ባይደን የሰሜን ኢትዮጵያው ሁኔታ ባለመሻሻሉ ያስተላለፍኩት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ እንዲራዘም ወስኛለሁ አሉ

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ መሻሻል ባለማሳየቱ ከዚህ ቀደም የተላለፈው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ በአንድ ዓመት እንዲራዘም ወስኛለሁ አሉ።

ፕሬዝዳንቱ ከሁለት ዓመት ገደማ በፊት መስከረም 7/2014 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ጥሰቶችን ፈጽመዋል በተባሉ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።

ይህ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተሳታፊ በሆኑት የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የኤርትራ መንግሥት፣ የአማራ ክልል አስተዳደርና የህወሓት አባላት ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ነው።

ለኢትዮጵያ ደኅንነት ስጋት የፈጠሩ፣ ጦርነቱ እንዲራዘም አስተዋጽኦ ያደረጉ፣ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነትን ያደናቀፉ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ፣ ተኩስ አቁም እንዳይደረስ እክል የሆኑ፣ በጦርነቱ ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ ያደረጉ እና ሌሎች ላይ ማዕቀብ መጣል ያስችላል።

ፕሬዝዳንቱ ትናንት ሐሙስ ጷጉሜን 2/2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ በሰሜን ኢትዮጵያ አሁንም ያለው ሁኔታ የአገሪቱን እና የመላው የአፍሪካ ቀንድ ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋት ስጋት በመሆን በመቀጠሉ ዩናይትድ ስቴትስ በቀጠናው ያላትን ብሔራዊ ደኅንነት እና የውጭ ፖሊሲ አደጋ ውስጥ የሚከት ነው ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ፕሬዝዳንቱ በፊርማቸው መስከረም 7/2014 ዓ.ም. አስተላልፈውት የነበረው እና መስከረም 6/2016 ዓ.ም. ማብቃት የነበረበት ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ በአንድ ተጨማሪ ዓመት እንዲራዘም ወስነዋል።

ምንም እንኳ ይህ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ እንዲወጣ ምክንያት የሆነው የኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት ፕሪቶሪያ ላይ በተደረሰው የሰላም ስምምነት ቢያበቃም በጦርነቱ ጥሰቶችን ፈጽመዋል በሚባሉ ሰዎች ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችለው ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም ተደርጓል።

ለሁለት ዓመታት የተካሄደው የሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሽ ጦርነት ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ኪሳራ አስከትሏል። በኢትዮጵያም በቀጠናውም ላይ ከፍተኛ አደጋም ላይ ጥሎ ነበር።

በዚህ ጦርነት በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለው የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።

በጦርነቱ ተሳታፊ የነበሩት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ኃይሎችና የህወሓት ኃይሎች ከጦር ወንጀል ጋር ሊስተካከል የሚችል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ስለመፈጸማቸው የተባበሩት መንግሥታት አስታውቆ ነበር።

ጆ ባይደን ይህን ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ሲፈርሙ ትዕዛዙን ተከትሎ የሚተላለፉ ማዕቀቦች በግለሰቦች እና ተቋማት ላይ እንጂ በኢትዮጵያ ወይም በኤርትራ ሕዝቦች ላይ ያተኮሩ እንደማይሆን ገልጸው ነበር።

"ማዕቀቦቹ ያተኮሩት በጦርነቱ ሰብዓዊ ቀውስን በፈጠሩ ግለሰቦች ወይም አካላት ላይ ነው። ከማንኛውም አገር በበለጠ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ እና የልማት ዕርዳታ እንሰጣለን። በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማቅረብ ከአጋሮቻችን ጋር መሥራታችንን እንቀጥላለን" ብለው ነበር።

ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዙን መሠረት በማድረግ የሚወጡ ማዕቀቦችን በዋነኝነት የሚያስፈጽመው የአሜሪካ ግምጃ ቤት (ዲፓርትመንት ኦፍ ትሬዠሪ) ሲሆን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱም ተባባሪ ይሆናል።

በሰሜን ኢትዮጵያ መሻሻሎች ካሉ አሜሪካ፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ጦርነት የምታገግምበትን መንገድ እና ምጣኔ ሀብቷን ለማነቃቃት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር እተባበራለሁ ብላ ነበር።

ጆ ባይደን ከሁለት ዓመት በፊት በዚህ ፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ ላይ ፊርማቸውን ካኖሩ በኋላ ኢትዮጵያ ዩናይትድ ስቴትስ በያዘችው አቋም የተሰማትን ቅሬታ ገልጻ ነበር።

የሻከረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ ኢትዮጵያ ከምዕራባውያን አገራት ጋር በተለይ ደግሞ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሻክሮ ቆይቷል።

የባይደን ትዕዛዝ መውጣን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ እያራመደችው ያለውን አቋም በማንሳት ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በደብዳቤያቸው የኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ ወዳጅ ነች ያሏት አሜሪካ "ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምትከተለው ፖሊሲ አስገራሚ ብቻ ሳይሆን በግልጽ በሚታይ ሁኔታ ለሰብዓዊነት ከመቆርቆር የዘለለ ነው" ሲሉ ተችተዋል።

አሜሪካ በሰሜኑ ጦርነት ተሳታፊዎች ናቸው ባለቻቸው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የጦር አመራሮች እና ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ከመጣሏ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ከነበረችበት የአሜሪካ የንግድ መርሃ ግብር ተጠቃሚነት መሰረዟ ይታወሳል።

ከሁለት ዓመታት ገደማ በፊት የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያና በኤርትራ ባለሥልጣናት፣ ወታደራዊና የደኅንነት አባላት፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ኃይሎችና በህወሓት አባላት ላይ የቪዛ ዕቀባ መጣሉ ይታወሳል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በግለሰቦቹ ላይ ማዕቀብ መጣል ያስፈለገው አሜሪካ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚካሄደው ግጭት እንዲቆምና የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ እንዲወጡ፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲሻሻል እንዲሁም በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑት ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመጡ ያደረገችው ጥረት ተቀባይነት ባለማግኘቱ ነው ብሏል።

በዚህ ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ ተጠቃሚ ሆና ከነበረበት የአፍሪካ የዕድገትና ዕድል ድንጋጌ (አጎዋ) የንግድ መርሃ ግብር ተጠቃሚነት እንድትሰረዝ መደረጓ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶችን ከቀረጥ ነጻ በሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ እየላከች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመከፈቱ በላይ አገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ስታገኝበት ቆይታለች።

ይሁን እንጂ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ኢትዮጵያ ከአጎዋ ሥርዓት ውጪ እንድትሆን ተደርጋለች።