ኪም እና ፑቲን ሊገናኙ ነው

ኪም እና ፑቲን በ2019 በተገናኙ ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY IMAGES

የምስሉ መግለጫ, ኪም እና ፑቲን በ2019 በተገናኙ ጊዜ

የሰሜን ኮሪያው ፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን በዚህ ወር ሩሲያን ሊጎበኙ ነው።

ኪም ጆንግ ኡን ወደ ሩሲያ አቅንተው ፑቲንን የሚያገኙበት ዋናው ምክንያት በጦር መሣሪያ ዙርያ ለመነጋገር እንደሆነ ተዘግቧል።

ሩሲያ በዩክሬን ጦርነት የሚያስፈልጋትን በቂ የጦር መሣሪያ ከሰሜን ኮሪያ እንዲቀርብላት በጽኑ ትፈልጋለች።

ሁለቱ ኃያል መሪዎች ተገናኝተው የሚመክሩበት ዋንኛው አጀንዳም ይኸው ሊሆን እንደሚችል ተጠቅሷል።

ሁለቱ መሪዎች በትክክል የት እንደሚገናኙ ስፍራው አልተመላከተም።

የኪም እና የፑቲን መገናኘት ጉዳይ መጀመርያ የተዘገበው በቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ አጋር፣ ሲቢኤስ ቴሌቪዥን ሲሆን ይህ ሚዲያ ለመረጃው ምንጭ ያደረገው ደግሞ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣንን ነው።

ይህ ዜና ከሩሲያም ሆነ ከሰሜን ኮሪያ በኩል አልተዘገበም።

ሌሎች የዜና ምንጮች ለኒው ዮርክ ታይምስ እንደተናገሩት ደግሞ ኪም ወደ ሩሲያ የሚያጓዙት በጦር ባቡር ሊሆን ይችላል።

የጦር ባቡር የሚባለው ጥይት በማይበግረው የብረት ልባስ የተሠራና በርካታ የጦር ቅኝት መሣሪያዎች የተገጠሙለት ልዩ ወታደራዊ ባቡር ነው።

የሁለቱ መሪዎች የመገናኘት ዜና የወጣው አሜሪካ ኪምና ፑቲን በጦር መሣሪያ ዙርያ እየተነጋገሩ እንደሆነ መረጃ አለኝ ማለቷን ተከትሎ ነው።

የአሜሪካ የብሔራዊ ደኅንነት ካውንስል ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ እንደተናገሩት ደግሞ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ ወደ ፒዮንጊያንግ ባቀኑ ጊዜ ኪም ለሩሲያ የጦር መሣሪያ እንድታቀርብ አግባብተዋቸዋል።

ከዚያን ጊዜ ወዲህ ኪምና ፑቲን ትብብራችን እንዴት ይጠናከር በሚለው ዙርያ በደብዳቤ ሐሳብ ሲለዋወጡ ቆይተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አሜሪካ የሁለቱን መሪዎች ግንኙነት እንዳሳሰባት የገለጸች ሲሆን ሰሜን ኮሪያ መሣሪያ እንዳታቀርብ የተጣለባትን ማዕቀብ እንድታከብር ጠይቃለች።

እንደተፈራው ሰሜን ኮሪያ ለሩሲያ የጦር መሣሪያ የምታቀርብ ከሆነ አሜሪካ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደምትጥል የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ካውንስል ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ ተናግረዋል።

ኪም እና ፑቲን መገናኘታቸው ያስጨነቃት አሜሪካ ብቻ አይደለችም። ደቡብ ኮሪያም በተመሳሳይ ነገሩ አሳስቧታል።

ሁለቱ አገሮች ከሁሉ ያሳሰባቸው ደግሞ ኪም ለሩሲያ ጦር መሣሪያ ስታቀርብ በምላሹ ሰሜን ኮሪያ ከሞስኮ ምንድነው የምታገኘው የሚለው ነው።

የደቡብ ኮሪያ ደኅንነት መሥሪያ ቤት እንደሚጠረጥረው ምናልባት ሦስቱ አገሮች ማለትም ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያና ሩሲያ በጋራ የባሕር ኃይል ጦር ልምምድ ለማድረግ የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾይጉ ሐሳብ ሳያቀርቡ አልቀረም።

ከሁሉም በላይ አሳሳቢ የሆነው ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያ በኒክሊየር ጦር መሣሪያ ዙርያ በዕውቀት ልታግዛት ትችላለች የሚለው ነው።

ሌሎች ደግሞ ይህ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ምናልባት ስልታዊ የጦር አጋርነት ግንኙነት ሳይሆን መደበኛ የንግድ ግንኙነት ብቻ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።

እነዚህ ተንታኞች እንደሚሉት ሩሲያ ጦር መሣሪያን ተጠምታለች፤ ሰሜን ኮሪያ ደግሞ በቂ የምግብ አቅርቦት የላትም። ስለዚህ ኪም ለሚያቀርቡት የጦር መሣሪያ ከሩሲያ ጠርቀም ያለ ገንዘብ ትከፍላለች ይላሉ።

ኪምና ፑቲን በክሬምሊን ወይስ በሌላ ቦታ ይገናኙ የታወቀ ነገር ባይኖርም ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ምንጮቼ ነገሩኝ ብሎ እንደዘገበው ኪምና ፑቲን የሚገናኙት በምሥራቅ ጠረፍ ሩሲያ በምትገኘው ቪላዲቮስቶክ በምትባል የወደብ ከተማ ነው።

ጋዜጣው ምንጮቹን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ከሳምንታት በፊት የሰሜን ኮሪያና የሩሲያ ኃላፊዎች የፕሮቶኮል ጉዳዮችን ለማሰናዳት ወደዚህች የወደብ ከተማ አቅንተው ነበር።

አንድ ከዚህ ቀደም በሰሜን ኮሪያ የዩኬ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ዲፕሎማት ለቢቢሲ ሲናገሩ ኪም ለደኅንነታቸው እጅግ የሚጨነቁ መሪ ከመሆናቸው የተነሳ ምናልባት የሚገናኙበት ቦታ ቀድሞ ከታወቀና በዚህም ስጋትና ጭንቀት ከገባቸው በመጨረሻ ሰዓት ጉብኝታቸውን እስከመሰረዝ የሚሄዱ መሪ ናቸው ብለዋል።

ኪምና ፑቲን ከዚህ ቀደም ሚያዝያ 2019 ዓ/ም በዚህችው አሁን ይገናኙባታል ተብሎ በሚገመተው ቪላዲቮስቶክ ከተማ ተገናኝተው ነበር።

ይህን የሆነው ኪም ትራምፕን በቬትናም ካገኟቸውና ከተወያዩ በኋላ ውይይቱ ፍሬ ሳያፈራ መቅረቱን ተከትሎ ነበር።