውቀው። በእንዲህ ዓይነት ድርጅት ውስጥ ምንም አይነት የግለሰቦች ወይም የቡድኖች ነጻ አስተያየት የለም። ስለዚህ ችግር ከተፈጠረ በተለይ በጣም ሰፊ እና አባላት በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ድርጅት ከሆነ አንድ ሰው ነው ያደረገው ልትል ትችላለህ፤ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ከታች እስከላይ በማዕከላዊነት ተጠርንፎ በሚሠራ ድርጅት የሚፈፀም ማንኛውም ነገር ሄዶ አናቱ ላይ ነው የሚመጣው። ከአናቱ እውቅና ውጪ የሚሠራ ነገር የለም።
ቢቢሲ፡ ለመጨረሻ ጊዜ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የተገናኙት አንድ ለአንድ ነበር?
አቶ አንዳርጋቸው፡ አዎ። ብዙ ጊዜ እንደዚያ ነው የምንገናኝ የነበረው። ጊዜውን በመስጠት በኩል ከሚገባው በላይ ጊዜ ሰጥቶኛል ብዬ ነው ያማስበው።
ቢቢሲ፡ ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ያወሩት ወይም መልዕክት የተለዋወጡት መቼ ነው?
አቶ አንዳርጋቸው፡ እኔ የመጨረሻውን ጊዜ አላስታውስም። ምናልባት አራት ወይም አምስት ዓመት ሊሆን ይችላል። ወደ ኤርትራ ሁለት ጊዜ ሄጃለሁ፤ የሄድኩትም የማውቃቸው ሰዎችን ሐዘን ለመድረስ እና ለሠርግ ነበር። በዚያ ወቅት የኤርትራ ፕሬዝዳንትን እና የመንግሥት ባለሥልጣናትን አላገኘሁም። ከፕሬዝዳንቱ ጋር ከተገናኘን አምስት ዓመት ሊሞላው ነው።
ቢቢሲ፡ ስለዚህ በሁለቱ መሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል የሚለው ላይ መረጃ የልዎትም?
አቶ አንዳርጋቸው፡ አዎ። ምንም የለኝም።












